ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ሩሲያ የተጣለባትን ማዕቀብ የጣሰ ነዳጅ ጫኝ መርከብ መያዟን ፈረንሳይ አስታወቀች
ሩሲያ የተጣለባትን ማዕቀብ የጣሰ ነዳጅ ጫኝ መርከብ በሜድትራኒያን ባሕር ላይ መያዟን ፈረንሳይ አስታወቀች።
የፈረንሳይ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን እንደተናገሩት 'ዘ ግሪንች' የተባለው ነዳጅ ጫኝ መርከብ "በሐሰተኛ ሰንደቅ አላማ ሲንቀሳቀስ" የነበረ ሲሆን "ዓለም አቀፍ ማዕቀብ" የተጣለበት ነው።
የፈረንሳይ ባሕር ኃይል እንደ ዩናይትድ ኪንግደም ካሉ አጋሮቹ ጋር መርከቡ በስፔን እና ሞሮኮ መካከል ሲንቀሳቀስ በቁጥጥር ሥር አውሎታል።
በፓሪስ የሩሲያ ኤምባሲ መርከቡ ስለመያዙ መረጃ እንዳልደረሰው አስታውቋል።
'shadow fleet' የሚል ስያሜ የተሰጣቸው ነዳጅ ጫኝ መርከቦች ምዕራባውያን ሩሲያ ላይ ከጣሉት ማዕቀብ ለማምለጥ የሚንቀሳቀሱ ናቸው። የመርከቦቹ ባለቤት ግልጽ ሳይደረግ ነዳጅ ያዘዋውራሉም ተብሏል።
'ዘ ግሪንች' የተባለው መርከብ በሰሜን ሩሲያ አካባቢ ሲንቀሳቀስ ነው የተያዘው። መርከቡ የኮሞሮስ ሰንደቅ አላማ እንዳለው ፈረንሳይ አስታውቃለች።
ማክሮን በኤክስ ገጻቸው "ማዕቀቦች ተፈጻሚነት እንዲኖራቸው ዓለም አቀፍ ሕግን እንተገብራለን። መርከቡ ዩክሬን ላይ የተከፈተውን ጦርነት ለመደገፍ የሚውል እንቅስቃሴ ያደርጋል" ብለዋል።
መከላከያ ሚኒስትሩ ጆን ሄሊ እንዳሉት የዩናይትድ ኪንግደም ባሕር ኃይል መርከቡን "በመከታተል እና በመቆጣጠር" ድጋፍ ሰጥቷል።
"ከአጋሮቻችን ጋር በመሆን የፑቲንን ሕገ ወጥ የዩክሬን ወረራ የሚደግፉ መርከቦችን እንገታለን" ብለዋል።
ዩኬ በሩሲያ ሥር በሚተዳደሩ 544 መርከቦች ላይ ማዕቀብ ጥላለች።
የዩክሬን ፕሬዝዳንት ቮሎድሚር ዘለንስኪ እርምጃውን አድንቀዋል።
"የሩሲያ ነዳጅ ለጦርነቱ ግብዓት እንዳይውል የሚረዳ እርምጃ ነው። መርከቦቹ መያዝ አለባቸው። የጫኑት ነዳጅ ቢሸጥስ ፍትሐዊ አይሆንም?" ሲሉ በኤክስ ገጻቸው ጽፈዋል።
በዳቮስ ባደረጉት ንግግር የአውሮፓ መሪዎች ደኅንነታቸውን ለማስጠበቅ ተጨማሪ እርምጃ እንዲወስዱ ጠይቀዋል።
"አውሮፓ ስለወደፊቱ ማውራት ትወዳለች። እርምጃ ለመውሰድ ግን አትፈቅድም" ሲሉም ተናግረዋል።
ጦርነቱ ከተጀመረ ወዲህ በርካታ የአውሮፓ አገራት ሩሲያ ላይ ማዕቀብ ጥለዋል።
በያዝነው ወር መባቻ፤ አሜሪካ የደገፈቻቸው የዩኬ ወታደሮች የሩሲያ ሰንደቅ አላማ ያለው ነዳጅ ጫኝ መርከብ በአትላንቲክ አቅራቢያ በቁጥጥር ሥር አውለዋል።
መርከቡ ማዕቀብ በመጣስ ከቬንዝዌላ ወደ ሩሲያ ነዳጅ እያጓጓዘ ነበር ተብሏል።
ሩሲያ መርከቡ መያዙን ኮንናለች። በሌሎች አገራት የተመዘገቡ መርከቦችን የመያዝ መብት እንደሌላቸውም አስታውቃለች።
ያለፈው ጥቅምት ላይ ፈረንሳይ 'ዘ ቦራኬይ' የተባለ ማዕቀብ የተጣለበት ነዳጅ ጫኝ መርከብ በምዕራባዊ የአገሪቱ ክፍል ይዛለች።
ቬንዝዌላ፣ ኢራን እና ሩሲያ ማዕቀብ የተጣለባቸው ነዳጅ ጫኝ መርከቦችን ማንቀሳቀሳቸው እየተለመደ መጥቷል።
ኤስኤንድፒ የተባለው የፋይናንስ ተቋም እንዳለው፤ በመላው ዓለም ከሚንቀሳቀሱ አምስት መርከቦች አንደኛው ማዕቀብ የተጣለበትን ነዳጅ ያዘዋውራል።