ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ዩኤስኤስ አብርሀም ሊንከን፡ ወደ ኢራን እየተጠጋ ያለው ግዙፉ የአሜሪካ የጦር መርከብ ምን ይዟል?
የአሜሪካ ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ ኢራን ከአሜሪካ ጋር በአስቸኳይ ስምምነት ላይ ካልደረሰች ከአሜሪካ የሚገጥማት ቀጣዩ ጥቃት ከዚህ በፊት ከነበረው "በጣም የከፋ ይሆናል" ሲሉ አስጠንቅቀዋል።
ከጥቂት ሳምንታት በፊት በኢራን የተነሳውን ተቃውሞ ተከትሎ ትራምፕ ኢራን ላይ ጥቃት ሊፈፅሙ እንደሚችሉ ዝተዋል።
ትራምፕ ትሩዝ ሶሻል በተሰኘው ማኅበራዊ ገፃቸው ዩኤስኤስ አብርሀም ሊንከን የተሰኘው ግዙፍ የጦር መከርባቸው እና ሌሎች ኃይሎች ወደ ባሕረ-ሰላጤው መሰማራታቸውን አስታውቀዋል።
አስፈላጊ ሲሆን "በፍጥነት እና በአደገኛ ሁኔታ" የሚሰጣቸውን ተልዕኮ ለመፈጸም ዝግጁ መሆናቸውንም ጠቁመዋል።
ምንም እንኳ ይህ የአውሮፕላን ማረፊያ ያለው መርከብ ትክክለኛ አድራሻውን ከአንድ ሳምንት በላይ ይፋ ያላደረገ ቢሆንም አንድ አውሮፕላን ኦማን አካባቢ ሲያርፍ ፍላይራዳር24 በተባለው የአውሮፕላኖች መከታተያ ድረ-ገፅ በመታየቱ መርከቡ ኦማን አካባቢ እንዳለ ይገመታል።
ሌሎች ሦስት የጦር መርከቦችም ወደ መካከለኛው ምስራቅ ቢሰማሩም ዩኤስኤስ አብርሀም ግዙፉ ነው። ለመሆኑ ይህ የጦር መርከብ ምን ይዟል?
የአሜሪካ ማዕከላዊ ዕዝ በኤክስ ገፁ ዩኤስኤስ አብርሀም የጥቃት ቡድን "በአሁኑ ወቅት ቀጣናዊ ፀጥታ እና ደኅንነት ለማስጠበቅ መካከለኛው ምስራቅ ይገኛል" ሲል ፅፏል።
ዩኤስኤስ አብርሀም ሊንከን የኒውክሌር የጦር መሣሪያ ከያዙ የአሜሪካ የጦር መርከቦች አንዱ ሲሆን የአሜሪካ ባሕር ኃይል "የዓለማችን ትልቁ የጦር መከርብ" ሲል ይጠራዋል።
የአውሮፕላን ማኮብኮቢያ እና ማረፊያ ያለው ይህ መርከብ ኤፍ-35 እንዲሁም ኤፍ/ኤ-18 ሆርኔት የተሰኙት የጦር ጄቶችን እንደታቀፈ አሶሺየትድ ፕሬስ ዘግቧል።
ዩኤስኤስ አብርሀም ሊንከን እና ሦስቱ የጦር መርከቦች በሺዎች የሚቆጠሩ የአሜሪካ ወታደሮችን ይዘው ወደ መካከለኛው ምስራቅ እንደተሰማሩ ይነገራል።
መርከቡ የተለያዩ ሚሳዔሎች ሊኖሩት እንደሚችሉትም ይታመናል። ከእነዚህ መካከል የኔቶው ሲ ስፓሮው ፀረ-ሚሳዔል መሣሪያ ይጠቀሳል።
332 ሜትር የሚረዝመው ዩኤስኤስ አብርሀም ሊንከን ሌሎች የጦር መርከቦች ላይ ጥቃት መፈፀም የሚችሉ ፋላንኤክስ የጦር መሣሪያዎች ይይዛል።
ፋላንኤክስ በኮምፒውተር ቁጥጥር የሚደረግለት በራዳር የሚመራ የጦር መሣሪያ ነው።
መርከቡ ከዚህ አልፎ ራም የተባለው ሱፐርሶኒክ የሚሳኤል ሥርዓት እንደተገጠመለት ይታመናል።
