ኢትዮጵያዊያን እና ኤርትራዊያን ስደተኞች ወደ አውሮፓ ለመግባት ቤላሩስን የሚመርጡት ለምንድን ነው?

የቤላሩስ ድንበር ጠባቂዎች ሁለት ኤርትራዊያን ስደተኞች አብሯቸው ሲጓዝ ነበር የተባለ ስደተኛ አስከሬን ይዘው በላቲቪያ ድንበር አዋሳኝ በሆነው ብራትስላቭ ክልል ውስጥ ማግኘቱን የኤስቢ የዜና አገልግሎት ዘግቧል።

ኤርትራዊ መሆናቸውን በአስተርጓሚ የገለጹት ስደተኞቹ ላቲቪያ መግባታቸውን፤ ነገር ግን የወታደር ልብስ በለበሱ ሰዎች ድብደባ እንደተፈፀመባቸው ገልጸዋል።

በተጨማሪም ተንቀሳቃሽ ስልኮቻቸው እንደተወሰደባቸው እና በሽጉጥ በማስፈራራት በቤላሩስ ድንበር ላይ እንደተጣሉ ተናግረዋል።

በጉዞ ላይ ሳሉ በደረሰበት ድብደባ የሞተው የ29 ዓመቱ ስደተኛ ሕይወቱ ማለፉን የቤላሩስ ፖሊስ አረጋግጦ የአስከሬን ምረምራ እየተደረገ ነው ብሏል።

ሁለቱ ኤርትራውያን ስደተኞች ደግሞ ወደ ጤና ተቋም ተወስደው የሕክምና እርዳታ ተደርጎላቸዋል።

ስደተኞች ቤላሩስን እንደ መሸጋገሪያ የሚጠቀሙት ለምንድን ነው?

የቤላሩስ እና የፖላንድ ድንበሮች በሺዎች ለሚቆጠሩ ስደተኞች በጣም አደገኛ ከሆኑ ወደ አውሮፓ የመግቢያ መንገዶች አንዱ ነው።

ከአውሮፓውያኑ 2021 ጀምሮ በርካታ ሺህ ስደተኞች የዚህችን አገር ድንበር በማቋረጥ ወደ አውሮፓ እንደሚገቡ የተለያዩ ዘገባዎች ያመለክታሉ።

መንገዱ አስቸጋሪ በሚሆንበት ጊዜ ስደተኞቹ ወደ ሊትዌኒያ በሰሜን ምዕራብ ቤላሩስ፣ በሰሜናዊ ቤላሩስ ላቲቪያ እና በምሥራቅ ቤላሩስ ወደ ፖላንድ የመሻገር አማራጭ አላቸው።

ከቀድሞዋ ሶቪየት ኅብረት ግዛቶች አንዷ የነበረችው ቤላሩስ፣ በምሥራቅ አውሮፓ የምትገኝ እና ከአምስት አገራት ጋር የምትዋሰን የባሕር በር የሌላት አገር ናት።

በአውሮፓውያኑ 1990 ከሶቭየት ኅብረት ተነጥላ ራስዋን የቻለች አገር የሆነችው ቤላሩስ በስተምሥራቅ እና ሰሜን ምሥራቅ ከሩሲያ፣ በስተደቡብ ከዩክሬን፣ በስተምዕራብ ከፖላንድ በስተሰሜን ምዕራብ ደግሞ ከሊትዌንያ እና ከላቲቪያ ጋር ትዋሰናለች።

ከሦስት የአውሮፓ ኅብረት አባል አገራት ጋር የምትዋሰነው ቤላሩስ የኅብረቱ አባል የመሆን ፍላጎት የላትም።

ይህች በአውሮፓ ኅብረት የስደተኞች መሸጋገሪያ ናት በሚል ከፍተኛ ትችት የሚሰነዘርባት ቤላሩስ፣ ብዙ ስደተኞችንም ወደ አገራቸው መልሳለች።

በቤላሩስ በኩል ወደ ሌሎች የአውሮፓ አገራት የሚገቡት አብዛኞቹ ከኢራቅ፣ ከአፍጋኒስታን እና ከሶሪያ የመጡ ስደተኞች ሲሆኑ ኢትዮጵያዊያን እና ኤርትራዊያን ጨምሮ በርካታ አፍሪካዊያንም ይህንን መስመር ይጠቀማሉ።

