ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የአሜሪካ ኃያላን ፖለቲከኞች እና ቱጃሮች በድብቅ በሚገናኙበት ስፍራ ባዕድ አምልኮ ይካሄዳል?
"ከ10 ዓመት በፊት በጥቁር አፍሪካ ከቅኝ ግዛት ነፃ የሆኑ ሀገራት ሁለት ብቻ ነበሩ። እነሱም ኢትዮጵያ እና ላይቤሪያ ናቸው።"
ሪቻርድ ኒክሰን በአውሮፓውያኑ 1967 በርካታ ሀገራትን ጎብኝተው መጡ።
ኒክሰን በ1968 ለሚደረገው ምርጫው ራሳቸውን ዕጩ አድርገው አቅርበዋል። የምረጡኝ ዘመቻቸውን እያጧጧፉት ነበር።
በወቅቱ ያለውን የዓለም ሁኔታ የቃኙበትን ረዘም ያለ ንግግር ያሰሙት ቦሄሚያን ግሮቭ ተብሎ በሚታወቀው ክበብ ነው።
ኒክሰን ምርጫውን አሸነፉ። 37ኛው የአሜሪካ ፕሬዝደንት ሆኑ።
የፕሬዝደንትነት ዘመናቸው በስኬት እና ቅሌት የታጀበው ኒክሰን ቦሄሚያን ግሮቭ የተሰኘው ክበብ ተገኝተው ለቱጃር ጓደኞቻቸው ንግግር ሲያደርጉ በሮናልድ ሬገን ታጅበው ነበር።
ይህ ክበብ በጥሪ ወረቀት የሚገባበት፤ ሳን ፍራንሲስኮ ጫካ ውስጥ ተደብቆ የሚገኝ ቦታ ነው።
የዓለማችን ኃይላን ፖለቲከኞች እና ቱጃሮች በዓመት አንድ ጊዜ ተሰባስበው ይዝናናሉ፤ ይዶልታሉ፤ አምልኮ መሰል ነገር ያደርጋሉ... ሌላም ሌላም።
አመሠራረት
ቦሄሚያን ግሮቭ በአውሮፓውያኑ 1872 በአርቲስቶች፣ በፀሐፊያን፣ በተዋንያን፣ በጠበቆች እና በጋዜጠኞች የተመሠረተ ክበብ ነው።
መሥራቾቹ የሚያመሳስላቸው አንድ ነገር ነበር። ሁሉም ቀን የወጣላቸው ሀብታሞች ነበሩ።
ክበቡን ሲመሠርቱት ዓላማቸው በዓመት አንድ ጊዜ ተገናኝተው ባሕል እና ፖለቲካን ከጥበብ ጋር እያዋዙ ማውጋት ነበር።
ይህን ለማድረግ ፖለቲከኞች እና የንግድ ሰዎችን ለማካተት ወሰኑ።
በካሊፎርኒያ ግዛት ሶኖማ ተብላ በምትታወቀው መንደር ሬድዉድ ጫካ ውስጥ እየተገናኙ ያወጉ ጀመር።
ነገር ግን እነዚህ ኃያላን ሰዎች ተገናኝተው ምን እንደሚያደርጉ የሚያውቅ የለም። ክበቡ በሽቦ አጥር የተከበበ፣ ለመግባት እና ለመውጣት ፈቃድ የሚያስፈልገው፣ ካሜራ የማያውቀው ነው።
ቦሄሚያን የሚለው ቃል የዘመነ፣ የተማረ፣ ከተሜ የሚለውን ለመግለጽ የዋለ ነው። የክበቡ አርማ ደግሞ 'አውል' አሊያም ጉጉት የምትባለው ወፍ ናት።
ቱጃሮቹ ሲገናኙ ይበላሉ፣ ይጠጣሉ፣ ሙዚቃዊ ትዕይንት ይታደማሉ። ሲጀመር የሚገናኙበት አድራሻ ከዓመት ዓመት ይለያይ ነበር። ነገር ግን በ1930ዎቹ ሳን ፍራንሲስኮ የሚገኘው ሬድዉድ ጫካ ቋሚ አድራሻቸው እንዲሆን ወሰኑ።
ምሥጢራዊው ክበብ
ክበቡ ከተመሠረተ ከ150 ዓመታት በላይ አስቆጥሯል።
የዚህ ክበብ አባል ለመሆን የጥሪ ካርድ ያስፈልግዎታል። ድረ-ገፁ እንደሚለው ከተመሠረተ ጊዜ ጀምሮ 2600 ገደማ አባላት አፍርቷል።
አባል ለመሆን የሚጠባበቁ ሰዎች ቁጥርም ቀላል አይደለም። የክበቡ አባል ለመሆን ከሀብታምም የናጠጡ ሀብታም፣ ከፖለቲከኛም ፈርጣማ ፖለቲከኛ መሆን ይጠይቃል።
ወደ ጉግል አቅንተው ቦሄሚያን ግሮቭ ብለው ቢፈልጉ በሤራ ትንታኔ የታጨቁ በርካታ ውጤቶችን ያገኛሉ።
ሌላው ቀርቶ አባል ካልሆኑ የክበቡ ድረ-ገፅን እንኳ መጎብኘት አይችሉም። ነጭ መደብ ላይ 'ሎግኢን ያድርጉ' የሚል መልዕክት ብቻ ነው የሚያገኙት። ወረድ ብሎ በክበቡ ተቀጥረው መሥራት ለሚፈልጉ የሥራ ማስታወቂያ ማስፈጠንሪያ ተቀምጧል።
