ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የመዝናኛ ከተማዋ ዱባይ በአልኮል ላይ ጥላ የነበረውን ግብር እና ቁጥጥር አነሳች
ዱባይ የቱሪዝም ገበያዋን ከፍ ለማድረግ የአልኮል መጠጥ ላይ ጥላ የነበረውን የ30 በመቶ ግብር አነሳች።
በተጨማሪም ከዚህ ቀደም ሲተገበር የነበረውን አልኮም መጠቀም የሚፈልግ ሰው መያዝ የነበረበትን ‘የግል የአልኮል ፍቃድ’ ሰርዛለች።
በዱባይ አልኮል መጠቀም የሚችለው ሙስሊም ያልሆነ እና ከ21 ዓመት በላይ የሆነ ሰው ከፖሊስ የሚሰጥ ከፕላስቲክ ካርድ የተሰራ ‘የግል አልኮል ፍቃድ’ የያዘ ብቻ ነበር።
መጠጥ ቤቶች እና የምሽት መዝናኛ ስፍራዎችን ይህን የፍቃድ ካርድ ብዙ ጊዜ ባይጠይቁም፣ ይህን ፍቃድ ሳይዝ አልኮል ሲጠጣ የተገኘ ሰው ግን ቅጣት ይጠብቀዋል።
ዱባይ ከአልኮል ሽያጭ እና አጠቃቀም ጋር በተያያዘ የነበራትን ጥብቅ ሕግ ስታላላ ቆይታለች።
የዩናይትድ አረብ ኤሚሬትስ የንግድ ከተማዋ ዱባይ፤ በረመዳን ወቅት አልኮል በቀን እንዲሸጥ ከመፈቀዷም በላይ፣ በኮቪድ-19 የእንቅስቃሴ ገደብ ወቅት ሰዎች በቤታቸው ሆነው የአልኮም መጠጥ እንዲመጣላቸው ማዘዝ እንዲችሉ ፈቅዳ ነበር።
ዱባይ በአልኮል ላይ ጥላ የነበረውን ግብር ያነሳቸው የውጭ አገራት ጎብኚዎችን በመሳብ ከጎረቤት ከተሞች የገጠማትን ፉክክር ለመቋቋም ነው ተብሎ ተገምቷል።
በዱባይ የአልኮም መጠጦችን የሚያከፋፈሉት ሁለቱ ኩባንያዎች፤ ማሪታይም ኤንድ ሜርካንታይል ኢንተርናሽናል (ኤምኤምአይ) እና አፍሪካ ኤንድ ኢስተርን የተባሉት ድርክቶች የግብር ለውጡ በዋጋችን ላይ ለውጥ ያመጣል ብለዋል።
“ሥራችንን በዱባይ ውስጥ ከጀመርን ከ100 ዓመታት ወዲህ፤ ኤሚሬቶች ውሳኔ ጥንቃቄ የተሞላበት እና ሁሉንም ያካተት ነው” ሲሉ የኤምኤምአይ ቃል አቀባይ ታይሮን ሪይድ ለአሶሺዬትድ ፕሬስ ተናግረዋል።
አልኮል አቅራቢ ኩባንያዎች ግብር መነሳቱ በዱባይ እና በተቀረው የተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች አልኮል ኃላፊነት በተሞላበት መንገድ እንዲገዛ እና ጥቅም ላይ እንዲውል የሚያበረታታ ነው ብለዋል።
አኮል ላይ ተጥሎ የነበረው ግብር ከትናንት እሁድ ጀምሮ ተግባራዊ ይደረግ እንጂ ውሳኔው ቋሚ ስለመሆኑ ግልጽ አይደለም።
ፋይናንሻል ታይምስ ግብሩ የተነሳው ለአንድ ዓመት የሙከራ ጊዜ ነው ሲል ዘግቧል።
በዱባይ ካሉት ነዋሪዎች 90 በመቶ ያክሉ የውጭ አገራት ዜጎች ሲሆኑ አልኮል ለመግዛት ኡማ አል ቁዋይን ወደተባለች ከተማ መጓዝ ግድ ይላቸው ነበር።
ዱባይ በአካባቢው ካሉ የአረብ ከተሞች በተለየ ጥብቅ ሕግ ስለሌላት በበርካታ የውጭ አገራት ዜጎች ተመራጭ ከተማ ሆና ቆይታለች።