እንጀራ እና ዳቦ ከመሆን አልፎ ለወተትነት መታለብ የጀመረው ጤፍ

ለኢትዮጵያውያን ዋነኛ የምግብ ምንጫቸው የሆነው ጤፍ የሺዎች ዓመታት ታሪክ እንዳለው ይነገራል።

ይህ አካሉ የደቀቀ የገለባ እህል ለዘመናት በዋነኛነት በእንጀራ እና በዳቦ መልክ ለምግብነት ሲውል ቆይቷል።

ነጭ፣ ቀይ፣ ሰርገኛ እየተባለ ባለው ቀለም የሚለየው ጤፍ በተወሰነ መልኩም ቢሆን መልኩን እና ቅርጹን ለውጦ በዓለም አቀፍ ደረጃ ወደ ገበያ መውጣት የጀመረው ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ነው።

ጤፍ ከእንጀራነት ባሻገር በኮርንፍሌክስ፣ በኬክ፣ በዳቦ ቆሎ እና በሌሎች ደረቅ ምግቦች መልክ አሽጎ ማቅረብ እየተለመደ መጥቷል። አሁን ደግሞ ለወተትነት መታለብ ጀምሯል።

የወተት አምራች ድርጅቱ 'ዘ ኦሪጂናል ቴፍሊ ሊሚትድ' መሥራቾች አንዱ የሆኑት እና የድርጅቱ ዋና ዳይሬክተር ዮሴፍ ብርሃነ የጤፍ ወተቱ "በዓለማችን የመጀመሪያው ነው" ብለዋል።

ምርቱ 'ቴፍሊ' በሚል መለያ ልክ እንደ አኩሪ አተር እና ኮከናት ወተት ሁሉ ከእፅዋት የተሠራ የወተት ምርት ሆኖ በመመዝገብ ገበያ ላይ ውሏል።

ሃሳቡ እንዴት ተወለደ?

የድርጅቱ ዋና ዳይሬክተር ዮሴፍ እንዳሉት ሃሳቡ በአንድ ጊዜ የመጣ አልነበረም።ብዙ ሲብላላ የቆየ ነው። የሃሳቡ ዋነኛ መነሻ ይህን "ትውልድ እና ዕድገቱ በኢትዮጵያ የሆነውን" ጠቃሚ የእህል ዘር እንዴት ለሁለት እና ለሦስት ሺህ ዓመታት በእንጀራ ብቻ እንመገበዋለን የሚል ነው።

ጤፍ በውስጡ የያዘው ንጥረ ነገር፣ የእፅዋት ተዋፅኦ ብቻ የሆኑ ምግቦች የሚመገቡ ሰዎች (ቬጋኖች) መበራከት እና በተለይ ለአንጀት ጤና ያለው ጠቀሜታ ከፍ ያለ ሆኖ መገኘቱ የፈጠራ ሃሳባቸውን ይበልጥ እንዲጎለብት አድርጎታል።

ከዚህም ባሻገር "ከጤፍ ጋር ተያይዞ ያለው የተሳሳተ ትርክት እና ወደፊት ያለውን ተግዳሮት ስናስብ አንድ ነገር ለማድረግ ወሰንን" ይላሉ አቶ ዮሴፍ።

"ጤፍ ያለምንም ፈጠራ በተለመደው መልኩ ከትውልድ ትውልድ እየተላለፈ ነው የመጣው" የሚሉት አቶ ዮሴፍ፣ አዲስ ሃሳብ ይዞ በመምጣት ለትውልድ ማቀበልንም አብዝተው ሲያስቡበት እንደቆዩ ገልጸዋል።

ከሌሎች የእህል ዘሮች ጋር ሲነፃፀር ከሥነ ምግብ ይዘቱ፣ ለአንጀት ጤና ተስማሚነቱ፣ ከግሉቲን ነፃ መሆኑ ጤፍን ለየት እንደሚያደርገውም አስረድተዋል።

ገበያ ላይ የሚገኙት እንደ አልመንድ፣ ሶያ፣ ኮኮናት ያሉ ከእፅዋት የሚዘጋጁ ወተቶች ከጤና እንዲሁም ከአመጋገብ ምርጫ አንፃር ተመራጭ እየሆኑ መምጣታቸውም ከትውልድ አገራቸው ሃብት [ጤፍ] ወተትን ለማለብ እንዳነሳሳቸው ዋና ዳይሬክተሩ ገልጸዋል።

