ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በዚህ ዘመን በምዕራቡ ዓለም በኮከብ ቆጠራ የሚያምኑ ሰዎች ቁጥር ለምን ጨመረ?
መቼስ ሁላችንም በዙሪያችን አንድ ኮከብ ቆጠራ (Astrology) የምትወድ/የሚወድ ጓደኛ ሳይኖረን አይቀርም።
በሚቀጥለው ሳምንት የሚገጥማቸውን የፍቅር አጋጣሚ፣ ወይ ደግሞ የሕይወት ፈተና፣ ወይ ደግሞ ሥራቸውን በከዋክብት አሰላለፍ ተመርኩዘው፣ ልደት ቀናቸውን አስልተው፣ ለዕጣ ፈንታቸው የሚዘጋጁ ጓደኞች።
ነገሩ ለእኛ ቢያስቀንም ለእነርሱ ግን አያስቃቸውም፤ የምር ጉዳይ ነው።
ደግሞም ሁሉም ሰው እንደእነዚህ ጓደኞቻችን ቀለል ላሉ ጉዳዮች ብቻ አይደለም ኮከብን የሚቆጥሩ፤ ኮከብ ቆጣሪን የሚያማክሩ።
አሁን አሁን በዓለም ላይ ብዙ ሰዎች ለትልልቅ ፖለቲካዊ እና አገራዊ ጉዳዮች ሳይቅር ኮከብ ቆጠራን ማማክር ይዘዋል።
ኮከብ ቆጠራን የሙጥኝ ያሉ ሰዎች በልደታቸው ቀን የኮከቦች እና የፕላኔቶች አሰላለፍ የሕይወታቸውን መስመር እና ዕጣ ፈንታ እንደሚወስን ያምናሉ።
ከሰው ጋር የሚኖራቸውን ግንኙነት፣ ባህሪ፣ አስተሳሰብ እና ዕድል በዚህ 'የከዋክብት እና የፕላኔቶች አሰላልፍ የተቃኘ ነው' ይላሉ።
ይህ ነገር ለብዙ ሰዎች ለስለስ ያለ ባዕድ አምልኮ ሊመስል ይችላል። ሆኖም ግን በተቀረው ዓለም የቢሊዮን ዶላሮች ቢዝነስ ብቻ ሳይሆን የሰዎች ጽኑ እምነት ያረፈበት፣ ከመዝናኛነት ከፍ ያለ፣ እንደ ዋዛ የማይታይ፣ ኮስተር ያለ ዘርፍ ነው።
ዘመን አመጣሽ አይደለም። አስትሮሎጂ በሕንድ እና በቻይና ከጥንት ጀምሮ የነበረ ነው። ምዕተ ዓመታትን አስቆጥሯል።
በተለይ በሕንድ ነገሩ ዛሬም ድረስ እንደዋዛ አይታይም።
አሁን አሁን በሕንድ አንዳንድ ፖለቲከኞች ምርጫ ለማሸነፍ ያላቸውን ዕድል የሚጠይቁት የፖለቲካ አማካሪዎቻቸው አይደለም፤ ኮከብ ቆጣሪዎችን እንጂ።
በምዕራቡ ዓለምም ቢሆን ብዙ ሰዎች ዛሬ ዛሬ ፖለቲካን ለመረዳት እና ለመተንበይ ኮከብ ቆጠራን በአማራጭነት ይመለከታሉ።
በዩናይትድ ኪንግደም (ዩኬ) እና በአውሮፓ ተቀባይነቱ እንደ እሲያ ሰፊ ባይሆንም ተጽእኖው ቀላል ነው ማለት አይቻልም።
በዚህ ዘመን ስፍር ቁጥር የሌላቸው ቪዲዮዎች በኮከብ ቆጠራ ዙሪያ ተወዳጅ ይዘቶችን ይፈበርካሉ፤ በየዕለቱ፣ በየደቂቃው።
በተለይ ከሰሜን አሜሪካ የሚሰናዱ በርካታ ይዘቶች ተመልካቾቻቸውን በጂኦፖለቲክስ፣ በስፖርት፣ በዓለም አቀፍ ጉዳዮች የኮከብ ቆጠራን መሠረት ባደረገ ትንታኔ ያጠግባሉ።
ለትንታኔያቸው ሰፋፊ እና የሚያማምሩ ካርታዎችን ይጠቀማሉ። ካርታዎቹ የሚያሳዩት የፀሐይን፣ የጨረቃን እና የከዋክብትን አሰላለፍ/አቀማመጥ ነው።
