ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ስምረት ፓርቲ "ኋላቀሩ" ቡድን "ከባድ መሣሪያዎችን ወደ አማራ እና አፋር ክልሎች እያስጠጋ ነው" አለ
በጠቅላይ ሚኒስትሩ የምሥራቅ አፍሪካ ጉዳዮች አማካሪ ጌታቸው ረዳ የሚመራው ተቃዋሚው ፓርቲ ዴሞክራሲያዊ ስምረት ትግራይ (ስምረት)፤ "ኋላቀር ቡድን" ሲል የጠራው አካል "የአፋር ክልል እና ጎንደርን የሚያካልል መጠነ-ሰፊ ጥቃት" ለማካሄድ የሚያደርገውን "ዝግጅት ጨርሶ ተኩስ" ከፍቷል ሲል ወነጀለ።
ቡድኑ "ከባድ መሳሪያዎችን ከቀበረበት እና ከደበቀበት በማውጣት ወደ አማራ እና አፋር ክልሎች እያስጠጋ" ነው ያለው ስምረት፤ የፕሪቶሪያ ስምምነትን "በይፋ አፍርሶታል" ሲልም ከስሷል።
ከህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) ተነጥለው በወጡ ከፍተኛ የቀድሞ የትግራይ አመራሮች የተመሠረተው ስምረት፤ ይህንን መግለጫ ያወጣው የመከላከያ ሠራዊት እና የትግራይ ኃይሎች ግጭት ውስጥ መግባታቸው ከተዘገበ በኋላ ነው።
የዜና ወኪሎቹ ኤኤፍፒ እና ሮይተርስ የአማራ እና የትግራይ ክልሎች በይገባኛል በሚወዛገቡበት ጸለምት አካባቢ በኢትዮጵያ መንግሥት እና በትግራይ ኃይሎች መካከል ግጭት መካሄዱን የደኅንነት እና የዲፕሎማቲክ ምንጮችን በመጥቀስ ዘግበዋል።
ስምረት ሐሙስ ጥር 21/2018 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ ጸለምት ላይ ግጭት መካሄዱን ጠቁሟል። ተቃዋሚው ፓርቲ በአካባቢው ለተካሄደው ወታደራዊ እንቅስቃሴ ተጠያቂ ያደረገው "ኃላቀር እና የወንጀል ቡድን" ሲል የጠራውን አካል ነው።
የፓርቲው ፕሬዝዳንት የሆኑት አቶ ጌታቸው ከዚህ ቀደም ባደረጓቸው ንግግሮች አጋሮቻቸው የነበሩትን የህወሓት አመራሮች በዚህ ስያሜ ሲጠሩ ቆይተዋል።
ፓርቲው በመግለጫው ይህ ቡድን "የፕሪቶሪያውን የሰላም ስምምነት በመጣስ የሕዝባችንን ደኅንነት ወደ አደጋ የሚከት የጦርነት ዘመቻ ጀምሯል" ብሏል። ቡድኑ ይህንን እያደረገ ያለው "የግዛት አንድነትን እና የተፈናቃዮችን ጉዳይ" በምክንያትንት በማንሳት እንደሆነ በመጥቀስም ወቅሷል።
"ይህ ቡድን ከሻዕቢያ የተሰጠውን ተልዕኮ በመቀበል ለትግራይ ግዛታዊ አንድነት ምንም ትርጉም የሌለው፣ እስከ አፋር ክልል እና ጎንደር የሚያክልል፣ መጠነ ሰፊ ጥቃት ለማካሄድ ዝጅግቶቹን ጨርሶ ለሕዝብ በቅጡ ሳይናገር የኃይል እንቅስቃሴ እና ተኩስ እያደረገ ነው" ብሏል።
"ቀደም ብሎ የቀበራቸው እና የደበቃቸው ከባድ መሣሪያዎችን ከቀበረበት እና ከደበቀበት በማውጣት ወደ አማራ እና አፋር ክልሎች እያስጠጋ ይገኛል" ሲልም ከስሷል።
ይህ ወታደራዊ እንቅስቃሴ እየተከናወነ ያለው "ሕግን እና ሥርዓትን በመርገጥ" እንዲሁም "የፕሪቶሪያውን ውል ሙሉ በሙሉ በማፍረስ" እንደሆነም በመግለጫው አስፍሯል። ቡድኑ ይህንን "የዘፈቀደ ጦርነት" እየመራ ያለው "ከሻዕቢያ ሥርዓት ጋር ተሰልፎ" ነው ሲልም ከስሷል።
ስምረት "በተጎዱ የትግራይ ሠራዊት አባላት ስም በማመካኘት ገንዘብ ሲሰበስብ እና ሁለገብ ዝግጅት ሲያካሂድ" ነበር ሲልም ቡድኑን ወንጅሏል።
"በዚህ ሳምንት በጸለምቲ አቅጣጫ የጀመረውን ጦርነት ጫሪነት የድሃ ልጆች የሆኑ ወጣቶች የጥይት እራት አድርጎ ታሪክ ይቅር የማይለው ስህተት ሲፈጽም ታይቷል" ሲልም በአማራ እና በትግራይ አዋሳኝ አካባቢ ወታደራዊ እንቅስቃሴ እንደነበር አመልክቷል።
"የትግራይ የግዛት ወሰን ማስከበር እና የተፈናቃዮቻችን ደኅንነቱ በተጠበቀ መንገድ መመለስ" አስፈላጊ መሆኑን የጠቀሰው ስምረት፤ ይህ ግን በሰላማዊ እና በሕጋዊ መንገድ በፕሪቶሪያው ውል መሠረት የሚፈጸም እንጂ በጦርነት እና በጦርነት ዛቻ የሚመለስ አይደለም" ሲል አቋሙን አሳውቋል።
ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ የፕሪቶሪያ ስምምነት እንዲፈጸም "ሁለንተናዊ ጫና እንዲያሳድር" እንዲሁም ይህ ቡድን "ከትግራይ ሕዝብ ጫንቃ ላይ እንዲወርድ እንዲተባበር" ጥሪ አቅርቧል።
የትግራይ ሕዝብ "እየተካሄደ ያለውን አደገኛ የውጭ ኃይሎች ጦርነት በጥብቅ እንዲያወግዝ" እንዲሁም "ሠራዊት ውስጥ ያሉ ልጆቹን እንዲመክር" ጠይቋል።
ባለፉት ቀናት በፌደራል መንግሥት እና በትግራይ ኃይሎች መካከል ግጭቶች መካሄዳቸውን የሚጠቁሙ መረጃዎች ቢወጡም እስካሁን ድረስ በሁሉቱም በኩል የተሰጠ ይፋዊ ማረጋገጫም ሆነ ማብራሪያ የለም።