ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የሰሜን ኮሪያው ኪም ጆንግ ኡን በአዲሱ የፈረንጆች ዓመት ምን አስበዋል?
ዓለም አዲሱን ዓመት ሊቀበል ተፍ ተፍ በሚልበት ወቅት ኪም ሚሳኤል ለመሞከር ተፍ ተፍ ይሉ ነበር።
አዲሱ ዓመት ሊገባ ጥቂት ሰዓታት ሲቀሩት ምዕራቡ ዓለም ደማቅ ርችቶችን ወደ ሰማይ ሲተኩስ ነበር።
ኪም ግን አዲሱ ዓመት ሊገባ ሦስት ሰዓት ሲቀሩት ጀምሮ ሚሳኤል እየሞከሩ ነበር።
በእርግጥ ያለፈው የፈረንጆች ዓመት ለሰሜን ኮሪያ ስኬታማ የሚባል ነበር።
አንደኛ ከመቼውም ጊዜ በላይ በአንድ ዓመት በርካታ ሚሳኤል ተኩሳለች፣ ሁለተኛ ኪም የሚመሯት አገር ሰሜን ኮሪያ ኒውክሊየር ታጣቂ እንደሆነች በይፋ ያረጋገጡበት ዓመት ነበር።
ይህ በመሆኑ በኮሪያ ባሕረ ገብ አካባቢ ውጥረት ነግሷል።
አሁን በአዲሱ የፈረንጆች ዓመት ታዲያ ምን ይጠበቃል? ኪም ምን አስበዋል?
የኒውክሊየር ጦር መሣሪያን ማበልጸግ
በ2022 ሰሜን ኮሪያ በጦር መሣሪያ ግንባታ ረገድ የላቀችበት ዓመት ነው ብለናል።
ዓመቱን የጀመሩት ደቡብ ኮሪያን ሊመታ የሚችል ባለ አጭር ርቀት ሚሳኤል በመሞከር ነበር።
ከዚያ ደግሞ ጃፓንን ሊመታ የሚችል ባለ መካከለኛ ርቀት ሚሳኤል ገነቡ።
በዓመቱ መጨረሻ ደግሞ በታሪካቸው ያልነበረ አህጉር አቋራጭ ተምዘግዛጊ ሚሳኤል አበለጸጉ።
ህዋሶንግ-17 የሚሉት ይህ ሚሳኤል በጽንሰ ሐሳብ ደረጃ ተምዘግዝጎ የአሜሪካን ምድር ላይ ያለ ዒላማን ማደባየት የሚችል ነው።
ባለፈው መስከረም ኪም አገራቸው ሰሜን ኮሪያ በማይቀለበስ ሁኔታ የኒውክሊየር ጦር መሣሪያ መታጠቋን ካበሰሩ በኋላ አንድ ነገር ተናግረዋል።
ያበለጸጉት መሣሪያ ከእንግዲህ ጥቃት ለመከላከል ብቻ እንደማይውል አውስተዋል።
በሌላ አነጋገር ከተከላካይነት ወደ አጥቂነት የሚያሸጋግረን ነው ብለዋል።
የፈረንጆቹ 2022 ማብቂያ ላይ የሠራተኛ ፓርቲውን ከፍተኛ አመራሮች ሰብስበው ነበር ኪም።
በአዲሱ ዓመት 2023 ምን እንሥራ ብለው መክረዋል፤ ዕቅድም አውጥተዋል።
በእቅዱ መሠረት ዋናው ግብ ተብሎ የተቀመጠው በርካታ የኒውክሊየር መሣሪያ ማምረት ነው።
እነዚህ ታክቲካል የሚባሉ አነስተኛ የኒውክሊየር መሣሪያዎቸን መገንባት የፈለጉት ኪም 'አይቀሬ' በሚሉት ከጎረቤታቸው ደቡብ ኮሪያ ጋር ለሚኖር ጦርነት ጠቃሚ ሆኖ ስለታያቸው ነው።
ታክቲካል ኒውክሊየር ከስትራቴጂክ ኒውክሊየር የሚለየው በሚያደርሰው ጥፋት አነስ ያለ እና ለመደበኛ ጦርነት የሚውል መሆኑ ነው።
