ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ዩክሬን ኢትዮጵያን ጨምሮ ለተለያዩ አገራት የምትልከው እህል ምን ያህል ነው?
ባለፈው ወር 21 እህል የጫኑ መርከቦች የዩክሬንን ወደብ ለቀው ወደተለያዩ ስፍራዎች አቅንተዋል። ከዚህ ውስጥ አብዛኛው የሚሄደውም ወደ ኢትዮጵያ ነው።
ከግማሽ ሚሊዮን ቶን በላይ ስንዴ እና ሌሎች የእህል ዓይነቶች ከዩክሬን ወደቦች መጫናቸውን የተባበሩት መንግሥታት አስታውቋል።
ሐምሌ 15፣ 2014 ዓ.ም ሩሲያ በወደቦች ላይ ጥላው የነበረውን እገዳ አነሳች። ይህም መርከቦች በጥቁር ባሕር በኩል ባለው መተላላፊያ እንዲገቡ እና እንዲወጡ አስችሏቸዋል።
ይሁን እንጂ ዩክሬን በአሁኑ ወቅት እየላከች ያለችው የእህል መጠን ከጦርነቱ በፊት ከነበረው በግማሽ መጠን ያህል ነው።
ከዩክሬን የተነሳው እህል ምን ያህል ነው? ወደ ኢትዮጵያስ ምን ያህል ተልኳል?
ደኅንነቱ የተጠበቀ የባሕር መተላለፊያ (ኮሪደር) ሰኔ 15፣ 2014 ዓ.ም ከተከፈተ ጀምሮ 560 ሺህ ቶን እህል እና ሌሎች የምግብ ዓይነቶች ከዩክሬን ወደቦች ተልከዋል።
ይህ ጭነት ላይ 451 ሺህ 481 ቶን በቆሎ፣ 41 ሺህ 622 ቶን ስንዴ፣ 6 ሺህ ቶን የሱፍ ዘይትን ይዟል።
70 በመቶው የሚሆነው እህልና ምግብ ወደ ቱርክ፣ ኢራን እና ደቡብ ኮሪያም አቅንቷል።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የዩክሬን እህል ዋነኛ ገዥ ሲሆን፤ ይህንንም እህል በረሃብ አደጋ ውስጥ ወደሚገኙ አገሮችም ይልካል።
አንደኛዋ መርከብ፣ ብሬቭ ኮማንደር የምትሰኝ ሲሆን በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የተገዛውን 23 ሺህ ቶን ስንዴ ለኢትዮጵያ በጂቡቲ ወደብ በኩል ተልኳል።
የተመድ የዓለም ምግብ ፕሮግራም ከዩክሬን ለኢትዮጵያ የገዛው ስንዴ በሚቀጥለው ሳምንት ጂቡቲ ወደብ ይደርሳል ተብሎ ይጠበቃል።
የዓለም ምግብ ፕሮግራም የኢትዮጵያ ቃል አቀባይ ክሌር ኔቪል ለቢቢሲ እንደተናገሩት ስንዴው ተቋሙ በጦርነት እና በአስከፊ ድርቅ ምክንያት የተጎዱ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ነዋሪዎችን ለመመገብ የሚያደርገውን ጥረት ይደግፋል።
ከ22 ወራት በፊት በተቀሰቀሰው ደም አፋሳሽ የአርስ በርስ ጦርነት ችግር ላይ 3.4 ሚሊዮን የሚሆኑ የትግራይ ክልል ነዋሪዎችን እንዲሁም በአፋር እና አማራ ያሉ ህዝቦች ለመርዳት እንደሚውል ክሌር አክለው ገልጸዋል።
በተጨማሪ በሶማሌ ክልል በተከታታይ የዝናብ እጥረት ምክንያት በድርቅ ለተጠቁ 2.4 ሚሊዮን ነዋሪዎችን ይደጉማል ተብሎ ይጠበቃል።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እስካሁን 60 ሺህ ቶን ስንዴ ከዩክሬን በመግዛት በችግር ላይ ላሉ አገራት ለመላክ ችያለሁ ብሏል።
የባሕር መተላላፊያ (ኮሪደሩ) መከፈቱን ተከትሎ የዓለም የምግብ ዋጋ መቀነስ አሳይቷል።
የዓለም የምግብ እና የእርሻ ድርጅት (ፋኦ) መረጃ እንደሚያሳየው የሐምሌ ወር የዓለም አቀፉ የምግብ ዋጋ 9 በመቶ ቀንሷል።
የባሕር ኮሪደሩን የሚያስተዳድረው የጋራ ማስተባበሪያ ማዕከል (ጄሲሲ) እንዳስታወቀው 15 የጭነት መርከቦች በአሁኑ ወቅት በጥቁር ባሕር ወደ ዩክሬን ወደቦች በመጓዝ ላይ ናቸው።
የዩክሬን መንግሥት በበኩሉ በወደቦቻቸው 30 መርከቦች ምግብ ለመጫን ጥያቄ ማቅረባቸውን ተናግሯል።
በዩክሬን ምን ያህል እህል ተከማችቷል?
