ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ከኬንያዋ ማንዴራ ግዛት እንዲወጡ ማስጠንቀቂያ የተሰጣቸው ኢትዮጵያዊያን ስጋት
በሰሜን ምሥራቅ ኬንያ፣ ማንዴራ ግዛት የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን አካባቢውን በአስቸኳይ ለቅቀው ካልወጡ 'ትገደላላችሁ' የሚል ማስጠንቀቂያ እንደተሰጣቸው ተናገሩ።
ስማቸው እንዳይገለጽ የጠየቁ በማንዴራ ግዛት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች "ሕይወታችን አደጋ ላይ ወድቋል" ሲሉ ለቢቢሲ ገልጸዋል።
በኬንያ የኢትዮጵያ ኤምባሲ በበኩሉ ጉዳዩን እየተከታተለ እንደሚገኝ አስታውቋል።
ቢቢሲ ካነጋገራቸው ኢትዮጵያውያን አንደኛው የሁለት ልጆች አባት ሲሆን፤ በማንዴራ ለስምንት ዓመት እንደኖረ ተናግሯል።
"ሞተር ገዝተን፣ ሆቴል ከፍተን እየሠራን ነበር። መነሻውን አናውቅም ግን 'ኢትዮጵያዊ የሆኑ ሁሉም ይውጡ' ብለው ተነሱ" ብሏል።
ኢትዮጵያዊው ስደተኛ "ይውጡ ብለው ቢተውን ጥሩ ነበር። ግን ዝም ብለው እያሰሩ ብር እየተቀበሉ ነው። በፓሊስ መኪና መጥተው ከታክሲ ውስጥ እያፈሱ እየወሰዱ ነው። በጣም ተቸግረናል" ሲልም አክሏል።
ኢትዮጵያዊው "የሚያግዘን ሰው አጥተናል" በማለትም ያሉበትን ሁኔታ ይገልጻል።
በርካታ ኢትዮጵያዊያን በማንዴራ ግዛት በተለያዩ ሥራዎች ላይ ተሰማርተው እንደሚኖሩ የሚናገው ነዋሪው "የኢትዮጵያዊያን ቁጥር በ10ሺህ ይገመታል" ብሏል።
"ኢትዮጵያዊያንን አንፈልግም፤ ይውጡልን። አገራችንን እየወረሱ ነው ብለው ነው የተነሱት" የሚለው ስደተኛው፤ ስለ ጉዳዩ ማብራሪያ ለመጠየቅ ቢሞክሩም "የአገር ሽማግሌዎችን ጠይቁ" የሚል ምላሽ እንደተሰጣቸው ገልጿል።
ከኢትዮጵያዊያኑ መካከል የተወሰኑት ወደ አገር ሽማግሌዎች ሲሄዱ ደግሞ "እናንተን ማየት አንፈልግም። አገራችንን ለቅቃችሁ ውጡ" እንደተባሉም አክሏል።
በማንዴራ ግዛት በተደረጉ ስብሰባዎች ላይ፤ ኢትዮጵያዊያን ስደተኞች በሞተር ሳይክል የሟጓጓዝ እና የሆቴል ዘርፍ ላይ መሰማራታቸውን በመጥቀስ "እኛስ ምን ሠርተን እንብላ?" የሚል ቅሬታ መነሳቱንም ገልጿል።
በማንዴራ ግዛት ከሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን አብዛኞቹ ከወላይታ ዞን እና ኦሮሚያ ክልል አካባቢዎች መሰደዳቸውን ቢቢሲ ያነጋገራቸው ነዋሪዎች ይገልጻሉ።
"እስከ ጥር 5 ለቅቃችሁ ካልወጣችሁ ትገደላላችሁ ብለውናል"
ሌላ ቢቢሲ ያነጋገረው ኢትዮጵያዊ ስደተኛ በበኩሉ "የአሁኑ 'የውጡልን ዘመቻ' የተጀመረው ባለፈው ሳምንት ኢትዮጵያዊ መገደሉን ተከትሎ ነው" ብሏል።
የኢትዮጵያዊውን አስከሬን ወደ አገር ቤት ለመላክም "አልፈቀዱልንም" ሲል ነዋሪው ይገልጿል።
ኢትዮጵያዊው ስደተኛ ቡራቡር የሚባል አካባቢ እንደተገደለ ጠቅሶ "የተገደለበት ጥይት ከሰውነቱ ወጥቷል" የሚል ምላሽ እንደተሰጣቸው እና የአስከሬን ምርመራ ሳይደረግ እንደቀረ ተናግሯል።
በዚያው አካባቢ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን ከቀበሩት በኋላ 'ኢትዮጵያዊያንን አንፈልግም፤ ለቅቀው ይውጡልን' የሚል ዘመቻ መነሳቱን ገልጿል።