ታክቲካል ኒውክሊየር መሣሪያን ለመሥራት መለስተኛ የኒውክሊየር ቦምብን መቀመም ይሻል።
እነዚህ ኒውክሊየር ቦምቦች ደግሞ በአነስተኛ ሚሳኤሎች የሚጫኑ ይሆናሉ።
የምዕራቡ ዓለም የወታደራዊ ደኅንነት ባለሙያዎች ትንፋሻቸውን ውጠው ይህን ለማየት እየጠበቁ ነው።
ሰሜን ኮሪያ በአውሮፓውያኑ 2022 ያን እንዳላሳካቸው ያውቃሉ።
ምናልባት በ2023 ይህ ቀዳሚው አጀንዳዋ ሊሆን ይችላል።
ሰላዩን ሳተላይትን መላክ
ኪም ሁለተኛው ሁነኛ ዕቅዳቸው ሰላዩን ሳተላይት መገንባት ነው።
ይህ ወደ መሕዋር የሚመጥቀው ሳተላይት ዋንኛ ተግባሩ መሬትን መሰለል ነው።
ይህን ሳተላይት መረጃ በማቀበል ረገድ ቁልፍ እና አስፈላጊ ሆኖ አግኝታዋለች ሰሜን ኮሪያ።
ሰሜን ኮሪያ አዲሱን ዓመትም እንዳለፉት ዓመታት ሁሉ ጦር መሣሪያ በመገንባት ታሳልፋለች ተብሎ ይጠበቃል።
ያሏትን ታዘምናለች፣ የሌሏትን ትፈጥራለች።
የተባበሩት መንግሥታት ይህን እንዳታደርግ ማዕቀብ ቢጥልም ኪም የተባበሩት መንግሥታት ጨርሶውኑ መኖሩን የረሱት ነው የሚመስሉት።
ከሰሜን ኮሪያ ጋር ንግግር ይኖራል?
ለመጨረሻ ጊዜ ከኪም ጋር ጥሩ መግባባት ላይ ደርሰው ነበር የሚባሉት የምዕራቡ መሪ ትራምፕ ነበሩ።
ነገሮች ግን እንደ አጀማመራቸው አልዘለቁም።
ኪም በአዲሱ ዓመት ከአሜሪካ ጋር ለመነጋገር ዕቅድ የላቸውም።
ቀጠናውን ከኒውክሊየር ስጋት ነጻ የማድረጉ ድርድር በ2019 ተጀምሮ በዚያው ዓመት ከከሰመ በኋላ የረባ ጥረት አልተደረገም።
ተንታኞች ኪም እየጠበቁ ያሉት ተደራዳሪነታቸው ላይ አቅም የሚፈጥር መሣሪያን አሳክተው እስኪጨርሱ ነው።
ኪም አገራቸው በጎረቤት አገራት እና በአሜሪካ ላይ ወሳኝ ጥቃት ማድረስ የሚችሉ አስተማማኝ ጦር መሣሪያዎቸን እንደገነቡ ሙሉ በሙሉ እርግጠኛ ሲሆኑ ወደ ንግግር ጠረጴዛ ሊመለሱ ይችላሉ።
ባለፈው ዓመት ሰሜን ኮሪያ ወደ ሩሲያ እና ቻይና በይበልጥ የተጠጋችበት ዓመት ነበር።
ኪም ሕልማቸው ሰምሮ ከባባድ የጦር መሣሪያ ግንባታቸውን በስኬት አጠናቀው ወደ ሩሲያ ካጋደሉ ምናልባት የዓለም ፖለቲካ አሰላለፍን እስከመጨረሻው ሊቀይር የሚችል ነገር ሊከሰት እንደሚችል ተንታኞች ይናገራሉ።
ለሰሜን ኮሪያ ፊት የማይሰጡት የደቡብ ኮሪያ መሪ
በቀጠናው ይበልጥ ውጥረት እንዲነግስ ያደረገው የኪም የሚሳኤል ሙከራዎች ብቻ አይደሉም።
በደቡብ ኮሪያ ብቅ ያሉት አዲሱ ፕሬዝዳንት እና የአመራር ዘይቤያቸው እንጂ።
