ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ትራምፕ፤ ካናዳ 'የሰላም ቦርድን' እንድትቀላቀል አቅርበው የነበረውን ጥሪ ሰረዙ
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ያቋቋሙትን 'የሰላም ቦርድ' ካናዳ እንድትቀላቀል አቅርበውት የነበረውን ጥሪ ሰረዙ።
በሁለቱ አገራት መካከል ያለው ግንኙነት መሻከሩን ተከትሎ ትራምፕ "ካናዳ ቦርዱን እንድትቀላቀል ቀርቦ የነበረው ጥሪ መሰረዙን በዚህ ደብዳቤ እናሳውቃለን" ሲሉ ለጠቅላይ ሚኒስትር ማርክ ካርኒ መልዕክት ልከዋል።
የካናዳው ጠቅላይ ሚኒስትር አሜሪካ በዓለም አቀፍ አሰላለፍ ያላት ሚና "እንደሚቀለበስ" ከሰሞኑ ተናግረዋል።
ካናዳ የትራምፕን 'የሰላም ቦርድ' ለመቀላቀል ገንዘብ እንደማትከፍል አስታውቃለች።
ቋሚ የቦርዱ አባል ለመሆን 1 ቢሊዮን ዶላር መክፈል ያስፈልጋል መባሉን ካናዳ አልተቀበለችም።
ከሦስት ዓመት በላይ ለሚዘልቅ ጊዜ የጋዛ ሰላም ቦርድ ቋሚ አባል መሆን የሚፈልጉ አካላት 1 ቢሊዮን ዶላር መክፈል አለባቸው።
የካናዳው ጠቅላይ ሚኒስትር የቀረበላቸውን ጥሪ መጀመሪያ ላይ ቢቀበሉም የቦርዱ አባል ለመሆን ገንዘብ እንደማይከፍሉ ገልጸዋል።
ትራምፕ ለካናዳ የተላከውን ጥሪ ለምን እንደሰረዙ በግልጽ አልተናገሩም።
ስለ ሰላም ቦርዱ በሚገልጽ ደብዳቤ ላይ ትራምፕ "ቦርዱ ከጋዛ ባሻገር ዓለም አቀፍ ግጭትን ለመፍታት አዲስ ስልት ይቀይሳል" ብለዋል።
ይህም የተባበሩት መንግሥታትን ሥልጣን እንደሚገዳደር ተሰግቷል። የተቋሙ የፀጥታዊ ምክር ቤት በዓለም አቀፍ መድረክ ሰላም የማስጠበቅ ኃላፊነት ተሰጥቶታል።
የቦርዱ የዕድሜ ዘመን መሪ ትራምፕ ይሆናሉ። ከፕሬዝዳንትነት ቢለቁም ቦርዱን መምራት ይቀጥላሉ።
ቦርዱ በሐማስ እና እስራኤል መካከል ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን እና ጋዛን መልሶ ለመገንባት ቢቋቋምም ሚናው ከዚያም እንደሚሻገር ተጠቁሟል።
ወደ 60 አገራት ቦርዱን እንዲቀላቀሉ ተጠይቀዋል።
አርጀንቲና፣ ፓኪስታን፣ ኮሶቮ፣ ግብፅ፣ ቱርክ፣ ዮርዳኖስ፣ ኢንዶኔዥያ፣ ኳታር፣ የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች፣ ባሕሬን፣ አልቤንያ፣ አርሜንያ፣ አዘርባጃን፣ ቤላሩስ፣ ሃንጋሪ፣ ካዛኪስታን፣ ሞሮኮ እና ቬትናም ቦርዱን ተቀላቅለዋል።
ሆኖም ግን የተባበሩት መንግሥታት ቋሚ የፀጥታዊ ምክር ቤት አባላት የሆኑት ቻይና፣ ፈረንሳይ፣ ሩሲያ እና ዩናይትድ ኪንግደም ቦርዱን እንደሚቀላቀሉ አልተገለጸም።
የዓለም ምጣኔ ሃብት ጉባዔ በዳቮስ ሲካሄድ የካናዳው ጠቅላይ ሚኒስትር ትራምፕን የሚተች ንግግር ካደረጉ በኋላ ታዳሚዎች በጭብጨፋ ድጋፍ ሰጥተዋቸዋል።
"መካለኛ አቅም" ያላቸው አገራት ተባብረው "የኃያላን አገራትን" የምጣኔ ሃብት ጫና መቋቋም አለባቸው ሲሉ ተናግረዋል። በንግግራቸው አሜሪካን በቀጥታ አልጠቀሱም።
ትራምፕ በነጋታው በስዊዝ አልፓይን መዝናኛ "ካናዳ የምትኖረው በአሜሪካ ምክንያት ነው። ማርክ በቀጣይ ንግግር ስታደርግ ይሄንን አስታውስ" ብለው ተናግረዋል።
በቀጣዩ ቀን የካናዳው ጠቅላይ ሚኒስትር በሰጡት ምላሽ "ካናዳ የምትኖረው በአሜሪካ ምክንያት አይደለም። ካናዳ የበለጸገችው በካናዳውያን አማካኝነት ነው" ብለዋል።