ሩሲያ ዩክሬንን መውረሯን ተከትሎ ከዩክሬን እህል መውጣት አልቻለም።
ከየካቲት ጀምሮ ወደ ውጭ አገራት ለመላክ የታሰበ 20 ሚሊዮን ቶን እህል፣ በቆሎ የመሳሳሉ ሌሎች ምግቦች እና የሱፍ ዘይት ተከማችቶ ይገኛል።
ይህንንም ተከትሎ በተለያዩ የዓለም አገራት የምግብ አቅርቦት እጥረት እና የዋጋ ግሽበት አስከትሏል።
የዩክሬን ስንዴ ወደየትኞቹ አገራት ይላካል? ከፍተኛ የዩክሬን ስንዴ አስመጪዎች (በሚሊዮን ቶን)
- ግብፅ 3.62 ሚሊዮን ቶን
- ኢንዶኔዥያ 3.22 ሚሊዮን ቶን
- ባንግላዴሽ 2.3 ሚሊዮን ቶን
- ቱርክ 1.19 ሚሊዮን ቶን
- የመን 1.06 ሚሊዮን ቶን
- ፊሊፒንስ 1.02 ሚሊዮን ቶን
- ሞሮኮ 0.88 ሚሊዮን ቶን
- ቱኒዚያ 0.76 ሚሊዮን ቶን
- ሊቢያ 0.76 ሚሊዮን ቶን
- ኢትዮጵያ 0.68 ሚሊዮን ቶን
የአፍሪካ ልማት ባንክ ከዩክሬን የሚመጣው እህል መቆም በአህጉሪቱ ለ30 ሚሊዮን ቶን የምግብ እጥረት እና 40 በመቶ የምግብ ዋጋ ንረት ለመፈጠሩ አስተዋፅኦ ማድረጉን ገልጿል።
በናይጄሪያ እንደ ፓስታ እና ዳቦ ያሉ የምግብ ዓይነቶች ዋጋ 50 በመቶ ከፍ እንዲል አድርጓል።
በዓመት ከአንድ ሚሊዮን ቶን በላይ ስንዴ ከዩክሬን በምታስገባው የመን፣ የዱቄት ዋጋ 42 በመቶ፣ ዳቦ 25 በመቶ ጭማሬ አሳይቷል።
ሌላዋ ከፍተኛ የዩክሬን ስንዴ አስመጪ በሆነችው ሶሪያ የዳቦ ዋጋ በእጥፍ ጨምሯል።
ከዩክሬን በቂ ምግብ እየተላከ ነው?
ባለፈው ዓመት የነሐሴ ወር የመጀመሪያ አጋማሽ ላይ አገሪቱ 1.8 ሚሊዮን ቶን እህል በየብስ እና በባሕር ወጪ ንግድ ማድረጓን የዩክሬን መንግሥት ገልጿል።
እየተቋጨ ባለው በዚህ ዓመት የነሐሴ ወር የመጀመሪያ አጋማሽ ደግሞ 948 ሺህ ቶን እህል ብቻ ወደ ውጭ ተልኳል።
“ከዩክሬን በብዛት ምግብና ማዳበሪያ ማግኘት [ዓለም አቀፍ] የምርት ገበያውን ለማረጋጋት እና የዋጋ ቅነሳ ለማድረግ ወሳኝ ነው” ሲሉ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ በዩክሬኗ ኦዴሳ ወደብ ጉብኝት ባደረጉበት ወቅት አፅንኦት ሰጥተዋል።
የዩክሬን መንግሥት በመስከረም ወር 3 ሚሊዮን ቶን፣ በጥቅምት ደግሞ 4 ሚሊዮን ቶን እህል ወደ ውጭ መላክ እንደሚችልም ተናግሯል።
ይሁን እንጂ ይህ የሚወሰነው የመርከብ ኩበንያዎች መርከቦቻቸውን በጥቁር ባሕር መተላለፊያ (ኮሪደር) በኩል ወደ ዩክሬን ለመላክ ያላቸው ዝግጅት ጋር የተቆራኘ ነው።
ደኅንነቱ የተጠበቀ መተላለፊያ (ኮሪደር) እንዴት ነው የሚሠራው?