እኒህ ፕሬዝዳንት ለጎረቤት ሰሜን ፊት መስጠት አያስፈልግም ብለው ያምናሉ።
ፕሬዝዳንት ዩን ሱክ የዎል የሚያምኑት ሰሜን ኮሪያ ስታመር አብሮ ማምረር ነው የሚያዋጣው ብለው ነው።
ስለዚህ ሰሜን ኮሪያ የተሳካም ያልተሳካም ሙከራ ቢያደርጉ ደቡብ ኮሪያ ተመጣጣኝ ምላሽ መስጠት አለባት ብለዋል።
ለዚህም ነው በተከታታይ ከአሜሪካ ጋር ጥምር የጦር ልምምድ እያደረጉ ኪምን ይበልጥ ለብስጭት እየዳረጉ ያሉት።
ባለፈው ሳምንት ነገሮች የከረሩት በዚህ የተነሳ ነበር፥
ሰሜን ኮሪያ ባልተጠበቀ ሁኔታ አምስት ሰው አልባ አውሮፕላኖችን ወደ ደቡብ ኮሪያ የአየር ክልል ላከች። ደቡብ ኮሪያ መትታ ልትጥላቸው አልቻለችም። ይህ ደግሞ የደቡብ ኮሪያን የዝግጅት ክፍተትን አሳበቀ።
ፕሬዝዳንቱ ይህ እንዳይደገም አስጠነቀቁ። ከዚህ በኋላ ለሰሜን ኮሪያ ትንኮሳ ተመጣጣኙን ሳንሰጥ እንቅልፍ አይወስደንም ብለው ቃል ገቡ።
ይህ ነገር የምር ከሆነ በ2023 ሰሜን ኮሪያ እና ደቡብ ኮሪያ ከባድ ፍጥጫ ውስጥ ሊገቡ እንደሚችሉ ተፈርቷል።
ሰሜን ኮሪያ ድንበሯን ትከፍታለች?
የመጨረሻው ጥያቄ ሰሜን ኮሪያ በሯን ለውጭው ዓለም ትከፍታለች ወይ የሚለው ነው?
በሰሜን ኮሪያ የምግብ እጥረት አለ።
ይህን ለመጀመሪያ ጊዜ ኪም ራሳቸው ያመኑት ጉዳይ ነው።
ዜጎች ተጨምድደው በፍርሃት ቆፈን ነው የሚኖሩት።
የኮቪድ ተህዋሲ ደጃችንን አልረገጠም ሲሉ የነበሩት ኪም ኋላ ላይ ደግሞ ጨርሰን ደምስሰነዋል ብለው ነበር።
ቢሆንም የሰሜን ኮሪያ ድንበር ዝግ ነው። ተህዋሲው ገብቶ ነገር እንዳያበላሽ ከፍተኛ ጥንቃቄ ይደረጋል።
ይህ ሁኔታ ግን እስከ መቼ ሊቀጥል ይችላል ሲሉ ይጠይቃሉ የፖለቲካ አዋቂዎች።
ድንበር ካልተከፈተ የሰሜን ኮሪያ ምጣኔ ሃብት ሊንኮታኮት ይችላል።ሁነኛ የንግድ አጋሯ ቻይና ደግሞ በድጋሚ በተህዋሲው እየታመሰች ነው።
ለሰሜን ኮሪያ አዲሱ ዓመት ፈተና የሚሆንባትም ለዚሁ ነው።
ሌላው ጥያቄ ኪም አንድ ነገር ቢደርስባቸው አገሪቱን ማን ይረከባል የሚለው ጥያቄ ነው።
በኅዳር ወር ኪም ለመጀመሪያ ጊዜ ከሴት ልጃቸው ጋር መታየታቸውን ተከትሎ አገሬው ጉድ ሲል ነበር።
ይህ ፍጹም ያልተለመደ የሰሜን ኮሪያ መሪ ተግባር ሰሞኑን ለሁለተኛ ጊዜ ተደግሟል።
ምናልባት ኪም ያቺን አገራቸውን በሞት ጥለው ቢሰናበቱ ተተኪዋ ይቺ ልጅ ሳትሆን አትቀርም እየተባለ ነው።
2023 እና ሰሜን ኮሪያ እንዴት ይሆኑ ይሆን?