የፋኖ ኃይሎች በአንድ ድርጅት ሥር መሆን ድርድርን ያቀርባል ወይስ ውጊያን ያጠናክራል?

ከሁለት ዓመት ለተሻገረ ጊዜ በበርካታ የተለያዩ ዕዞች ስር ሆነው ከመንግሥት ጋር ሲዋጉ የቆዩት የፋኖ ኃይሎች፤ በመጨረሻም ወደ አንድ ድርጅት የመጡ ይመስላል።

በዘመነ ካሴ የሚመራው አማራ ፋኖ ብሔራዊ ኃይል (አፋብኃ) እና በእስክንድር ነጋ የሚመራው የአማራ ፋኖ ሕዝባዊ ድርጅት (አፋሕድ) ራሳቸውን "አክስመው" አንድ ታጣቂ ድርጅት መፍጠራቸውን ይፋ አድርገዋል።

"የአማራ ፋኖ ብሔራዊ ንቅናቄ (አፋብን)" የሚል ስያሜ የያዘው አዲሱ ድርጅት፤ "የመጨረሻዎቹ የፋኖ ኃይሎች ተዋህደው" የፈጠሩት እንደሆነ የድርጅቱ የሕዝብ ግንኙነት መምሪያ ኃላፊ ሆነው የተመደቡት አስረስ ማረ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

የፋኖ ኃይሎች አዲስ ድርጅት መመሥረታቸውን ይፋ ያደረጉት፤ ለበርካቶች ሞት እና በሚሊዮኖች ለሚቆጠሩ ሕጻናት ከትምህርት ውጪ መሆን ምክንያት የሆነው የአማራ ክልል ግጭት ወደ ሦስተኛ ዓመቱ እያመራ ባለበት ጊዜ ነው።

እንደ ካፒቴን ማስረሻ ሰጤ፣ ኮሎኔል ፈንታው ሙሀባው እና እያሱ አባተ ያሉ የአማራ ፋኖ ሕዝባዊ ድርጅት አመራሮችም የትጥቅ ትግልን በመተው ከመንግሥት ጋር ስምምነት የፈጸሙትም በዚሁ ሰሞን ነው።

መንግሥት የሰላም ንግግርን በተመለከተ በተለይም ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ አባላት በሚሰጣቸው ማብራሪያዎች ላይ የፋኖ ኃይሎች የተበታተነ ዕዝ ስር መሆንን እንደ አንድ እንቅፋት ሲጠቅስ ቆይቷል። አሁን የፋኖ ኃይሎች የአንድ ድርጅት ምሥረታ በመንግሥት በኩል ሲነሳ የቆየውን አንድ ተግዳሮት የሚያስወግድ ይመስላል።

በእርግጥ ግን የፋኖ ኃይሎች ወደ አንድ መምጣት የሰላም ንግግርን ያቀርባል? ወይስ የተገዳዳሪነት ስሜትን በማጠናከር ድርድር እንዲገፋ ያደርጋል?

ባልተማከለ ዕዝ የተመራ የትጥቅ እንቅስቃሴ

የዶክትሬት ዲግሪያቸውን በሰላም እና ደኅንነት ላይ የሠሩት ዶ/ር ዳንኤል (ስማቸው የተቀየረ)፤ የፋኖ ኃይሎች እንቅስቃሴ እና አወቃቀርን በተመለከተ የተለያዩ ጽሁፎችን አሳትመዋል። የፋኖ ኃይሎች ትጥቅ ትግል "የተለያዩ ቡድኖች 'የአማራ ጥያቄ ነው' ብለው የሚያስቡትን ይዘው፣ ከታች የተነሱበት እቅስቃሴ" እንደሆነ ያስረዳሉ።

በዚህም ምክንያት "በየቦታው በጣም ብዙ የተለያዩ ቡድኖች" እንደነበሩ የሚገልጹት ተመራማሪው፤ የታጣቂዎቹ የአመራር መስመር "ማዕከላዊ ዕዝ የሌለው" እንዲሁም "ያልተማከለ" እንደነበር አብራርተዋል።

