ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በአሜሪካ የስደተኞችን መሳደድ በመቃወም የንግድ ተቋማት ተዘግተው ነዋሪዎች አደባባይ ወጡ
በአሜሪካዋ ሚኒሶታ ግዛት በመቶዎች የሚቆጠሩ ተቋማት ተዘግተው በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ከባዱ ቅዝቃዜ ሳይበግቸራው አደባባይ በመውጣት የአሜሪካ መንግሥት በስደተኞች ላይ የሚያካሂደውን ማሳደድ ተቃወሙ።
በአብዛኛው የግዛቲቱ ክፍሎች ውስጥ ተቃውሞው የታየው አስተባባሪዎቹ የአሜሪካ የስደት እና የጉምሩክ ተቆጣጣሪ ተቋም (አይስ) የሚያካሂደውን ዘመቻ ለመቃወም ነዋሪዎች ወደ ሥራ፣ ትምህርት እንዲሁም ለግብይት እንዳይሄዱ ካበረታቱ በኋላ ነው።
አይስ በሚኒሶታ ግዛት ውስጥ ሕገወጥ ያላቸውን ስደተኞች ማደን የጀመረው ከስድስት ሳምንታት በፊት በፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ትዕዛዝ ከተሰጠው በኋላ ነው።
መንግሥት እየወሰደ ያለው እርምጃ የሕብረተሰቡን ደኅንነት ለመጠበቅ በሕገወጥ መንገድ ወደ አሜሪካ ገብተዋል ያላቸውን ወንጀለኞች ለመያዝ ነው ቢልም፤ ተቺዎች ግን ምንም ዓይነት የወንጀል ታሪክ የሌላቸው ስደተኞች እና የአሜሪካ ዜጋ ሆኑ ሰዎች ሳይቀሩ እየታሰሩ ነው ሲሉ እየተቃወሙ ነው።
አርብ ዕለት 100 የሚሆኑ ቀሳውስት በሚኒያፖሊስ አየር ማረፊያ የአሜሪካ አየር መንገዶች በመንግሥት ተይዘው ከአገር የሚባረሩ ስደተኞችን እንዳያሳፍሩ የሚጠይቅ ሰልፍ ሲደያርጉ በፖሊስ ለአጭር ጊዜ ተይዘው ነበር።
በአሁኑ ጊዜ በሺዎች የሚቆጠሩ የፌደራል መንግሥቱ ኃይሎች እየተካሄደ ያለውን ዘመቻ ለማገዝ በሚኒሶታ ግዛት ተሰማርተዋል።
ባለፈው ወር በግዛቲቱ ውስጥ የ37 ዓመቷ ሴት በአይስ መኮንኖች በተተኮሰባት ጥይት ከተገደለች በኋላ ተቃውሞው ተባብሶ ነዋሪዎች አደባባይ እየወጡ ነው።
ከዚሁ ግድያ ጋር በተያያዘ አንድ የሚኒያፖሊስ የኤፍቢአይ አባል በግድያው ዙሪያ የሚካሄደው ምርመራን መሥሪያ ቤቷ የያዘበትን መንገድ በመቃወም በዚህ ሳምንት ሥራዋን ለቅቃለች።
ትሬሲ መርገን የተባለችው የኤፍቢአይ አባል ሥራዋን ለመልቀቅ አንድ ምክንያት የሆናት "ምርመራው እንዲቋረጥ የደረሰባት ጫና" መሆኑን ሲቢኤስ ምንጮችን ጠቅሶ ዘግቧል።
ቢቢሲ የኤፍቢአይ አስተያየትን ለማግኘት ጥያቄ አቅርቧል።
ከሳምንታት በፊት በሚኒያፖሊስ ያሉ ቢያንስ ስድስት የአሜሪካ መንግሥት ዐቃቢያነ ሕጎች በፌደራል ደረጃ የሚደረገውን ምርመራ አስተዳደሩ የያዘበትን መንገድ በመቃወም ሥራቸውን መልቀቃቸው በአሜሪካ መገናኛ ብዙኃን ተዘግቧል።
አርብ ዕለት ከዜሮ በታች በሆነ ቅዝቃዜ ውስጥ የተደረገው የተቃውሞ ሰልፍ አስካሁን የአሜሪካ መንግሥትን የስደተኞች ፖሊሲ በመቃወም በሚኒሶታ ከታካሄዱት መካከል ትልቁ መሆኑ ተነግሯል።
በርካታ የንግድ ተቋማት በሮቻቸውን ዘግተው ተቃውሞውን የተቀላቀሉ ሲሆን፣ በስደተኞች ላይ እየተወሰደ ያለው እርምጃ በግዛቲቱ የምጣኔ ሀብት ስጋት መሆነን የገለጹ አሉ።
የአሜሪካ የስደት እና የጉምሩክ ተቆጣጣሪ ተቋም (አይስ) መኮንኖች በሚኒሶታ ግዛት ውስጥ እያካሄዱ ባለው አሰሳ ምክንያት ነዋሪዎች ስጋት ውስጥ ገብተው ከእንቅስቃሴ በመቆጠባቸው ሥራ እና ንግድ ቀንሶ ጫና መፈጠሩን የተቋማት ባለቤቶች ይናገራሉ።
ስጋቱ የተፈጠረው መንግሥት ሕገወጥ በሚላቸው ላይ ብቻ ሳይሆን የአሜሪካ ዜግነት ያገኙ እና ሕጋዊ ሰነድ ባላቸው የውጭ ዜጎች ላይ ጭምር በመሆኑ ተጽእኖው መክበዱ ተነግሯል።
የአይስ አባላት በግዛቲቱ መገኘት በርካታ የሚኒሶታ ነዋሪዎችን ያስቆጣ ሲሆን፣ በዚህም ምክንያት እነሱ እና ሌሎች የፌደራል መንግሥቱ ባለሥልጣናት በግዛቲቱ የሚያካሂዱትን ዘመቻ ተቃውመዋል።
ከቀናት በፊት በግዛቲቱ የሚገኙ የትምህርት ቤት ባለሥልጣናት እንዳሳወቁት ተቆጣጣሪዎቹ ዕድሜያቸው ከ5 አስከ 17 ዓመት የሚደርሱ ተማሪ ልጆችን ሳይቀር ይዘው ወስደዋል።
በአሜሪካ የቢቢሲ አጋር የሆነው ሲቢኤስ እንደዘገበው ደግሞ በደቡባዊ ሚኒያፖሊስ ከሰነድ አልባ አባቱ ጋር በመኪና እየሄደ የነበረ የሁለት ዓመት ሕጻንም ተይዟል።