ከቱርክ ኢስታንቡል እና አናቶሊያ፣ ከቤሩት [ሊባኖስ]፣ ከባግዳድ [ኢራቅ] እና ከዱባይ [አረብ ኤምሬት] ወደ ቤላሩስ ዋና ከተማ ሚኒስክ የቀጥታ በረራዎች አሉ።

ከቱርክ፣ ከቡልጋሪያ፣ ከሮማኒያ፣ ከሞልዶቫ እና ከዩክሬን ወደ ስዊድን፣ ኖርዌይ እና ጀርመን የሚሄዱ ስደተኞች መሸጋገሪያ አገር ነች።

የቤላሩስ አየር መንገድ ቤላቪያ ከቱርኮቹ ኢስታንቡል እና አንታሊያ እንዲሁም ከዱባይ በረራዎች አሉት።

የቱርክ አየር መንገዶችም ከኢስታንቡል ወደ ሚኒስክ በረራ አላቸው።

በተጨማሪም በሕጋዊ መንገድ ወደ ሩሲያ በመግባት ወደ ቤላሩስ ወደ ፖላንድ፣ ጀርመን እና ሌሎች አገራት ይሻገራሉ።

ለረጅም ጊዜ ከኢትዮጵያ እና ኤርትራ የሚነሱ ስደተኞች በሊቢያ እና በሜዲትራኒያን ባሕር አቋርጠው ወደ አውሮፓ የሚደርጉት ጉዞ አደገኛ ከመሆኑ የተነሳ ፊታቸውን ወደ ሌላ መስመር አዙረዋል።

በተጨማሪም ወደ አውሮፓ መድረስ አልመው ከአገራቸው የሚወጡ ስደተኞች በጦርነት ከፍተኛ ጉዳት በደረሰባት ሊቢያ ውስጥ እንግልት ይደርስባቸዋል።

በዚህ ምክንያት ብዙ አፍሪካውያን ስደተኞች በምሥራቅ አውሮፓ በኩል ወደ መካከለኛው አውሮፓ የሚወስደውን መንገድ ይመርጣሉ።

የአውሮፓ ኅብረት ቤላሩስ የአልጄሪያ፣ የግብፅ፣ የጋምቢያ፣ የግሪክ፣ የሄይቲ፣ የኢራን እና የናሚቢያ ዜጎችን ጨምሮ የ76 አገራት ዜጎች ያለ ቪዛ ወደ ግዛቷ እንዲገቡ መፍቀዷ ለስደተኞች መጉረፍ አንዱ ምክንያት ነው በማለት ከስሷታል።

እነዚህ የ76 አገራት ዜጎች ያለቪዛ ወደ ቤላሩስ መጀመሪያ ሲገቡ የ30 ቀናት ቪዛ ይሰጣቸዋል፤ ነገር ግን ቪዛው ሲያልቅ ወደ አገራቸው ከመመለስ ይልቅ የቤላሩስ መንግሥት ፖላንድ ድንበር ላይ ወስዶ ይጥላቸዋል የሚል ክስ ይቀርብበታል።

እንደ ኢትዮጵያዊያን እና ኤርትራዊያን ያሉ ስደተኞች በቪዛ ወደ ቱርክ ከገቡ በኋላ በግሪክ፣ በቡልጋሪያ፣ በሮማኒያ እና በዩክሬን በኩል ወደ ቤላሩስ በመግባት ለመንግሥት እጅ ይሰጣሉ።

ከዚያም የአገሪቱ መንግሥት ወደ ፖላንድ፣ ሊቱዌኒያ እና ላቲቪያ ያሉ አገራት ድንበሮች እንደሚወሰዱ አንድ ኤርትራዊ ለቢቢሲ ትግርኛ ተናግሯል።

ይኸው ግለሰብ "ወቅቱን ካልመረጥክ አስቸጋሪ ሁኔታ ሊገጥምህ ይችላል" በማለት የአየር ጠባዩ መንገዱን ለስደተኞቹ አስቸጋሪ ያደርገዋል ብሏል።

ስደተኞቹ አንዴ ወደ ፖላንድ፣ ላቲቪያ ወይም ሊቱዌኒያ ከተሻገሩ ወደ የትኛውም የአውሮፓ ክፍል በባቡር መሄድ ይችላሉ።

ነገር ግን ድንበር ላይ ከተያዙ ወደ ቤላሩስ ይመልሷቸዋል።

በ2024 ብቻ ኤርትራዊያን፣ ኢትዮጵያዊያን እና ሶማሊያዊያንን ጨምሮ ከ17 ሺህ በላይ ስደተኞች በቤላሩስ በኩል ወደ አገሪቱ ድንበር አቋርጠው መግባታቸውን መረጃዎች ያመለክታሉ።