አትርሳው ነጮ እና ያሬድ ደበበ የተባሉ አጥኚዎች የካቲት 2016 ዓ.ም. በሳተሙት አንድ ጽሁፍ፤ በክልሉ ዘጠኝ የተለያዩ የፋኖ ቡድኖች እንደሚንቀሳቀሱ አመልክተው ነበር። የእነዚህ ኃይሎች የእርስ በእርስ ግንኙነት "የላላ" እንደሆነ እንዲሁም "አብዛኞቹ አነስተኛ እና ራሳቸውን ችለው የሚንቀሳቀሱ" እንደሆኑ ጽፈዋል።

ይህንን ሀሳብ የሚጋሩት ዶ/ር ዳንኤል፤ " 'የአማራ ጥያቄ' በሚሉት ላይ ላይለያዩ ይችላሉ። ነገር ግን በአካሄዱ፣ በምን መንገድ ማስፈጸም እንችላለን፣ ምን ዓይነት የፖለቲካ እና ወታደራዊ ስትራቴጂ ይዘን ነው የምንሄደው የሚለው ላይ ይለያያሉ" ሲሉ በወቅቱ ስለነበሯቸው ልዩነቶች ያስረዳሉ።

ይህንን ዓይነቱን ቅርጽ የያዘ ትግል "የአማጺያን እንቅስቃሴ አንድ መገለጫ" እንደሆነ የሚያነሱት ዶ/ር ዳንኤል፤ በንድፈ ሀሳብ ደረጃ የራሱ ጥቅሞች እንዳሉትም ይገልጻሉ።

"ያልተማከለ በሆነ፣ የዕዝ ሰንሰለቱ የላላ በሆነ ቁጥር በማንኛው ሰዓት ያለማንም የበላይ ትዕዛዝ የራሳቸውን ወታደራዊ ኦፕሬሽን መሥራት ይችላሉ። በመንግሥት ዒላማ የመደረግ ዕድላቸውም በጣም ይቀንሳል፤ ምክንያቱም ብዙ ቦታዎች ላይ ነው ያሉት" በማለት ያብራራሉ።

በተቃራኒው ግን ይህ አካሄድ "አንድ አለመሆን" እንደሚያስከትል ያነሳሉ። እንደ ዶ/ር ዳንኤል ገለጻ፤ ቡድኖቹ አንድነት ከሌላቸው "በድርድር የሚመጣ የሰላም መፍትሔን ለማስፈጸም በጣም ከባድ" ይሆናል።

"ፍላጎቶቻቸው እና ጥቅሞቻቸው በግልጽ የተብራሩ እንዳይሆኑ" እንደሚያደርግም ያክላሉ። ይህም "ቀውስ እንዲበዛ" እንዲሁም እንቅስቃሴው "እንዲጠለፍ" ምክንያት እንደሚሆን አስረድተዋል።

የፋኖ ኃይሎች "ለመዋሃድ" ለምን ረጅም ጊዜ ወሰደባቸው?

የፋኖ ኃይሎች የተበታተነ ዕዛቸውን በአንድ መዋቅር ስር ለማድረግ በተለያዩ ጊዜያት ድርድሮችን ማካሄዳቸውን ሲገልጹ ቆይተዋል። እነዚህ ሂደቶች የተሳኩባቸው አጋጣሚዎች ቢኖሩም ረጅም ጊዜያት የወሰዱ ድርድሮች ሲከሽፉም ተስተውለዋል።

የፋኖ ኃይሎች በመካከላቸው ያለው ልዩነት ሰፍቶ "በደም የሚፈላለጉ እና እርስ በእርስ የተዋጉ" ሆነው እንደነበር ዶ/ር ዳንኤል ያስታውሳሉ።

ባንታየው ሽፈራው እና ጆን ኢሺያማ የተባሉ አጥኚዎች የፋኖ ኃይሎች አንድነት እና ክፍፍልን በተመለከተ ባለፈው ዓመት መጨረሻ ባሳተሙት መጣጥፍ፤ ቡድኖቹ "የርዕዮተ ዓለም እና የፖለቲካ ግብ" ልዩነት እንዳላቸው ጽፈዋል።

