ዩክሬን ከአሜሪካ እና ከሩሲያ ጋር እንደምትነጋገር ዜለንስኪ አስታወቁ

ፕሬዝዳንት ቮሎዲሚር ዜለንስኪ የዩክሬንን ጦርነት ለማስቆም ከሩሲያ እና ከአሜሪካ ጋር የሚደረጉት የሦስትዮሽ ውይይቶች በተባበሩት አረብ ኤምሬቶች እንደሚከናወኑ አስታወቁ። ይህንን የገለጹት ከፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ጋር በዳቮስ ከተነጋገሩ በኋላ ነው።

የዲፕሎማሲው ፍጥነት እየጨመረ ባለበት ወቅት ትራምፕ ከዘሌንስኪ ጋር ያደረጉት ስብሰባ ጥሩ እንደነበር ተናግረዋል። የአሜሪካው ልዑክ ስቲቭ ዊትኮፍ በበኩላቸው ከሩሲያው ቭላድሚር ፑቲን ጋር ለመነጋገር ወደ ሞስኮ አምርተዋል።

ከትራምፕ ልጅ ባለቤት ጃሬድ ኩሽነር ጋር ወደ ሞስኮ የሚጓዙት ዊትኮፍ በስምምነቱ ዙሪያ ተስፋ እንዳላቸው ተናግረዋል።

"ወደ አንድ ጉዳይ የመጣን ሲሆን በጉዳዩ ላይ በተደጋጋሚ ተወያይተናል። ይህም ማለት ሊፈታ የሚችል ነገር ነው" ሲሉ ከስዊዘርላንድ ከመነሳታቸው በፊት ገልጸዋል።

የትራምፕ መልዕክተኛ ስለቀረው ጉዳይ ምንም ዝርዝር ነገር ባይሰጡም፣ ዜለንስኪ ግን የምሥራቅ ዩክሬን የወደፊት ዕጣ ፈንታ ያልተፈታው ጉዳይ መሆኑን ግልጽ አድርገዋል።

በኤምሬትስ የታቀደው ውይይት ሩሲያን እንዲሁም አሜሪካን እና ዩክሬንን እንደሚያካትት አስታውቀዋል። "ዩክሬን ብቻ ሳትሆን ሩሲያም ልትተው የሚገባ ነገር እንዳለ በማወቅ ዝግጁ መሆን አለባት" ብለዋል።

"ዋነኛው ጉዳይ መሬት ነው። ይህ ነው እስካሁን ያልተፈታው ጉዳይ" ሲሉ ዜለንስኪ በዳቮስ፣ ስዊዘርላንድ በዓለም ኢኮኖሚ ፎረም ላይ ለታደሙ ጋዜጠኞች ተናግረዋል።

ለዩክሬን የኢንደስትሪ ማዕከል ለሆነው ዶንባስ የቀረበው የአሜሪካ ሐሳብ አካባቢው ከወታደራዊ ቀጠና ነፃ እና ነፃ የኢኮኖሚ ዞን እንዲሆን በማድረግ ለኪየቭ የደኅንነት ዋስትናዎችን መስጠትን ነው።

"ሁለቱም ወገኖች ይህንን ለመፍታት ከፈለጉ መፍትሄ እናገኝለታለን" ያሉት ዊትኮፍ ከሞስኮ በኋላ ወደ አቡ ዳቢ እንደሚያመሩ አስረድተዋል።

ዜለንስኪ ለጋዜጠኞች እንደተናገሩት ከአሜሪካ የሚቀርበውን የደኅንነት ዋስትና በተመለከተ ከትራምፕ ጋር ስምምነት ላይ ደርሰዋል። ምንም ዝርዝር ነገር ባይሰጡም ከመፈረማቸው በፊት ወደ አሜሪካ ኮንግረስ እና የዩክሬን ፓርላማ መቅረብ እንደሚያስፈልገው ተናግረዋል።