ዕጣ ፈንታ የሚወሰነው በእነዚህ የሰማያት ዓለማት አሰላለፍ እና በትወልድ ቀን ነው።
ለምሳሌ ስለፖለቲካ ሲተነትኑ ኢራን እና አሜሪካ ሲመሠረቱ የነበረውን የከዋክብት አሰላልፍን መሠረት ያደርጉና በሁለቱ አገራት መካከል ሊኖር የሚችለውን የጦርነት ስጋት በሰፊው ያብራራሉ።
"ዶናልድ ትራምፕ ከኢራን ጋር የዩራነስ መስመር ነው ያላቸው፤ ይህ ደግሞ አደገኛ ነው" ይላል አንድ አሜሪካ በኢራን ላይ ዘመቻ በከፈተች ማግስት የተለቀቀ ተንቀሳቃሽ ምሥል።
ሌላ በተመሳሳይ ቀን የተለቀቀ ተንቀሳቃሽ ምሥል ደግሞ ኢራን ከባድ የአጸፋ ምላሽ እንደምትሰጥ ያብራራል።
ነገር ግን ኢራን ከባድ የአጸፋ ምላሽ አልሰጠችም።
ተንቢቶቹ ስህተት ሆነው መገኘታቸው ታዲያ የኮከብ ቆጠራን መታመን አይቀንሰውም። ሕይወት ይቀጥላል። ከዋክብትም እንዲሁ።
ኮከብ ቆጣሪዎቹ ትንቢት ሲስቱ ኮከብ ቆጠራን የሚሹ ሰዎች እንዲያውም ቁጥራቸው በተቃራኒው እየጨመረ ነው የመጣው።
ባለፉት አምስት ዓመታት የጉጉል ማሰሻ "አስትሮሎጂ'' እና ''ጦርነት" የሚሉ ቃላት ፈላጊዎች በብዙ እጥፍ መጨመራቸውን ይፋ አድርጓል።
በተለይ የኮቪድ ወረርሽን ዘመን ከፍተኛ ቁጥር ያለው ሰው በኮከብ ቆጠራ ዙሪያ ሸብረክ እንዲል አድርጎ ነበር።
ከኮቪድ ወዲህ ደግሞ ጦርነቶች ሲቀሰቀሱ ሰዎች ሮጠው ኮከብ ቆጠራን ይበረብራሉ።
ለምሳሌ በአውሮፓውያኑ የካቲት 2022 በሩሲያ እና በዩክሬን መካከል ጦርነት ሲቀሰቀስ፣ ከዚያ ወዲህ ደግሞ ባለፈው ግንቦት ሕንድ እና ፓኪስታን በካሽሚር ግጭት ሲጀምሩ ሚሊዮኖች ወደ ኮከብ ቆጠራ ዘርፍ ጎርፈዋል።
ባለፈው ሰኔ አሜሪካ ኢራን ላይ ከባድ ጥቃት ስትፈጽም እንዲሁ ከፍተኛ ሕዝብ ወደ ኮከብ ቆጣሪዎች ፊቱን አዙሮ ነበር።
በለንደን ነዋሪ የሆነች አንድ ኢራናዊት ለቢቢሲ እንደተናገረችው በቴህራን ላይ ቦምቦች መዝነብ ሲጀምሩ ቀድማ ያደረገችው ነገር ቢኖር ኮከብ ቆጣሪዋን ማግኘት እና ማማክር ነበር።
እህቷም ተመሳሳይ ነገር እንዳደረገች ትናገራለች።
በጉጉል በይነ መረብ ''አስትሮሎጂ'' እና ''ጦርነት'' የሚሉ ቁልፍ ቃላት ሲደጋገሙ ፈላጊዎቹ ከየትኛው የዓለም ክፍል እንደሆኑ ለማየት ተሞክሮ ነበር። ሕንድ እና ሰሜን አሜሪካ መሆናቸው ተደርሶበታል።
በካናዳ ዎተርሉ ዩኒቨርሰቲ የሥነ ባሕል እና ማኅበረሰብ አጥኚ የሆኑት ዶክተር ጋለን ዋትስ፣ አስትሮሎጂን ለውስብስብ የዓለም አቀፍ ፖለቲካ ትንታኔ መጠቀም "የማይመስል ነገር ነው" ይላሉ።
እርሳቸው እንደሚሉት በዚህ ረገድ አስትሮሎጂ ትክክል ስለመተንበዩ እስከዛሬ አንድም አስታማማኝ መረጃ አልተገኘም።