በእስክንድር ነጋ የሚመራው አፋሕድ "የአማራ ማንነት ከኢትዮጵያዊነት ጋር የተጣበቀ" በመሆኑ "አማራዎች ራሳቸውን ከኢትዮጵያ ነጥለው መመልከት እንደሌለባቸው" እንደሚሞግት አስፍረዋል።

በተቃራኒው ወገን ያሉት ኃይሎች ምልከታ ደግሞ "ጥልቅ መሠረቱን የጣለው በአማራ የብሔር ማንነት ላይ" እንደሆነ ፀሐፊዎቹ ጠቁመዋል።

"ይህ አመለካከት የአማራ ብሔርተኝነትን እንደ ኢትዮጵያዊነትን መልሶ መገንቢያ መንገድ አድርጎ ከማየት ይልቅ፤ ለአማራን ኅልውና እና ጥቅም ቅድሚያ የሚሰጥ ነው" ሲሉ ልዩነቱን አብራርተዋል።

ዶ/ር ዳንኤል፤ ይህ "አማራነት ወይስ ኢትዮጵያዊነት ይቅደም" የሚል ክርክር አንዱ የክፍፍል ምንጭ እንደነበር ቢያምኑበትም፤ ከዚህ በላይ ግን "አውራጃዊነት" ዋነኛ ተግዳሮት ነው ይላሉ። ይህ ጉዳይ "የዕዝ መዋቅሩን ማን መምራት አለበት?" በሚለው ላይም ይንጸባረቅ እንደነበር በማንሳት ይከራከራሉ።

ከዚህም ባሻገር በውጭ አገር በሚገኙ "ዲያስፖራዎች እና የዲያስፖራ ሚዲያዎች" መካከል ያለው የአቋም ልዩነት "አንድ እንዳይሆኑ ትልቅ አስተዋፆ አድርጓል" ሲሉ ተጨማሪ የሚሉትን ምክንያት ጠቅሰዋል።

የአዲሱ ድርጅቱ የሕዝብ ግንኙነት መምሪያ ኃላፊ የሆኑት አስረስ ማረም በምክንያትነት የሚያነሱት ይህንኑ ጉዳይ ነው።

"ከውስጥ ከውጭም ጣልቃ ገብነቶች ነበሩ" የሚሉት አስረስ፤ "በተለይ የመደራጀት ሚናውን መሬት ላይ ላለው ኃይል፣ ለመሪው ያለመተው፣ ይልቁንም በርቀት ሆኖ የመወሰን ፍላጎቶች [ነበሩ]" ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

"የራስ ጉዳይን በራስ በመወሰን ረገድ የነበረ ክፍተትንም" ከዚህ ጋር የተያያዘ ሌላ ምክንያት አድርገው ጠቅሰዋል።

'የአማራ ፋኖ ብሔራዊ ንቅናቄ' እንዴት ተዋቀረ?

የአማራ ፋኖ ብሔራዊ ንቅናቄ "የሁለት ድርጅቶች ውህደት" መሆኑን የሚያነሱት አስረስ፤ "የተፈጠረው ድርጅት ጥምረት፣ ግንባር ወይም ትብብር ሳይሆን ሙሉ በሙሉ ውህድ ድርጅት ነው" በማለት ያስረግጣሉ።

"አሁን ባለንበት ሰዓት ከአማራ ፋኖ ብሔራዊ ንቅናቄ ውጪ የሆነ አንድም ጠመንጃ የያዘ አካል አይደለም በቡድን ደረጃ፣ በግለሰብ ደረጃ የለም። ሁሉንም ያቀፈ፣ ሁሉንም የፋኖ ኃይሎች ያካተተ ድርጅት ነው የተመሠረተው" ሲልም ይሞግታሉ።

የድርጅቱ መዋቅር ሲወሰን "ፖለቲካዊ እና ወታደራዊ ክንፉን" የተለያየ ከማድረግ ይልቅ "ሁለቱንም በአንድ ማዕቀፍ ስር የሚመራበት" አካሄድ እንደተመረጠ አስረድተዋል። "ሊቀመንበሩ የአጠቃላይ የፖለቲካውም የወታደራዊ አመራሩም የመጨረሻ ትዕዛዝ ሰጪ ነው" ብለዋል።