ኢትዮጵያዊያን ከማንዴራ ግዛት ለቅቀው እንዲወጡ የተቀመጠው 'ቀነ ገደብ' ጥር 5 እንደሆነ የተናገረው ነዋሪው፤ ከዚያ በኋላ በአካባቢው የሚገኙ ስደተኞች "በድንጋይ ተቀጥቅጠው ይገደሉ" የሚል ዘመቻ መከፈቱን ይናገራል።
ኢትዮጵያዊያን ስደተኞች ከማንዴራ ግዛት ለቅቀው ይውጡ፤ ካልወጡ ግን ይገደላሉ የሚለው "የአገር ሽማግሌዎች ውሳኔ ነው" የሚል ነገር መስማታቸውን የተናገረው ነዋሪው፤ "ድምጽ ማጉያ መኪና ላይ ተጭኖ እየተዞረ ጭምር ውጡልን የሚል ዘመቻ እየተለፈፈ" መሆኑን ለቢቢሲ አስረድቷል።
"ትዕዛዙ የወጣው ከአገር ሽማግሌዎች ነው። የመንግሥት አካላትም ሳይኖሩበት አይቀርም። እያሰሩ እስከ 20ሺህ [ሽልንግ] ይጠይቃሉ። የከፈለውን ይለቃሉ። ገንዘብ የሌለውን እስከ ሁለት ወር ያስራሉ።"
'አገራችንን ለቅቀው ይውጡልን' የሚለው ነገር ከዚህ ቀደምም እንደነበረ የጠቀሰው ኢትዮጵያዊው የአሁኑ ግን "በጣም የበረታ" ከመሆኑ የተነሳ "ሁኔታው ለሕይወታችንም አስጊ ነው" በማለት ይገልጻል።
"ከዚህ በፊት በአፍ ያወራሉ እንጂ 'ፓወር' አልነበረውም። ልጁ ከሞተ ወዲህ ግን ነገሩ እየጠነከረ እየሄደ ነው። የአገር ሽማግሌዎቹ [ኢትዮጵያውያኑ] ቢገደሉም ተጠያቂነት የለም የሚል አዋጅ አውጥተዋል" ሲልም አክሏል።
"ሴት እና ወንድ ተቃቅፈው ይሄዳሉ" እንዲሁም "በማታ ወንዶች ለዘረፋ ይወጣሉ" በሚል ስለ ኢትዮጵያዊያኑ ስደተኞች እንደሚነገር እና ብረታ ብረት ለቀማ ሥራ ላይ እንኳን እንዳይሰማሩ ዘመቻ መከፈቱን ተናግሯል።
ኢትዮጵያዊያኑ በዚህ የኬንያ ግዛት በብዛት ዝቅተኛ ገቢ በሚያስገኙ ሥራዎች ላይ እንደተሰማሩ የጠቀሰው ነዋሪው፤ ዘመቻ ከተከፈተባቸው በኋላ ቀጣሪዎች ደመወዛቸውን ቶሎ ከፍለዋቸው ከማንዴራ እንዲወጡ በአገር ሽማግሌዎች እንደተነገረ ይገልጻል።
"ራሳችንን ማዘጋጀት እንጂ ሌላ አማራጭ የለንም"
በማንዴራ ግዛት በተለያየ ሥራ ላይ ተሰማርተው ከነበሩ ኢትዮጵያዊያን መካከል የተወሰኑት ለቅቀው እንደወጡ እና ሌሎችም ለመውጣት እየተዘጋጁ እንደሆነ ስደተኞቹ ተናግረዋል።
"እኛም ያለን መፍትሔ ራሳችንን ማዘጋጀት እንጂ ሌላ አማራጭ የለንም" ሲል አንደኛው ስደተኛ ይገልጻል።
ከሳምንት በፊት የተገደለው ኢትዮጵያዊ ፍትሕ አለማግኘቱን በማንሳትም፤ ". . .ሰውን የመሰለ ነገር ደሙ ፈስሶ ወደ አገራችን ሬሳው እንዳይገባ ብሎ ወደ ሕግ ተጠግቶ እስካልተጠየቀ ድረስ ደም የለንም ማለት ነው። መንግሥት እንደሌለን ነው የሚያሳየው" ብሏል።
በኬንያ የኢትዮጵያ ኤምባሲ በበኩሉ "ጉዳዩ አዲስ አይደለም፤ እየተከታተልነው ነው" ሲል ለቢቢሲ ምላሽ ሰጥቷል።
የሚሲዮኑ ምክትል ኃላፊ አምባሳደር ደመቀ አጥናፉ "ለውጭ ጉዳይ አሳውቀናል። ከዚህ በፊት እንዳደረግነውም ለማንዴራ አስተዳደርም አሳውቀን እየተከታተልን ነው" ብለዋል።
በአካባቢው ተመሳሳይ ዘመቻዎች ከዚህ ቀደም እንደነበሩ በመግለጽ "የመንግሥት አይደለም፤ ግለሰቦች ናቸው። ያኔ ጊዜ ገደብ አልሰጡም፤ አሁን ሰጥተዋል" ሲሉም አክለዋል።
የአካባቢው አስተዳደር እንዲሁም ማዕከላዊው መንግሥትም "እየተባበረ ነው" ያሉት አምባሳደር ደመቀ፤ ከማኅበረሰብ ተወካዮች ጋርም እየተነጋገሩ እንደሚገኙ ተናግረዋል።
ስደተኞቹ "ሕገ ወጥ ናቸው፤ መታወቂያ የላቸውም" ማለት የሚችለው የመንግሥት አካል ብቻ እንደሆነ ጠቅሰውም "የመንግሥት አካል ያለው ነገር የለም። አስፈላጊውን ጥበቃ እየሰጠ ነው" ሲሉም ለቢቢሲ ገልጸዋል።