ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የአሜሪካ ከፍተኛ ባለሥልጣን ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ጋር ስለ "ቀጣናዊ ሰላም እና ደኅንነት" ሊመክሩ ነው
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ምክትል ሚኒስትር ክርስቶፈር ላንዳው እና የአሜሪካ የአፍሪካ ዕዝ አዛዥ ጄነራል ዳግቪን አንደርሰን "በቀጣናዊ የሰላም እና ደኅንነት ጉዳዮች" ላይ ከጠቅላይ ሚኒስት ዐቢይ አሕመድ ጋር ለመምከር ወደ ኢትዮጵያ ሊጓዙ ነው።
ምክትል ሚኒስትሩ ከኢትዮጵያ በተጨማሪ ወደ ግብፅ፣ ኬንያ እና ጅቡቲ እንደሚያመሩ የአገሪቱ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት አስታውቋል።
የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት አርብ ጥር 15/2018 ዓ.ም. ያወጣው መረጃ እንደሚያመለክተው፤ ለስምንት ቀናት የሚዘልቀው ጉብኝት የሚጀምረው ዛሬ ቅዳሜ ጥር 16 ነው።
የሚቀጥለው ሳምንት እሑድ ጥር 24 እንደሚጠናቀቅም በመሥሪያ ቤቱ ምክትል ቃል አቀባይ ቶሚ ፒጎት ስም የወጣው መግለጫ ያስረዳል።
ክርስቶፈር በኤክስ ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሑፍ ወደ ግብፅ፣ ኢትዮጵያ፣ ኬንያ እና ጅቡቲ የሚያደርጉት "የመጀመሪያ ጉዞ" እንደሆነ ጠቅሰዋል።
የውጭ ጉዳይ ምክትል ሚኒስትሩ በአራቱም አገራት በሚያደርጓቸው ጉዞዎች በአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ "ቅድሚያ የሚሰጣቸውን ጉዳዮች" እንደሚያራምዱ መሥሪያ ቤታቸው ገልጿል። ቅድሚያ የሚሰጣቸው ጉዳዮች ተብለው የተዘረዘሩት "የንግድ ሚዛንን ማመጣጠን፣ ምቹ የንግድ ሁኔታን ማረጋገጥ እንዲሁም ሰላም እና ደኅንነት ማስፈን" የሚሉት ናቸው።
የመሥሪያ ቤቱ መረጃ እንዳመለከተው፤ ምክትል ሚኒስትሩ ክርስቶፈር የመጀመሪያ ጉዟቸውን የሚያደርጉት ወደ ግብፅ ነው። የክርስቶፈር የካይሮ ጉዞ የመጣው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የናይል ወንዝ ጉዳይን በተመለከተ ግብፅ እና ኢትዮጵያን ለማደራደር ያላቸውን ፍላጎት እየገለጹ ባሉበት ሰዓት ነው።
ትራምፕ ይህንን ፍላጎታቸውን የገለጹት ባለፈው ሳምንት ለግብፁ ፕሬዝዳንት አብዱል ፈታህ አል-ሲሲ በጻፉት ደብዳቤ ነው። በዚህ ሳምንት ደግሞ ሁለቱ ፕሬዝዳንቶች በስዊዘርላንዷ ዳቮስ ከተማ ሲካሄድ በነበረው የዓለም ኢኮኖሚ ፎረም ላይ ተገናኝተው ይህንኑ ጉዳይ አንስተዋል።
የውጭ ጉዳይ ምክትል ሚኒስትሩ ክርስቶፈር በግብፅ ቆይታቸው ከአገሪቱ ባለሥልጣናት ጋር ውይይት ከሚያደርጉባቸው ጉዳዮች አንዱ "በቀጣናዊ ተግዳሮቶች ላይ የሚደረግ ትብብርን" የሚመለከት እንደሆነ መሥሪያ ቤታቸው ገልጿል።
"የአሜሪካ እና ግብፅን የኢኮኖሚ ግንኙነት ስለማጠናከርም" ከባለሥልጣናቱ ጋር የሚነጋገሩት ምክትል ሚኒስትሩ፤ አገሪቱ ውስጥ "ኢንቨስት ከሚያደርጉ እና ከሚንቀሳቀሱ የአሜሪካ ኩባንያዎች ጋር" ውይይት እንደሚያደርጉ ተጠቅሷል።
የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤቱ መረጃ እንደሚያስረዳው ክርስቶፈር ከግብፅ በኋላ የሚኖሯቸውን ጉዞዎች የሚያደርጉት ከአሜሪካ የአፍሪካ ዕዝ አዛዥ ጄነራል ዳግቪን አንደርሰን ጋር ነው።
ምክትል ሚኒስትሩ፤ ወደ ኢትዮጵያ በሚያደርጉት ጉዞ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ እና ሌሎች ባለሥልጣናትን እንደሚያገኙ ተገልጿል። የመሥሪያ ቤቱ መረጃ፤ "ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድን ጋር ጨምሮ ከኢትዮጵያ ባለሥልጣናት ጋር በቀጣናዊ የሰላም እና ደኅንነት ጉዳዮች ላይ ይመክራሉ" ይላል።
በተጨማሪም ባለሥልጣናትን እና የግል ዘርፍ ተዋናዮችን አግኝተው "ለአሜሪካ የንግድ ተሳትፎን [ለማሳደግ] ያሉ ዕድሎችን ያስተዋውቃሉ" ተብሏል። በተጨማሪም በአዲስ አበባ ቆይታቸው፤ ከአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ማሕሙድ አሊ ዩሱፍ ተገናኝተው
"እንደ ሰላምን ማስፈን፣ የንግድ ትብብርን ማስፋፋት እና ሰብአዊ ቀውሶችን መፍታት ባሉ ቅድሚያ የሚሰጣቸው የጋራ ጉዳዮች ላይ" እንደሚወያዩ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤቱ አስታውቋል።
የውጭ ጉዳይ ምክትል ሚኒስትር ክርስቶፈር የኬንያ ቆይታ ከአገሪቱ ባለሥልጣናት ጋር "ሰፋ ያሉ ቀጣናዊ ጉዳዮችን" በተመለከተ ጭምር ውይይት የሚደረግበት እንደሆነ ተጠቅሷል።
የመሥሪያ ቤቱ መረጃ "ከኬንያ ባለሥልጣናት ጋር የንግድ ተሳትፎን፣ የፀረ ሽብር ትብብርን፣ ኬንያ በሄይቲ ደኅንነትን ለማስጠበቅ የምታደርገውን አስተዋጽኦ እና ሰፋ ያሉ ቀጣናዊ ጉዳዮችን አስመልክቶ ይወያያሉ" ሲል በናይሮቢ የሚነሱ አጀንዳዎችን ዘርዝርሯል።
የጅቡቲ ጉዞም በተመሳሳይ "በደኅንነት እና በፀረ-ሽብርተኝነት ትብብር እንዲሁም ንግድ ግንኙነቶች" ላይ እንደሚያተኩር ተገልጿል።