አስረስ እንደሚናገሩት "የሊቀመንበሩን ሥልጣን ፖሊት ቢሮ እና ምክትል ሊቃነ መናብርት የሚጋሩት እንዲሆን" ተደርጓል። የሚመራውም "በአንድ ሊቀመንበር" እና "በአንድ አስፈጻሚ ኮሚቴ" እንደሆነም አክለዋል።

በድርጅቱ መተዳደሪያ ደንብ መሠረት ሊቀመንበሩን ጨምሮ ሁሉም የሥራ አስፈጻሚ "በየዓመቱ የመተማመኛ ድምፅ" እንደሚሰጥበት ገልጸዋል። "ያንን የመተማመኛ ድምጽ 50+1 ያላመጣ አመራር በኃላፊነት አይቀጥልም" ሲሉ አሠራሩን አብራርተዋል።

"አንድ ሊቀ መንበር ለሁለት የሥልጣን ዘመን ብቻ ነው መወዳደር የሚችለው፤ ለሦስተኛ ጊዜ መመረጥ አይችልም" የሚል ድንጋጌ መቀመጡንም አንስተዋል።

አስረስ እንደሚናገሩት፤ የድርጅቱ አመራሮችን የመምረጥ ሂደት "ሰፊ ንግግር የተደረገበት እና ረዘም ያለ ጊዜ የወሰደ" ነው። "ከሁለቱ ድርጅቶች ማን ከየትኛው ሊቀ መንበርነቱን ቦታ ይያዝ? ማን ምክትል ሊቀ መንበር ይሁን? ማን ወታደራዊ አዛዥ ይሁን?" የሚሉት እንዳነጋገሩ አልሸሸጉም።

ዋና ዋና የሚባሉትን የአመራር ቦታዎች የተወሰኑት "የተለያዩ መንገዶችን በመጠቀም" እንደሆነ አንስተዋል። በአመራሮች መረጣ ወቅት ግንዛቤ ውስጥ ገብተዋል ከተባሉት መስፈርቶች መካከል "ግለሰባዊ አቅም"፣ "የውክልና ጉዳይ" እንዲሁም "በሠራዊቱ ውስጥ ያለ ቅቡልነት" የሚሉት ይገኙበታል።

በሁለቱ ድርጅቶች ድርድር ወቅት "ክርክር" ተደርጎበታል የተባለው ሌላኛው ጉዳይ ርዕዮተ ዓለምን የሚመለከት ነው። የአማራ ፋኖ ብሔራዊ ንቅናቄ መመሥረት ይፋ በተደረገበት መግለጫ ላይ ድርጅቱ የሚመራው "በአማራ ብሔርተኝነት ርዕዮተ ዓለም" እንደሆነ ተገልጿል።

አስረስ "የአማራ ብሔርተኝነት ስንል በዘላቂነት የአማራን ማንነት ግንባታን መሠረት ያደረገ የፖለቲካ እንቅስቃሴ" ማለት መሆኑን ይናገራሉ።

ይህ ምልከታ "የአማራ ሕዝብ መብት እና ጥቅም ሲከበር፣ ፍላጎት እና ርዕይ ተግባራዊ ሲደረግ የኢትዮጵያ ኅልውናም አብሮ ተግባራዊ የሚደረግ መሆኑን [የሚያምን ነው]" ሲሉም አክለዋል።

የፋኖ ኃይሎች መደራጀት የግጭቱን አቅጣጫ ይቀይራል?

የአፋብን የሕዝብ ግንኙነት መምሪያ ኃላፊው አስረስ አንድ ድርጅት መመሥረቱ "በፖለቲካም፣ በወታደራዊም ረገድ ከፍተኛ ለውጥ ያመጣል" ባይ ናቸው። የድርጅቱ መመሥረት ጥቅሞች ብለው ከሚጠቅሷቸው ጉዳዮች አንዱ የፋኖ ኃይሎችን በተመለከተ ያለውን "ምልከታ ይቀየራል" የሚል ነው።