ምንም እንኳን በእንግሊዝ እና በፈረንሳይ የሚመራው "የፈቃደኞች ጥምረት" ስምምነቱን ለመከታተል መሬት ላይ ኃይሎችን እንደሚያሰማራ ቢናገሩም፣ "ያለ አሜሪካ ምንም የደኅንነት ዋስትና አይሠራም" ሲሉ የትራምፕን ድጋፍ አስፈላጊ እንደሚሆን አጥብቀው ገልጸዋል።

ቀደም ሲል በዳቮስ ንግግራቸው ወቅት የአውሮፓ አጋሮቻቸው በሩሲያ ላይ እርምጃ ለመውሰድ "የፖለቲካ ፍላጎት" እጦት አሳይተዋል በማለት ተችተዋል።

"አውሮፓ አንድ እንዳትሆን እና እውነተኛ መፍትሄዎችን ለማግኘት እንዳትናገር የሚያግዷት ማለቂያ የሌላቸው ውስጣዊ ክርክሮች እና ያልተነገሩ ነገሮች አሉ" ሲሉ ከትራምፕ አሜሪካ ጋር ያለውን በንፅፅር አሳይተዋል።

"ፕሬዝዳንት ትራምፕ ማንነታቸውን ይወዳሉ። አውሮፓን እንደሚወዱ ይናገራሉ፣ ነገር ግን አውሮፓን አያዳምጡም" ብለዋል።

የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ወደ ዳቮስ ለማቅናት በሌሊት መጓዛቸው ተነግሯል።

መጀመሪያ ላይ ሩሲያ በኪየቭ ላይ በሰነዘረችውን ጥቃት ምክንያት የኃይል መሠረተ ልማት በመቋረጡ የዋና ከተማዋን በርካታ አካባቢዎች ማሞቂያ፣ ውሃ ወይም ኃይል እንዳያገኙ ሆነዋል። በዚህም ነዋሪዎች በአራት ዓመታት ውስጥ በጣም አስቸጋሪ ክረምት እንዲያሳልፉ በመገደዳቸው ፕሬዝዳንቱ ጉዟቸውን ለመሰረዝ ተገደው ነበር። በሺዎች የሚቆጠሩ የመኖሪያ ሕንጻዎች ማሞቂያ የላቸውም።

ዜለንስኪ ባለፈው ወር ጦርነቱን ለማቆም የተዘጋጀው ባለ20 ነጥቡ የአሜሪካ ዕቅድ 90 በመቶ ዝግጁ መሆኑን እና ዩክሬን በምሥራቅ ዩክሬን፣ ዶንባስ ላይ ያላት አቋም ከሩሲያ የተለየ መሆኑን ተናግረዋል።

በአሜሪካው ባለ 20 ነጥብ ዕቅድ መሠረት ዜለንስኪ በዶንባስ የኢኮኖሚ ዞን ለመፍጠር ዩክሬን አሁንም ከምትቆጣጠረው የዶኔትስክ ክልል 25 በመቶ ወታደሮችን እስከ 40 ኪሎሜትር ለማስውጣት ሐሳብ ቀርቧል። ሩሲያምተመሳሳይ እርምጃ ትወስዳለች ይላል።

የክሬምሊን ቃል አቀባይ ዲሚትሪ ፔስኮቭ ሐሙስ ዕለት ከአሜሪካ ልዑካን ጋር የሚያደርጉት ውይይት "በዩክሬን እና በሌሎች ተዛማጅ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ" እንደሚቀጥል ቢገልጹም የዊትኮፍን ተስፋ ስለመጋራታቸው ለመናገር ፈቃደኛ አልሆኑም።

ፑቲን መላውን ክልል ለመቆጣጠር እንደሚፈልጉ የሚታወቅ ሲሆን የሩሲያ ኃይሎችም ባለፈው ዓመት በምሥራቅ አቅጣጫ ይዞታቸውን በዝግታ እያስፉ ነው።