ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ለሴቶች የሥነ ተዋልዶ ጤና ጠቃሚ የሆነው በብልት ውስጥ የሚገኘው ባክቴሪያ
በሴቶች ብልት ውስጥ የሚገኘው ባክቴሪያ ብዙም ትኩረት አልተሰጠውም። በተለይ ከአንጀት ባክቴሪያ አንጻር እምብዛም አልተነገረለትም።
በሴቶች ብልት ውስጥ በሺዎች የሚቆጠሩ ባክቴሪያዎች፣ ፈንጋይ እና ቫይረሶች ይኖራሉ። ለጠቃሚ ንጥረ ነገር ይፎካከራሉ።
በብልት ውስጥ የሚኖሩት እነዚህ ነፍሳት ለጤና ጠቀሜታ አላቸው። በሽታን በመከላከል እና የተሻለ እርግዝናን በመፍጠርም ይታወቃሉ።
ሆኖም ግን ላክቶባሲለስ (Lactobacillus) የተባለው ባክቴሪያ መጠን ከፍተኛ ሲሆን፣ ሴቶች እንዳይወልዱ ወይም እንዲያስወርዳቸው ያደርጋል። ሕጻናት ያለ ጊዜያቸው እንዲወለዱ ከማድረጉም ባሻገር ለማሕጸን ካንሰርም ያጋልጣል።
በብልት ውስጥ ያሉ ጠቃሚ የባክቴሪያ ዓይነቶችን ለማመጣጠን ሳይንቲስቶች እየተመራመሩ ነው። ይህም የሥነ ተዋልዶ ጤና የሚቀይር ይሆናል።
በልጅነት ያለው የብልት ባክቴርያ (vaginal microbiome) አነስተኛ ኦክስጂን ባለበት ሁኔታ በሕይወት መቀጠል የሚችል ነው። የኦኤስትሮጂን መጠን ከፍ ሲል ማለትም በአዋቂ ሴቶች ብልት ውስጥ የሚገኘው ባክቴሪያ የተሻለ ሁኔታ በመፍጠር ሌሎች ባክቴሪያዎችን ያስጠጋል።
የባክቴሪያዎች ስብስብ (Lactobacillus) በብልት ውስጥ ይኖራል። ለጤና ጠቃሚ እንደሆነ ባለሙያዎች ይናገራሉ።
እነዚህ ባክቴሪያዎች ሴቶችን ከኢንፌክሽን የመከላከል እና ሰውነትን የሚጎዱ ነፍሳትን የማገድ ጠቀሜታ አላቸው።
የዩናይትድ ኪንግደም የመድኃኒት እና ጤና ቁጥጥር ኃላፊ ቼርሲ ሰርኪ "ጎጂ ነፍሳት ያግዳሉ። ጎጂ ማይክሮብ እንዳይኖር ይከላከላሉ። የሰውነትን በሽታ የመከላከል አቅም ስለሚያጠናክሩ ከኢንፌክሽን ይከላከላሉ። ወደ ሰውነት ለመግባት የሚሞክር ባክቴሪያን ይገድላሉ" ይላሉ።
የብልት ባክቴሪያ ከተስፋፋ እና ከጠፋ ወይም ሚዛኑን ከሳተ ባክቴሪያል ቫጃይኖሲስ (bacterial vaginosis) ወይም የሽንት ትቦ ኢንፌክሽን የመፈጠር ዕድላቸው ይሰፋል።
ሴቶች በግብረ ሥጋ ለሚተላለፉ በሽታዎች የመጋለጥ ዕድላቸው ይጨምራል። አነስተኛ የባክቴሪያ መጠን ያላቸው ሴቶች ለኤችአይቪም በቀላሉ ይጋለጣሉ።