"በቀጣናው ያሉ ኃይሎችም ሆኑ፣ በርቀት ያሉት ምዕራባውያን፣ ሌላውም የሚመለከተው 'ጉዳይ አለኝ' የሚል አካል ሁሉ ይህንን ትግል የሚያይበት መነጽር በፍጹም ይቀየራል" ብለዋል።

"ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ መንግሥት የመሆን ዕድል ያለን መሆኑን፤ ትግሉን በማንሸንፍ ጊዜ ለአገር የሚታመን፣ ኃላፊት የሚወስድ አመራር፣ ቡድን ያለው መሆኑን በሚገባ የሚያመላክት ነው" ሲሉም አክለዋል።

በታጣቂዎቹ ዘንድም "አዲስ መነሳሳት ይፈጥራል" እንዲሁም "ሕዝቡ በትግሉ ላይ ያለውን እምትነት ይጨምራል" ሲሉም ተናግረዋል።

የፋኖ ኃይሎች እንቅስቃሴ ላይ ጥናት ያደረጉት ዶ/ር ዳንኤል ግን ይህ ዓይነቱ ድምዳሜ ላይ ከመድረስ ይቆጠባሉ።

አንድ ድርጅት መመሥረቱ "ትልቅ እርምጃ" መሆኑን የሚያነሱት ተመራማሪው፤ የኃይሎቹ ወደ አንድ መምጣት የግጭቱን አካሄድም ቢሆን ይቀይረዋል የሚል እምነት እንደሌላቸው ይናገራሉ።

"[ወደፊት] የሚፈጠረውን እናያለን። አካሄዱን የሚቀይረው አይመስለኝም። ባለበት ነው ሊሄድ የሚችለው። ከዚህ በፊትም በወታደራዊ ኦፕሬሽን ላይ በጋራ ሆነው 'ዘመቻ እንደዚህ' እያሉ ያከናውናሉ። አሁንም ቢሆን ከዚያ ውጪ ሊያደርጉ የሚችሉት ነገር ያለ አይመስለኝም" ሲሉ ምልከታቸውን ያስረዳሉ።

እንደዚህ ዓይነት የትጥቅ ትግሎች ውጤታማ ለመሆን "ከአንድ ማዕከል ተነስቶ እየሰፋ የሚሄድ" ቁጥጥር ሊኖረው እንደሚገባ የሚያነሱት ዶ/ር ዳንኤል፤ የፋኖ ኃይሎች ያሉትን ግን "በየገጠራማ ቦታው" እንደሆነ በመጥቀስ ይከራከራሉ።

አሁን የተዋሃዱት ቡድኖች "የመጨረሻዎቹ የፋኖ ኃይሎች ናቸው" የሚል እምነት እንደሌላቸውም ገልጸዋል። "አሁንም ያልጠሩ ነገሮች" እንዳሉ የሚናገሩት ተመራማሪው፤ ሊያጋጥሟቸው የሚችሉ የተለያዩ ተግዳሮቶችንም ይዘረዝራሉ።

"ትልቅ ተግዳሮት ያለባቸው ምንድነው? የወንጀል ክፍሉ በጣም ከባድ ነው። በየመንገዱ ዘርፊያ [አለ]። በየጊዜው ሰው ይታገታል። መንገድ ላይ ቀረጥ ክፈል ይባላል። መኪና ይቃጠላል። መሬት ላይ ያለው ሕዝብ ተማርሯል" ሲሉ ምልከታቸውን ተናግረዋል።

በተጨማሪም በፋኖ ኃይሎች መካከል አለ የሚሉት "አውራጃዊነት" እና የበላይነትን ለመያዝ የሚደረግ "ሽሚያም" በተግዳሮትነት ያነሳሉ።

"ያንን ማጥራት ከቻሉ፣ በትክክልም ወደ አንድ ማዕከላዊ የዕዝ ሰንሰለን ማምጣት የሚችሉ ከሆነ፣ የአውራጃዊነት ግንቡን ማፍረስ የሚችሉ ከሆነ [...] ቢያንስ ግፊት አድርገው [መንግሥትን] ወደ ንግግር፣ ውይይት ማምጣት የሚችሉ ይመስለኛል" ብለዋል።