የምንወደው እንጀራ እናት - ጤፍ

ከዓመታት በፊት የወጣ እና በዓለም አቀፉ የምግብ ፖሊሲ ጥናት ተቋም የታተመ አንድ ጥናት ጤፍን ከምግብ ሳይንስ አኳያ ያለውን የጤና ጥቅም ቃኝቷል።

ጥናቱን ያካሄዱት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የምግብ ሳይንስ እና ሥነ ምግብ ማዕከል ፕሮፌሰር ቃለአብ ባዬ ናቸው።

ፕሮፌሰር ቃለአብ ጤፍ ባለፉት ጥቂት ዘመናት በደቡብ አፍሪካ፣ በሕንድ፣ በኤርትራ እና በኢትዮጵያ ቢመረትም ለሰው ልጆች በምግብነት መዋል የጀመረው በኢትዮጵያ እና በኤርትራ ብቻ እንደነበር ጠቅሰዋል። ሆኖም ባለው የምግብ ይዘት ምክንያት በመላው ዓለም ተፈላጊነቱ እየጨመረ መጥቷል ብለዋል።

ጤፍ ያለው ጠቀሜታ በበቂ ሁኔታ ባይጠናም ብዙ ያልተነገረለት ጠቃሚ የምግብ ምንጭ እንደሆነም በጥናታቸው ላይ አስፍረዋል።

"ኢትዮጵያውያን የቀጨጩት እንጀራ ስለሚበሉ ነው" ተብሎ የጤፍን ጥቅም እስከማቃለል ተደርሶ እንደነበር የሚያወሱት ፕሮፌሰር ቃለአብ፤ ጤፍ በውስጡ በበርካታ ንጥረ ነገሮች እና ሚኒራሎች የበለፀገ እንደሆነ አስረድተዋል።

ጤፍ ካርቦሃይድሬት፣ አይረን/ብረት፣ ፕሮቲን፣ ከስንዴ እና ከሩዝ የተሻለ ስብ (ፋቲ አሲድ)፣ ሚኒራል፣ ካልሺየም እና ፋይበርን (አሰር) ጨምሮ በርካታ ንጥረ ነገሮችን እንደያዘ የፕሮፌሰር ቃለአብ ጥናት ያመለክታል።

የጤፍ ተፈጥሯዊ አፈጣጠሩ ያለውን የሥነ ምግብ ይዘት ጠብቆ ለመቆየት እንደረዳውም ሌሎች የዘርፉ ባለሙያዎች ይናገራሉ።

አንድ የጤፍ ፍሬ መጠን 1 ሚሊ ሜትር ሲሆን፣ ማነሱ እንደ ስንዴ ወይም መሰል እህሎች የላይኛውን ሽፋን ለማስወገድ ወይም ለመፈተግ የማይመች ያደርገዋል። ይህ የጤፍ የመጀመሪያ ጥቅም ነው ይላሉ ባለሙያዎቹ።

ጤፍ ከግሉቲን ነጻ በመሆኑም ለጤና ተስማሚ ነው።

ስንዴን ጨምሮ የተለያዩ ምግቦች በውስጣቸው በያዙት ግሉቲን የተሰኘ ንጥረ ነገር ምክንያት የአንጀት ቁስለት፣ የሆድ ሕመም እና በአየር መሞላት፣ ድርቀት፣ ምቾት ማጣት እና መሰል የጤና እክሎች የሚያጋጥማቸው ሰዎች አሉ።

በመሆኑም ጤፍ በተለይ በዚህ የጤና እክል ለሚቸገሩት በኖርዲክ (በሰሜን ዋልታ አካባቢ ያሉ) አገራት ለሚኖሩ ሰዎች ምቹ ነው።

በዚህም ምክንያት ጤፍ ቀጣዩ የዓለማችን ተፈላጊ ምግብ ሊሆን ይችላል የሚሉ መላ ምቶች እየጨመሩ መጥተዋል።

'ዘ ኦሪጂናል ቴፍሊ' ዳይሬክተር አቶ ዮሴፍ ጤፍ ከያዘው ንጥረ ነገር በተጨማሪ በኢትዮጵያ ከተለመደው ውጭ በተለያየ መልኩ መቅረቡ የሚያበረክተው አስተዋፅኦ ዘርፈ ብዙ ነው ይላሉ።