የሴቶች ጤና መምህርት ላውራ ጉድፌሎ እንደሚሉት፤ በደቡብ አፍሪካ ያለው የኤችአይቪ ተጋላጭነት ከ20 አስከ 30 በመቶ ደርሷል። በተለይም በወሲብ ንግድ በሚተዳደሩ ሴቶች ዘንድ በሽታው በስፋት እየተሠራጭ ነው።
ለዚህ ምክንያን ከሆኑ መካከል የብልት ባክቴሪያን ባለሙያዋ ይጠቅሳሉ።
"የብልት ማይክሮባክቴሪያ አነስተኛ መጠን ሲኖረው በኤችአይቪ የመያዝ ዕድል ከፍ ይላል" በማለት ያስረዳሉ።
የሂውማን ፓፒሎማ ቫይረስ (human papilloma virus) ተጋላጭነት እንዲሁም በማሕጸን ካንሰርን እና በማሕጸን ጫፍ ካንሰር ሊያዙ ይችላሉ።
የባክቴሪያ መጠን ማነስ ሴቶች በኤችፒቪ ከተያዙ በኋላ በፍጥነት እንዳያገግሙ ከማድረጉ ባሻገር ኢንፌክሽኑ ወደ ማሕጸን ካንሰር እንዲያድግ ምክንያት ይሆናል።
"ማይክሮባዮም እንደ ደን ነው። ጤናማ ደን ውስጥ ጤናማ አበባ ይበቅላል። መዋቅሩ ትክክል ካልሆነ ግን ጤናማው ሥርዓት ይዛባል" ይላሉ ባለሙያዋ።
ስለ ሴቶች የእርግዝና ሁኔታ እንዲሁም ለምን ያህል ጊዜ ልጆች በማሕጸናቸው እንደሚቆዩ ለማወቅም ይኸው ባክቴርያ ይረዳል።
አነስተኛ የባክቴሪያ መጠን ያላቸው ሴቶች በብዛት ለውርጃ ወይም ከማሕጸን ውጪ ለሚፈጠር እርግዝና (ectopic pregnancy) ይጋለጣሉ።
ሕጻናት ያለጊዜው (በ37 ሳምንታት ውስጥ) እንዲወለዱም ያደርጋል።
"ዳይባዮሲስ ያለባቸው ሴቶች በትክክለኛው ጊዜ ሊወልዱ ቢችሉም ሕጻናት ቀድመው የሚወለዱበት አጋጣሚም አለ" ይላሉ ባለሙያዋ።
ሕጻናት ቀድመው እንዳይወለዱ በማድረግ ጠቃሚ የሆነው ባክቴርያ 'Bifidobacterium' ይባል። አምስት በመቶ ያህል ሴቶች ሰውነት ውስጥ ይገኛል።
የወሊድ ሕክምና የሚሰጣቸው ሴቶች በባክቴሪያ መጠን ማነስ ምክንያት ሕክምናቸው ስኬታማ ላይሆን ይችላል።
በእርግዝና ወቅት ለሚፈጠር ኢንፌክሽን እና የሰውነት በሽታ የመከላከል አቅም መዳከም ምክንያትም ነው።
የልብ ሕመም፣ የስኳር በሽታ፣ ከልክ ያለፈ ውፍረት፣ አልዛይመርስ፣ ውርጃ እና ያለ ጊዜ የሚወለዱ ልጆች መነሻ ከሆኑ ምክንያቶች አንዱ ይኸው የባክቴሪያ መጠን አለመመጣጠን ነው።
በብልት ውስጥ ያለው የፈሳሽ መጠን አነስተኛ እንዲሆን በማድረግ ጉዳት እንደሚያስከትል ባለሙያዋ ይናገራሉ።
ይሄ የባክቴሪያ ዓይነት አንጀት ውስጥም ይገኛል።
የሰውነት መመረዝ (inflammation) ከፍተኛ እንዳይሆን በማድረግ ስለሚያግዙ "በጎ ባክቴሪያ" ተብለው ይጠራሉ።
እንደ ክለሜድያ፣ ጨብጥ እና ቂጥኝ ያሉ በግብረ ሥጋ ግንኙነት የሚተላለፉ በሽታዎችን ለመከላከል ባክቴሪያዎች ያስፈልጋሉ።