ሩሲያ እና ዩክሬን ከተባበሩት መንግሥታት እና ቱርክ ጋር በጥቁር ባሕር ደኅንነቱ የተጠበቀ መተላለፊያ (ኮሪደር) ለመክፈት ስምምነት ተፈራርመዋል።
የስምምነቱ ዋና ዋና ነጥቦች ምንድን ናቸው?
- ከኦዴሳ እና ሁለት አጎራባች ወደቦች ወደ ኢስታንቡል የባሕር ዳርቻ መተላለፊያ (ኮሪደር) 310 ማይል የባሕር ርዝመት (357 ማይል) እና ሦስት የባሕር ማይል ስፋት ያለው
- መሣሪያ በተጠመደባቸው የወደብ ውሃ ውስጥ የዩክሬን መርከቦች ወደ ውጭ የሚገቡ እና የሚወጡ የእህል ጭነት መርከቦችን እንዲያጅቡ
- ጭነቶች በሚንቀሳቀሱበት ወቅት ሩሲያ የተኩስ አቁም ስምምነት ለማድረግ ተስማምታለች
- የሩሲያ የጦር መሣሪያ ዝውውርን ስጋት ለማስወገድ ቱርክ መርከቦችን እንድትመረምር
- ሩሲያ በጥቁር ባሕር በኩል እህል እና ማዳበሪያ ወደ ውጭ መላክ ተፈቅዶላታል
- ስምምነቱ ከ120 ቀናት በኋላ ማለትም በኅዳር አጋማሽ ያበቃል
የጭነት መርከቦች በነዚህ የባሕር ኮሪደሮች ሲተላለፉ ዋስትና እየሰጠ ያለው ማነው?
የለንደን ሎይድስ መድን ሰጪዎች ወደ ዩክሬን ወደቦች ለሚሄዱ እና ለሚመጡ መርከቦች የመድን ሽፋን ሲሰጡ ቆይተዋል።
“የጦርነት አደጋ” ኢንሹራንስ ላይ ልምድ በማካበት የተካኑ ሲሆኑ ከዚህ ቀደምም እንደ የመን እና ሶማሊያ ባሉ ሌሎች የጦር ቀጠናዎች የጭነት መርከቦች ወደቦች እንዲደርሱ ዋስትና ሲሰጡ ቆይተዋል።
“ይህ ሰብአዊ እርዳታን የሚያካትት ስለሆነ ኢንሹራስ ሰጪዎች ክፍያቸው በተመጣጣኝ ዋጋ ነው የሚሆነው” ሲሉ የሎይድ ገበያ ማኅበር የኢንሹራንስ ኢንዱስትሪ ሠራተኛ የሆኑት ኒል ሮበርትስ ይናገራሉ።
ያለ አስተማማኝ የባሕር ኮሪደር እህል እንዴት ወደ ውጭ ሊላክ ይችላል?
ከጦርነቱ በፊት ዩክሬን ከ90 በመቶ በላይ የሚሆነውን ምግብ በባሕር ላይ ትልክ ነበር።
ወደቦቿ ሲዘጉ ዩክሬን ጭነት መኪና እና ባቡር በመጠቀም የምትችለውን ያህል በየብስ ለመላክ ሞከረች።
የአውሮፓ ኅብረት የዩክሬንን እህል በባልቲክ ባሕር ወደቦች እና እንዲሁም ከሮማኒያ የኮንስታንታ ወደብ እንዲጓጓዝ "የትብብር መንገዶችን" በማዘጋጀት ለመርዳት ሞክሯል ።
ወደ ኮንስታንታ የመጣው እህል በከፊል በዳንዩብ በጀልባ ሊጓጓዝ ይችላል።
ይሁን እንጂ በየብስ እና በባቡር አቅም እጥረት ዩክሬን በየብስ መላክ የምትችለው 10 በመቶ የሚሆነውን ነው።