አሁን ላይ በተለያዩ አገራት የሚመረተው ጤፍ ተፈላጊነቱ እየጨመረ በመምጣቱ የኢትዮጵያ ዋነኛ ምግብ የሆነውን ዘር ለመቆጣጠር ከሚቋምጡት ለማስጣልም የወተት ምርቱ ወሳኝ እርምጃ እንደሆነ ገልጸዋል።

"ለሚቀጥለው ትውልድ ኃላፊነታችንን በመወጣት እነርሱ ደግሞ የተሻለ ነገር አድርገው ማስቀጠል የሚችሉበትን ዕድል እንዴት እንፍጠር በሚል የተነሳው ሃሳብ ነው ወደ ወተትነት የተሸጋገረው" ብለዋል።

አሁን በዚህ እሳቤ ተጠንስሶ እውን የሆነው የጤፍ ወተት የሚመረተው በዩናይትድ ኪንግደም ሲሆን፣ እዚያው ገበያ ላይ ውሏል።

እንደ አቶ ዮሴፍ ገለጻ አሁን ላይ በድርጅቱ ተመርተው ገበያ ላይ የዋሉት አራት ዓይነት ምርቶች ናቸው።

እነዚህ ምርቶች ስኳር ያልተጨመረበት፣ 'ባሬስተር ኤዲሽን' የሚባል ከቡና ዘርፍ ጋር የተገናኘ እንደ ማኪያቶ ያሉ ትኩስ መጠጦችን ለማዘጋጀት የሚውል፣ ቫኒላ ጣዕም ያለው እና በጃፓኖች ዘንድ ተወዳጅነት እንዳለው 'ማቻ ላቴ' በተለይ በበጋ ወቅት ከቡና እና ከበረዶ ጋር ተደርጎ የሚጠጣ ወተት እና በቼኮሌት ጣዕም ለልጆች የተዘጋጁ ናቸው።

ወዲያውኑ እንዲጠጣ ተደርጎ የሚዘጋጀው ሌላኛው ዓይነት ምርትም በሚቀጥሉት ሦስት ወራት ገበያ ላይ ይውላል ተብሎ እንደሚጠበቅ ዳይሬክተሩ አክለዋል።

የወተት ምርት ሒደቱን ወደ ኢትዮጵያ ለማሸጋገር ዕቅድ እንዳለም ተጠቁሟል።ምርቱም ወደ ሌሎች አገራት ተደራሽ ይሆናል ተብሎም ይጠበቃል።

ዩናይትድ ኪንግደምን ጨምሮ በሌሎች አገራት ከእፅዋት የሚዘጋጅ ወተት ገበያ በፍጥነት እያደገ እንደሆነ ጥናቶች ያመለክታሉ።

ሚንትል የተባለው የገበያ ጥናት ተቋም በአውሮፓውያኑ 2019 ባካሄደው ጥናት አንድ ሦስተኛ የሚሆነው የዩናይትድ ኪንግደም ሕዝብ የሚጠጣው የእንስሳት ተዋፅኦ ያልሆኑ የወተት ምርቶችን እንደሆነ ማወቅ ችሏል።

ከእፅዋት የሚዘጋጁ ወተቶች ዘርፍ በዓለም በዓመት ከ20 ቢሊዮን ዶላር በላይ የገበያ ዋጋ አለው።

የጤፍ ወተት ከምግብነት ባሻገር . . .

ጤፍ በሌሎች አገራት ውስጥ መመረቱ ባይካድም "ኢትዮጵያዊ ታሪክ እና ቅርስ ያለው ነው" የሚሉት ዮሴፍ፣ የወተት ምርቱ በኢትዮጵያ በግብርናው፣ በቴክኖሎጂ፣ በሥራ ፈጠራ እና በውጭ ምንዛሬ ረገድ ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንደሚያደርግ ይናገራሉ።

"እንደ ድርጅት ወደ አገር ቤት ገብተን ማረሳችን ምርታማነትን ይጨምራል። ማምረቻ ድርጅት ስንከፍት የሥራ ዕድልን እንፈጥራለን። አርሶ አደሮችን ከማገዝ አንፃር የቴክኖሎጂ ሽግግርን ማሻሻል እንችላለን። ለአገሪቷም የውጭ ምንዛሪ ያስገኛል" ብለዋል።

ከዚህ ባሻገር መጪው ትውልድ ከእንጀራ ውጭ ለየት ያለን ሃሳብ እንዲያመጣ እና ያለውን አገራዊ ሃብት እንዲጠቀም በር እንደከፈተም ተናግረዋል።