በኒው ዮርክ የምትኖረው የኮከብ ቆጠራ ባለሙያ አሊዛ ኬሊ በዘርፉ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ብዙ ሰዎች ከፍተኛ ፍላጎት እያሳዩ መምጣታቸውን ትናገራለች። ነገር ግን የሙያው ሥነ ምግባር እየተጣሰ መምጣቱ ከሁሉ በላይ ያበሳጫታል።
በተለይ በማኅበራዊ ሚዲያ መድረኮች ላይ ማንም ቁንጽል ዕውቀት ይዞ እየተነሳ አስትሮሎጂን እየተነተነ መሆኑ "ሥነ ምግባር የጎደለው" ተግባር ሆኖ ይታያታል።
"የኒውክሊየር ጦርነት ይነሳል ወይ? 3ኛው የዓለም ጦርነት ሊቀሰቀስ ይችላል? ለሚል ጠጣር ጥያቄ በ90 ሰከንድ የቲክቶክ ቪዲዮ መልስ መመለስ የሙያው ሥነ ምግባር አይደለም" ትላለች፤ አሊዛ በስጨት ብላ።
"እንዲህ ዓይነት ቪዲዮዎች ብዙ ተመልካች ያገኛሉ፤ ምክንያቱም ስሜት ቀስቃሽ ስለሆኑ፤ እኛ ባለሙያዎች ግን ኮከብ ቆጠራ እንደርሱ እንዳልሆነ እንመክራለን።"
አሊዛ በአውሮፓውያኑ 2016 የአሜሪካ ምርጫ ወቅት በርካታ ሰዎች ውጤቱን ለማወቅ ወደ ኮከብ ቆጠራ እንደተሳቡ አስተውላለች።
ባልተጠበቀ ሁኔታ ዶናልድ ትራምፕ ሂላሪ ክሊንተንን ሲያሸንፉ፤ ያለውን ሁኔታ ባለመረዳት ምንድነው እየሆነ ያለው ለማለት ብዙ ሰዎች ጥያቄ ይዘው ወደ እርሷ ጎረፉ።
"ያን ጊዜ ነው ሰዎች ግራ የገባቸውን ነገር በተጨባጭ በኮከብ ቆጠራ ሊረዱት ሲሞክሩ ያስተዋልኩት" ትላለች።
ሰዎች ያልጠበቁት ነገር ሲገጥማቸው ፊታቸውን ወደ ኮከብ ቆጠራ ዘርፍ ማዞራቸው የተለመደ ነው።
የኮቪድ ወረርሽኝ ዓለምን ሲንጥ ብዙ ሰዎች "ልንጠፋ ይሆን?" ብለው ተጨንቀው ነበር። ያን ሰሞን ሚሊዮኖች ወደ ኮከብ ቆጠራ ፊታቸውን ያዞሩበት ነበር።
ካሲ ሌቨንታል አስትሮሎጂን መመልከት የጀመረችው በኮቪድ ወረርሽኝ ጊዜ ነበር። ወላጆቿ ሁለቱም የካንሰር ታማሚዎች ነበሩ።
ሕክምና ላይ ለነበሩት ወላጆቿ በዋናነት ምክር ትሰጣቸው የነበረው ከሐኪሞች ባገኘችው መረጃ ሳይሆን የከዋክብት እና የፕላኔቶችን አቀማመጥ በመመልከት ነበር።
እርግጥ የሐኪም ምክርንም ቸል አትልም። ነገር ግን ወደ አስትሮሎጂው ታመዝን ነበር።
አስትሮሎጂ ሳይንስ እንዳልሆነ ሲነገራት ያን እንደማትክድ፤ ሆኖም ግን ለነገሮች ጥልቀት እና ግራ ለሚያጋቡ ነገሮች ምላሽ ለማግኘት አስትሮሎጂ ወሳኝ መሆኑን ትሞግታለች።
ለምሳሌ ስለ ዶናልድ ትራምፕ ጥልቅ ማብራሪያ ስትሰጥ እንዲህ ትላለች፦
"ትራምፕ በመሬት ትይዩ የሆነ ፕላኔት የለውም፤ ጨረቃው (የስሜታዊ ትርጉም መስጫ) ሳጂታሪየስ ነው። የእሳት ምልክት አለው። ይህ ማለት ምን ማለት ነው? ሰውየው በባህሪው ግልፍተኛ እና ስሜታዊ ነው።"
አስትሮሎጂ ሃይማኖታዊ ነው መንፈሳዊ?