ይህም ከ2023 ጋር ሲነጻጸር በሦስት እጥፍ ይበልጣል።

በዚህ የአውሮፓውያን ዓመት ከቤላሩስ ወደ ላትቪያ ለመሻገር የሞከሩ ከ8 ሺህ በላይ ስደተኞች በአገሪቱ የድንበር ጠባቂዎች ወደ ሚኒስክ ተመልሰዋል።

ነገር ግን ድንበር አቋርጠው ወደ ሌሎች አገራት የገቡት ቁጥራቸው ምን ያህል እንደሆነ ግልጽ አይደለም ሲል የላቲቪያ ፖሊስ ገልጿል።

በ2024 ወደ ስድስት ሺህ የሚጠጉ ስደተኞች በላቲቪያ ድንበር ጠባቂዎች ተይዘው ወደ ቤላሩስ ተመልሰዋል።

በተመሳሳይ በ2024 ወደ 30 ሺህ እና በ2025 ከ26 ሺህ የሚበልጡ ስደተኞች ከቤላሩስ ወደ ፖላንድ ለመሻገር ሲሞክሩ በፖላንድ ድንበር ጠባቂዎች ተይዘው መታሰራቸውን ሰነዶች ያሳያሉ።

የአውሮፓ ኅብረት እንደ ቱርክ ያሉ አገራት የኢራቅ፣ የየመን፣ የሶሪያ ዜጎች በቱርክ አየር መንገድ ወደ ሚኒስክ (የቤላሩስ ዋና ከተማ) እንዳይበሩ ጠይቋል።

ቱርክ ካለፈው ዓመት መጨረሻ ጀምሮ ይህንኑ ተግባራዊ እያደረገች ነው።

የተባበሩት አረብ ኤሚሬትስ ከዚህ ዓመት መጀመሪያ አንስቶ የኢራቅ፣ የየመን፣ የሶሪያ፣ የሶማሊያ፣ የኤርትራ እና የኢትዮጵያን ጨምሮ የበርካታ አገራት ዜጎች በቀጥታ ወደ ቤላሩስ እንዳይበሩ ከልክላለች።

መሃሪ የተባለ ኤርትራዊ "ቤላሩስ እንደ ደረስኩ ከዱባይ ወጥቼ በቀጥታ ወደ ሚኒስክ ሄጄ ለአንድ ሳምንት ያህል ቆየሁ፤ ከዚያም በቤላሩስ ድንበር ላይ ወደምትገኘው ብሩዝጊ ከተማ ሄድኩ" ሲል ወደ አውሮፓ ለመግባት ያቋረጣቸውን አገራት ለቢቢሲ ተናግሯል።

መሃሪ በፖላንድ ኩዚኒካ ከተማ አቅራቢያ በምትገኘው ብሩዝጊ ውስጥ የስደተኞች ካምፕ እንዳለ እና በሺዎች የሚቆጠሩ ስደተኞች በዚያ ተጠልለው እንደሚገኙ ያስረዳል።

"ከቤላሩስ ወደ ፖላንድ ስታቋርጥ ከተያዝክ የፖላንድ ድንበር ጠባቂዎች ሰነድህን ወይም ሞባይል ስልክህን ወስደው ወደ ካምፑ ይመልሱሃል" ብሏል።

"እስከ አስራ አምስት ጊዜ በፖላንድ ፖሊሶች ተይዘው የተመለሱ ሰዎችን አስታውሳለሁ፤ ካምፑ ውስጥ ከ40 በላይ ኤርትራዊያን ነበሩ" ብሏል።

ሊትዌኒያ ከፖላንድ የሚመጡ ስደተኞችን ለመከላከል ድንበሯን አጥብቃ በመጠበቅ የቤላሩስ የሰሌዳ ቁጥር ያላቸው ተሽከርካሪዎች ወደ አገሪቱ እንዳይገቡ ከልክላለች።

በዚህ ምክንያት በ2024 ከቤላሩስ ወደ ሊትዌኒያ ለመሻገር የሞከሩ ከ800 ያላነሱ ስደተኞች በቁጥጥር ስር ውለዋል።