"ጥሩ ማይክሮባዩም በሰውነት ውስጥ ሲኖር ባክቴሪያን ቫጃይኖሲስን ይከላከላል። ልጆች ያለ ጊዜያቸው እንዳይወለዱም ያግዛል" ይላሉ ባለሙያዋ።
የብልት ባክቴሪያ ላይ የሚሠራው ጥናት የሥነ ተዋልዶ ጤና እንደሚለውጥ ይታመናል።
በኢምፔርያን ኮሌጅ ለንደን እየተሠራ ያለው ምርምር ላክቲቭ ቪ (Lactin-V) የተባለ ፕሮባዮቲክ በመስጠት የላክቶባክሲለስ ባክቴሪያ መጠንን ለመጨመር ይረዳል።
ያለ ጊዜያቸው የሚወለዱ ልጆችን ቁጥር ለመቀነስ ይረዳል ተብሏል።
የነፍሰ ጡር ሴቶች የደም ዓይነት እና ያለ ጊዜያቸው ልጆችን የመውለድ ዕድላቸው ትስስር እንዳላቸው የጥናት ቡድኑ ደርሶበታል።
ቢ እና ኦ የደም ዓይነቶች ያሏቸው ሴቶች ያለ ጊዜያቸው ልጆችን የመውለድ ዕድላቸው ከፍተኛ ነው።
የደም ዓይነታቸው ኤ የሆነ ሴቶች በአንጻሩ ጠቃሚ የሆነው ባክቴርያ (Lactobacillus crispatus) በሰውነታቸው ይገኛል።
የሴቶችን የብልት ባክቴሪያ ዓይነት በማጥናት የወደፊት የጤና ሁኔታቸውን እንዲሁም ምን ዓይነት እርግዝና እንደሚገጥማቸው ግምት ለማስቀመጥ ጥናቱ ሙከራ እንደሚያደርግ ባለሙያዋ ቼርሲ ሰርኪ ያስረዳሉ።
"ሕክምናውን በፍጥነት ለሴቶች ማድረስ እንደምንችል ተስፋ አደርጋለሁ" ይላሉ።
ብልትን ለማጽዳት በሚል በሕክምና የማይመከሩ መንገዶችን መከተል ጉዳቱ እንደሚያባብስ ባለሙያዎች ያስጠነቅቃሉ። ወደ ብልት ውስጥ ውሃ በማስገባት ለማጽዳት መሞከር አንደኛው ባለሙያዎች የማይመክሩት መንገድ ነው።
ጄል እና ስፕሬይ መጠቀምምመ አይመከረም። በሌላ በኩል የእርግዝና መቆጣጠሪያ መድኃኒቶች የብልት ባክቴሪያ መጠን ላይ ጉዳት አያስከትሉም።
ጤናማ አመጋገብ መከተል፤ በተለይም ቫይታሚን ኤ፣ ሲ፣ ዲ እና ኢ ያለባቸው ምግቦችን ማዘውተር ይመከራል።
ፎሌት እና ካልሸየም ያላቸው ምግቦችን መውሰድም ጠቃሚ ነው።
ከልክ ያለፈ ውፍረት የብልት ጤናማ ባክቴሪያ መጠንን እንደሚቀንስ ጥናቶች አሳይተዋል።
ሲጋራ ማጨስም በሴቶች የብልት ጤና ላይ ጉዳት ያስከትላል።
ከሚያጨሱ ሴቶች አንጻር 15 በመቶ የሚሆኑ የማያጨሱ ሴቶች የብልታቸው ባክቴርያ መጠን የተመጣጠነ ሆኖ ተገኝቷል።
"አትክልት እና ፍራፍሬ መመገብ፣ በቂ እንቅልፍ ማግኘት እና ውሃ አብዝቶ መጠጣት ይመከራል። እነዚህ አጠቃላይ ጤና እና የብልት ጤናን ለመጠበቅ ይረዳሉ" ይላሉ ባለሙያዋ።