"ጤፍ የኢትዮጵያ ሃብት ነው" የሚል አቋም ያላቸው አቶ ዮሴፍ፣ በምርቶቻቸው ማሸጊያ ላይ ሙሉ በሙሉ ኢትዮጵያን የሚያንፀባርቅ ዲዛይን መጠቀማቸውንም ተናግረዋል።

የወተት ምርቱ በለንደን በሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ በተካሄደ ዝግጅት በተዋወቀበት ወቅት አምባሳደር ብሩክ መኮንን፣ ጤፍ በኢትዮጵያውያን የአመጋገብ ሥርዓት እና የአየር ንብረት ለውጥን መቋቋም በሚችሉ የምግብ ሥርዓቶች ላይ ለሚደረጉ ጥናቶች አስተዋፅኦ እንደሚያበረክት መናገራቸው ተገልጿል።

ከእፅዋት የተዘጋጁ ወተቶች ታሪካዊ ዳራ

ከእፅዋት የተዘጋጁ ወተቶች በዓይነት እና በብዛት በየሱፐር ማርኬቱ መደርደሪያ ላይ ተሰድረው ማየት እየተለመደ መጥቷል።

እንደ ሶያ፣ አልመንድ፣ ኮኮናት፣ አጃ እና የአኩሪ አተር ወተት በተለይ የእንስሳት ተዋፅኦ በማይመገቡ እና በክርስትና እምነት ተከታዮች ዘንድ በፆም ወቅት ተመራጭ እየሆኑ ነው።

እነዚህን ከእፅዋት ተዋፅኦ የሚዘጋጁ ወተቶችን መጠቀም የመቶ ሺዎች ዓመታት ታሪክ ያለው ነው።

ከአምስት ሺህ ዓመታት በፊት ሰዎች የኮኮናት ፍሬን በመሰንጠቅ ተፈጥሯዊ ፈሳሹን ከመጠጣት ባለፈ በውስጡ ያለውን ሥጋ በመፈቅፈቅ እና ከውሃ ጋር በመቀላቀል ወተት ያዘጋጁ እንደነበር ይነገራል።

ይህ ልምድ እንደ ማዳጋስካር፣ ደቡብ ምሥራቅ እስያ እና ውቅያኖስ ላይ በሚገኙ ደሴቶች የሚኖሩ ሰዎች የፈጠሩት እንደሆነ ይታሰባል።

በስፋት ጥቅም ላይ መዋል የጀመረው ግን ከ2 ሺህ ዓመታት በፊት ነው። በተለይ በሕንድ እና በደቡብ ምሥራቅ እስያ አሁንም ድረስ ከመጠጥነት አልፎ ምግብ ለማብሰል ጥቅም ላይ ይውላል።

የአልመንድ ወተት ደግሞ የመቶ ዓመታት ታሪክ ያለው ሲሆን፣ ከሶያ ወተት ጋር ተቀራራቢ ዕድሜ አለው።

የሶያ ወተት ከላም ወተት በተሻለ በቀላሉ በሰውነት ውስጥ የሚዋሃድ በመሆኑ በ18ኛው ክፍለ ዘመን በቻይና መንገድ ላይ የሚሸጥ ታዋቂ ምግብ ነበር። ከዚያም በአውሮፓውያኑ 1910 በፈረንሳይ ፓሪስ የሶያ ወተት ፋብሪካ መገንባቱን ተከትሎ በብዛት መመረት ጀመረ።

በስዊዲናዊው የምግብ ተመራማሪ ሪካርድ ኦስተ የበለፀገው የአጃ ወተት ደግሞ ጥቅም ላይ መዋል የጀመረው በአውሮፓውያኑ 1990ዎቹ እንደሆነ ይነገራል።

ሌላኛው የአኩሪ አተር ወተት በአሜሪካ ገበያ ላይ የዋለው እንደ አውሮፓውያኑ በ2015 ሲሆን፣ የድንች ወተት ደግሞ በ2022 ገበያውን ተቀላቅሏል።

ጤፍ ጥንታዊ የእህል ዘር ቢሆንም በወተት መልክ "ለመጀመሪያ ጊዜ" በይፋ ለገበያ መቅረቡ የተገለፀው ጥር 6 ቀን 2018 ዓ.ም ነው።