ዩክሬን በፈጸመችው የሚሳኤል ጥቃት በመቶዎች የሚቆጠሩ የሩሲያ ወታደሮችን ገደልኩ አለች

ዩክሬን በሩሲያ ወረራ ሥር ባለው ዶኔስክ ግዛት ላይ በፈጸመችው የሚሳኤል ጥቃት 400 የሚደርሱ ሩሲያውያን ወታደሮችን እንደገደለች አሳወቀች።

ሚሳኤሉ ዒላማ ያደረገው ማኪቭካ በተባለው ከተማ፣ የሩሲያ ወታደሮች ይገኙበታል የተባለ ሕንጻን ነው።

ዩክሬን በጥቃቱ ገደልኩ ብላ የገለጸችው ሩሲያ ወታደሮች ቁጥር በገለልተኛ ወገን አልተረጋገጠም። ሩሲያን የሚደግፉ የአከባቢው ባለሥልጣናት በጥቃቱ ጉዳት መድረሱን ቢገልጹም፣ ሪፖርት የተደረገውን ቁጥር ግን አላረጋገጡም።

የሩሲያ የሰው አልባ አውሮፕላን (ድሮን) ጥቃት የቀጠለ ሲሆን፣ ትላንት እሑድ ምሽትም የአየር ድብደባ ማስጠንቀቂያ ድምጽ በኪዬቭ ሲሰማ ነበር።

በሩሲያ የሚደገፉ የዶኔስክ ከፍተኛ ባለሥልጠን የሆኑት ዳኒል ቤዝሶኖቭ እንዳሉት፣ የአውሮፓውያኑ አዲስ ዓመት ከገባበት እኩለ ሌሊት ሁለት ደቂቃ በኋላ ሚሳኤሉ ማኪቭታን መቷል።

“ከአሜሪካው ኤምኤልአርኤስ ሂማርስ [ሚሳኤል] በከፍተኛ ሁኔታ ሲወነጨፍ ነበር። የሞቱም፣ የቆሰሉም አሉ። የጉዳቱ ትክክለኛ ቁጥሩ አልታወቀም” ብለዋል።

ሩሲያውያን አስተያየት ሰጪዎች እና ጦማሪዎች ጥቃቱ መፈጸሙን ቢገልጹም፣ የተጎጂዎች ቁጥር ከተባለው ያነሰ እንደሆነ ጠቁመዋል።

ሩሲያዊው የቴሌቭዥን አቅራቢ ቭላድሚር ሶሎቭዮቭ በቴሌግራም የማኅበራዊ ትስስር መድረክ ላይ “ያጣናቸው ብዙ አሉ። 400 ግን አይደርሱም” ብሏል።

የዩክሬን ወታደራዊ ኃይል በበኩሉ ከሞቱት 400 ሩሲያውን በተጨማሪ 300 መቁሰላቸውን ገልጿል።

በዶኔስክ ግዛት ውስጥ በሩሲያ የተሾመው አስተዳደር እንዳለው በአውሮፓውያኑ አዲስ ዓመት ዋዜማ 25 ሮኬት ወደ ማኪቫካ ተተኩሷል።

ማኪቫካ ላይ ጥቃት በደረሰ በሰዓታት ውስጥ ወደ ኪዬቭ ሲተኮስ ነበር። የድሮን እና የሚሳኤል ጥቃቱ የዩክሬን መዲና መሠረተ ልማት ላይ ያነጣጠረ እንደነበር አገረ ገዢው ኦሌክሲ ኩሌባ ተናግረዋል።

ከመዲናዋ አንድ ሰው በተበላሸ የሩሲያ ድሮን ሳቢያ እንደተጎዳም አክለዋል።

የዩክሬን ፕሬዝዳንት በአዲሱ የአውሮፓውያን 2023 ለአገራቸው “ድል እና ወደ መደበኛው ሕይወት መመለስን” ተመኝተው ብዙም ሳይቆይ ነው ጥቃቱ የደረሰው።

የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ለአውሮፓውያኑ አዲስ ዓመት ባስተላለፉት መልዕክት፣ የአገራቸው ሉዓላዊነት እና ነጻነት ለማስከበር እንደሚታገሉ ተናግረዋል።

ጥቃቱ ከመድረሱ በፊት የኪዬቭ ወታደራዊ ኃይል በቴሌግራም ማስጠንቀቂያ አስተላልፏል።

የከተማው ወታደራዊ መሪ ሲርሂ ፖፕኮ፣ ነዋሪዎች ለደኅንነት አስተማማኝ በሆኑ ጥብቅ ቦታዎች እንዲቆዩ አስጠንቅቀዋል።

አገረ ገዢው እንደተናገሩት ደግሞ ጥቃት ያደረሱት ድሮኖች ኢራን ሠራሽ ናቸው።

ሩሲያ የዩክሬንን የኃይል መሠረተ ልማት አነጣጥራ ጥቃት ስትሰነዝር ወራት ተቆጥረዋል። ሕዝቡ በጨለማ እና በቅዝቃዜ ለመኖርም ተገዷል።