የአፋብን የሕዝብ ግንኙነት መምሪያ ኃላፊው አስረስ በበኩላቸው በተመራማሪው የሚነሳውን "የአውራጃዊነት" ክፍፍል አይቀበሉትም።

"ባለፉት 30 ወራት በተደረገው የትግል ሂደት ውስጥ አንድ ሰፈር ውስጥ እርስ በእስር በአደረጃጀቶች መካከል የተነሳ ቁርሾ ሊኖር ይችላል፤ ከአውራጃ ወደ አውራጃ ግን አንድም ጥይት ተተኩሶ አያውቅም፣ አንድም ግጭት ተከስቶ አያውቅም" ሲሉ ተከላክለዋል።

"የድርጅታችን መመሥረት ይሄንን የአውራጃዊነት የፖለቲካ እንቅስቃሴ እንዲደረግ ሲሠሩ የነበሩ ግለሰቦችን ያሳፈረ እና ያንን አጀንዳ የዘጋ ነው ብለን እናምናለን" ሲሉም በአጽንኦት አንስተዋል።

በአንድ ድርጅት ሥር መዋቀር የንግግር ዕድልን ያሰፋል?

የምሥራቅ አፍሪካ በይነ መንግሥታት ድርጅት (ኢጋድ)፣ የአፍሪካ ኅብረት እና የአውሮፓ ኅብረት ልዑካን ካለፈው ዓመት ጥር አንስቶ በአማራ ክልል የሚንቀሳቀሱትን የፋኖ ኃይሎች ከመንግሥት ጋር ለማደራደር እንቅስቃሴ ሲያደርጉ ቆይተዋል። የአማራ ፋኖ ሕዝባዊ ድርጅትን ሲመሩ የነበሩት እስክንድር ነጋም ከተቋማቱ ልዑካን ጋር ንግግር መደረጉን ከዚህ ቀደም አረጋግጠዋል።

እስክንድር የሚመሩትን ድርጅት "አክስመው" አዲሱን የአማራ ፋኖ ብሔራዊ ንቅናቄ መቀላቀላቸው ተገልጿል። ይህ ከመሆኑ አስቀድሞ ግን ቢያንስ ሦስት የአማራ ፋኖ ሕዝባዊ ድርጅት አመራሮች የትጥቅ ትግልን በመተው ከመንግሥት ጋር ስምምነት ፈጽመዋል።

ስምምነቱን ከፈጸሙት አመራሮች አንዱ የሆኑት እና የድርጅቱ ወታደራዊ አስተዳደር መምሪያ ኃላፊ እንደሆኑ የተገለጹት እያሱ አባተ፤ "የአማራ ፋኖ ሕዝባዊ ድርጅት በፋኖ ትግል ውስጥ ብቸኛው፣ የመጀመሪያውም ድርጅት ነው። ሁሉንም ፋኖ ወክለን ነው ያለነው" ሲሉ ተደምጠዋል።

ይህንን ሂደት የተከታተሉት ዶ/ር ዳንኤል፤ ወደ መንግሥት የተመለሱት አመራሮች በዚህ ስምምነት ሊጸኑ የሚችሉ ቢሆንም፤ በትጥቅ ማስፈታት እና መልሶ ማዋሃድ ሂደት ውስጥ የሚያልፉ ታጣቂዎች ግን ባሉበት ይቆያሉ የሚል እምነት የላቸውም።

"[ታጣቂዎቹ] ዲሞቢላይዝ እንዲሆኑ የተወሰነ ሳንቲም፣ ሥልጠና ይሰጣቸዋል። ያቺ ገንዘብ ስታልቅ ተመልሰው ወደ ጫካ ይሄዳሉ። ምክንያቱም ጫካ ውስጥ የበለጠ ገንዘብ ማግኘት ይችላሉ" በማለት አስረድተዋል።

ዶ/ር ዳንኤል በአጠቃላይ ግጭቱ ወደ ሰላም ድርድር ለማምራት በሚያስችል ደረጃ "በስሏል" ለማለት እንደሚቸገሩ ገልጸዋል።

ሁለት አካላት ወደ ድርድር ለመግባት "አቅማቸው ተሟጥጧል (exhausted) ወይ? ለመደራደር ፍላጎት አላቸው ወይ? የመደራደር ዕድል እና መድረክ ተሟልቷል ወይ? ሊያደራድሩ የሚችሉ አካላትስ አሉ ወይ?" የሚሉት ጥያቄዎች መመለስ እንደሚኖርባቸው ዘርዝረዋል።