ክበቡ በየዓመቱ በሚዘጋጀው ፕሮግራም ኮስተር ያለ ወሬ አይወራም፤ 'ለመዝናናት ነው የምነገናኘው' ይላል። ነገር ግን የአሜሪካ ኃያላን ግለሰቦች ተገናኝተው የዓለምን ሁኔታ የሚዘወር ውሳኔ ሁሉ እንደሚያስተላልፉ ይታማሉ።
ለማንሃታን ፕሮጀክት የዕቅድ ስብሰባ የተደረገው በቦሄሚያን ግሮቭ እንደሆነ ይታመናል። የማንሀታን ፕሮጀክት ለመጀመሪያው የአቶሚክ ቦምብ ውልደት ትልቅ አስተዋፅዖ ያደረገ ነው።
ቦሄሚያን ግሮቭ ከሦስት ዓመታት በፊት በአውሮፓውያኑ ሚያዝያ 2023 መነጋገሪያ ሆኖ ነበር።
ከአሜሪካ ዘጠኝ የጠቅላይ ፍርድ ቤት ዳኞች መካከል አንዱ የሆኑት ክላረንስ ቶማስ ቢሊየነር ከሆነ ወዳጃቸው በቀረበ ግብዣ ክበቡን ጎብኝተዋል ተብለው ተብጠለጠሉ።
'ፕሮፐብሊካ' የተባለው ጋዜጣ ባወጣው የምርመራ ዘገባ ጥቁር አሜሪካዊው የጠቅላይ ፍርድ ቤት ዳኛ ቦሄሚያን ግሮቭ መገኘታቸውን የሚያረጋግጥ ዘገባ አሳተመ።
ቦሄሚያን ግሮቭ 1100 ሄክታር ላይ ያረፈ ቦታ ነው።
የክበቡ አባላት እንግዳ ይዘው መምጣት ይችላሉ። ነገር ግን መገናኛ ብዙኃንም ሆኑ ሌሎች ያልተጋበዙ ሰዎች በፍፁም መግባት አይችሉም።
ከኒክሰን እና ክላረንስ ቶማስ በተጨማሪ ትልቁ ቡሽ፣ ፕሬዝደንት ሬጋን፣ ቱጃሩ ሮከፌለር፣ ፀሐፊው ማርክ ትዌይን፣ 'የ21ኛው ክፍለ ዘመን ዲፕሎማሲ አባት' ተብለው የሚጠሩት ሄንሪ ኪሲንጀር ክበቡን ከጎበኙ ታዋቂ ሰዎች መካከል ናቸው።
የክበቡ አባላት በአብዛኛው ወግ አጥባቂ የሆኑ ነጭ ወንዶች ናቸው።
ውስጡ ምን አለ?
ለሁለት ሳምንታት የሚቆየው የክበቡ አባላት ስብሰባ በመድረክ ትዕይንት፣ በአምልኳዊ ድርጊቶች እና በመጠጥ የታጀበ ነው። አባላቱ ውሃ ሽንታቸውን ባገኙት ሜዳ ላይ እንደሚሸኑ ይነገራል።
አባላቱ ብዙውን ጊዜ የሚገናኙት በወርሀ ሐምሌ ነው። የካሊፎርኒያ ፀሐይ አናት በምትበሳበት ወቅት።
ፀረ-ካፒታሊስቶች፣ የአካባቢ ጥበቃ ተሟጋቾች እና የፀረ-ኒውክሌር አራማጆች የኃያላኑን ስብሰባ ተቃውመው ሰልፍ አድርገዋል።
ነገር ግን የተቃዋሚዎች ቁጥር በየዓመቱ እየቀነሰ እንደመጣ ይነገራል።
በርካታ ጋዜጠኞች ወደ ቦሄሚያን ግሮቭ በድብቅ ገብተው ውስጡ ምን እንዳለ ለመዘገብ ሞክረዋል።
በአውሮፓውያኑ 1989 'ስፓይ' የተባለው መፅሔት "የዓለማችን እጅግ ድብቁ የወንዶች ፓርቲ" ሲል ጽፏል።
በ2000 ደግሞ የሤራ ትንታኔ አራማጁ አሌክስ ጆንስ በድብቅ ገብቶ የቀረፀው ምሥል የክለቡ አባላት አስፈሪ ያለው ነገር ሲያቃጥሉ ያሳያል።
ነገር ግን የጆንስ ዘጋቢ ፊልም ውሃ በማያነሱ ወቀሳዎች የተሞላ ሲሆን፣ 'ሰዎች ይሰዉበታል' የሚል ያልተረጋገጠ ክስ ያዘለ ነው።
አብሮት የነበረው ሌላኛው ጋዜጠኛ ጆን ሮንሰን በበኩሉ "በዕድሜ ገፋ ያሉ ሰዎች እንደ ልጅ የሚቦርቁበት ስፍራ" እንጂ የተለየ ነገር አላየሁም ይላል።
ከአሌክስ ጆንስ በተጨማሪ በርካታ ዩቲዩበሮች ወደ ቦሄሚያን ግሮቭ በድብቅ ገብተው ተንቀሳቃሽ ምሥል ይዘው ቢወጡም የባዕድ አምልኮ ይካሄድበታል፤ የኢሉሚናቲ ድርጊት ይስተዋላል ከሚሉ ከሤራ ትንታኔ ባለፈው ይህ ነው የሚባል ተጨባጭ መረጃ የላቸውም።
ነገር ግን ከክበቡ አባላት ውጪ ያለው አመለካከት አንዳች ስውር ነገር የሚዶለትበት እና የሚፈጽሚበት ስፍራ ታደርጎ መጠርጠሩ ቀጥሏል።