ዶክተር ዋትስ እንደሚሉት ኮከብ ቆጠራ ሃይማኖታዊ እና መንፈሳዊ መልክ አለው ብሎ ለመደምደም አስቸጋሪ ነው።
"ሆሮስኮፕን የሚመለከቱ ሰዎች ቢያንስ አንድ ከእነርሱ ገዘፍ ያለ ኃይል ስለ ሕይወታቸው ዕጣ ፈንታ የማመላከት አቅም እንዳለው ያመኑ ናቸው።"
ይሁንና አስትሮሎጂ በተለያየ ዓለም ብዙ ገጽታ አለው።
በሕንድ ለምሳሌ አስትሮሎጂ በቁም ነገር የሚታይ ነው። አተረጓጎሙም ቀጥታ እና በመታመን ነው።
ከጋብቻ በፊት ኮከብ ቆጠራ ተደርጎ እጮኛማቾቹ ይጣጣሙ እንደሆኑ ይመረመራል። አንዳንድ ቤተሰብ ኮከብ ቆጥሮ ጋብቻን ያጸድቃል ወይም ያፈርሳል።
ዶክተር ዋትስ እንደሚሉት በምዕራቡ ዓለም ሰዎች ከሕንድ በተለይ ኮከብ ቆጠራን እንደ አመቺነቱ ነው የሚጠቀሙበት።
"ምዕራባውያን ኮከብ ቆጣሪ ጋር ሲሄዱ እንደ አመቺነቱ ሁኔታዎችን ለማጤን ነው። የሞት ሽረት ጉዳይ አያደርጉትም፤ ትንታኔውን ደስ ካላቸው ሊቀበሉትም ካልሆነም ቸል ሊሉት ይችላሉ። ብዙም አያከ'ሩም።"
በቅርብ ጊዜ የተደረገ አንድ የዳሰሳ ጥናት በአሜሪካ 27 ከመቶ የሚሆነው ሕዝብ በኮከብ ቆጠራ እንደሚያምን አመላክቷል።
ዶክተር ዋት የኮከብ ቆጠራ በምዕራቡ ዓለም እየተስፋፋ ለመምጣቱ አንድ መላምት አላቸው።
በተለይ የዶናልድ ትራምፕ ወደ ሥልጣን መምጣት እና ያልተጠበቁ ነገሮች መከሰት ሰዎችን ወደ አስትሮሎጂ ሳይገፋፋቸው አልቀረም።
አሁንም ጥያቄው ለምን ብዙ ሰዎች በዚህ ዘመን ወደ ኮከብ ቆጠራ ትንቢት ተመለሱ? የሚለው ነው።
የዶክተር ዋትስ ምላሽ አጭር ነው፡-
"አንደኛ አዝናኝ ነው፤ ሁለተኛ በዚህ አሰልቺ፣ ግራ አጋቢ እና አስጨናቂ በሆነ ዘመን ቀላል ምላሽ ይሰጠናል። 'ቀላል' የሚለው ይሰመርበት።"