ከአሜሪካ ግዙፍ የጦር መርከቦች መካከል አንዱ የሆነው ዩኤስኤስ አብርሀም ሊንከን ሌሎች በርካታ የጦር መሣሪያዎች እና የራዳር ሥርዓቶች የተገጠሙለት ነው።
AN/SLQ-25A Nixie የተባለው ቴክኖሎጂ የሚያወጣው ድምፅ መርከቡን ለመከታተል የሚመጡ ኃይሎች ሰርጓጆችን ለማታለል የተሠራ ነው።
የራዳር ሥርዓቶቹ ደግሞ በአቅራቢያው ያሉ ሁኔታዎችን ለመቃኘት፤ የአየር ትራፊክን ለመዳሰስ እና ሚሳዔሎች ዒላማቸውን ጠብቀው እንዲመቱ ለማድረግ ያግዛሉ።
ዩኤስኤስ አብርሀም ሊንከን በሰዓት 60 ኪሎ ሜትር እንደሚጓዝ እና በአማካይ እስከ 5600 ሰዎች እንደሚይዝ ሲኤምኤንኦ የተባለው የሀገራት የጦር ኃይል መረጃ የያዘ ገፅ ይጠቁማል።
አሜሪካ ኢራን ላይ ጥቃት ትፈፅም ይሆን?
የዓለማችን ቁጥር አንድ ወታደራዊ ኃይል ያላት አሜሪካ ኢራን ላይ ጥቃት መፈፀም እንደምትችል አሳይታለች።
የአሜሪካ አየር ኃይል ባለፈው ዓመት ሰኔ 'ሚድናይት ሀመር' በተሰኘ ኦፕሬሽን የኢራን ኒውክሌር ማብላያዎች ላይ ጥቃት መፈፀሙ ይታወሳል።
በወቅቱ ከ100 በላይ የጦር ጄቶች ተሰማርተው የነበረ ሲሆን ቢ-2 የተባለው ጄት ከአሜሪካ ተነስቶ 'ባንከር ባስተር' የተባለ ዒላማ ለይቶ የሚመታ ቦምብ ጥሎ ተመልሷል።
አሁን ጥያቄው አሜሪካ ኢራን ላይ ድጋሚ ጥቃት ልትሰነዝር ትችላለች ወይ? የሚለው ነው።
በቬንዙዌላ ላይ የወሰዱትን እርምጃ ያነሱት ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ፤ ኢራን "ጊዜው እየሄደባት እንደሆነ" እና የኒውክሌር መርሃ ግብሯን በተመለከተ በፍጥነት "ወደ ድርድር ጠረጴዛ" ትመጣለች ብለው ተስፋ እንደሚያደርጉ አመልክተዋል።
ቀደም ሲል "ወደ ድርድር መጥተው ከስምምነት እንዲደርሱ ነግሬያቸው ነበር፤ ነገር ግን አልመጡም" በማለት ባለፈው ሰኔ ወር ላይ የተፈጸመው የአየር ጥቃት መከተሉን ገልጸዋል።
አሜሪካ በመካከለኛው ምስራቅ ባሉ የጦር ካምፖች እስከ 50 ሺህ ገደማ ወታደሮች እና በርካታ የጦር መሣሪያዎች አሏት።
ከእነዚህ መካከል 10 ሺህ የሚሆኑት ኳታር በሚገኘው አል-ኡዴይድ የጦር አውሮፕላን ማረፊያ ጣቢያ ይገኛሉ። በተጨማሪ አሜሪካ በዮርዳኖስ፣ ሳዑዲ አራቢያ፣ ኦማን፣ ባሕሬይን እና የተባበሩት አረብ ኤሜሬቶች የጦር ሠፈሮች አሏት።
ባለፉት ጥቂት ሳምንታት አሜሪካ ወደ አካባቢው ተጨማሪ ኃይል እያሰማራች እንደሆነ የበይነ መረብ ምርመራዎች ያመለክታሉ።
ተንታኞች አሜሪካ በመካከለኛው ምስራቅ ያላትን ኃይል ማጠነከሯ እንዲሁም የዩኤስኤስ አብርሀም ሊንከን እና ሌሎች መከርቦች ወደ ሥፍራው መሰማራት ኢራን ላይ ጥቃት ሊኖር እንደሚችል ጠቋሚ ነው ይላሉ።