የትግራይ ጦርነትን በማሳያነት የሚጠቅሱት ተመራማሪው፤ ጦርነቱ እስከ ደብረ ሲና እስከሚደርስ ባለው ጊዜ ውስጥ የተከፈለው "ሰብአዊ እና ቁሳዊ ዋጋ" የፌደራል መንግሥቱን "አቅም እንዲሟጠጥ" እንዳደረገ ይጠቅሳሉ።

በትግራይ ኃይሎች በኩልም "የመጨረሻው ምት" እንደነበር አስታውሰዋል። በሁለቱም በኩል የነበረው መዳከም የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ካሳደረው ጫና ጋር ተዳምሮ ተፋላሚዎቹ ወደ ድርድር እንዲሄዱ ማድረጉን አብራርተዋል።

"የዚህኛው ግን በፋኖ በኩል እንደዚህ ማድረግ የሚችሉ አይመስለኝም። አሁንም አጥቅቶ መሸሽ፣ የደፈጣ [እና] ድንገተኛ ጥቃት የመፈጸም፣ አንዳንድ ዒላማ ያላቸው ዘመቻዎችን የማድረግ ነገር ይኖራል። መደበኛ (conventional) የሆነ ፊት ለፊት መንግሥትን [መዋጋት አይኖርም" ይላሉ።

ይህ አካሄድ ለድርድር የሚያበቃ አስገዳጅ ሁኔታ የመፍጠር አቅሙ ዝቅተኛ መሆኑን ያነሳሉ።

አዲሱ ድርጅት "ጠንክሮ የሚመጣ ከሆነ፣ ቦታዎች መያዝ፣ ጫና መፍጠር የሚችል ከሆነ ያኔ እንዲደራደር ማስገደድ ይቻላል" ብለዋል። የዚህ ዓይነቱ መዋቅት "የመጨረሻ ግብ" ለድርድር የሚያበቃ "ጫና መፍጠር መሆን አለበት" የሚል አቋም እንዳላቸው ተናግረዋል።

የፌደራል መንግሥት ያለው "ወታደራዊ እና ኢኮኖሚያዊ አቅም እንዲሁ የሚጣጣል" እንዳልሆነ የሚያነሱት ዶ/ር ዳንኤል፤ "ከፈለገ እዚህም እዚያም መዋጋት ይችላል፤ [ግጭቱን] እየተቆጣጠረ (manage እያደረገ) ተራዝሞ እንዲቀጥልም ማድረግ ይችላል" ሲሉ ግምገማቸውን አጋርተዋል።

"እኔ ብቸኛ መፍትሔ የሚታየኝ መነጋጋር፣ መደራደር፣ መወያየት ነው። ምክንያቱም ሁለት ዓመት [ታይቷል]፤ ለማኅበረሰብ በጣም ዋጋ የሚያስከፍል ነው። እንደዚህ እቀጥላለሁ ቢባል ማኅበረሰቡ መሸከም የሚችል [ትክሻ] ያለው አይመስለኝም" ብለዋል።

በአጠቃላይ ግን የፋኖ ኃይሎች በአንድ መዋቅር ሥር መደራጀታቸው ድርድርን በተመለከተ "በጋራ እንዲወስኑ" እንዲሁም "በጠንካራ የዕዝ ሰንሰለት" ውሳኔውን ወደ "መደበኛው ተዋጊ" ማውረድ እንዲችሉ ዕድል እንደሚፈጠር አመልክተዋል።

የአማራ ፋኖ ብሔራዊ ንቅናቄ ሰላም ንግግር እና ድርድር በተመለከተ ምን ዓይነት አቋም እንዳለው የተጠየቁት የሕዝብ ግንኙነት መምሪያ ኃላፊው አስረስ በበኩላቸው፤ "አንድ ድርጅት የፈጠርነው ለድርድር ብለን አይደለም፤ ለማሸነፍ ነው" የሚል ምላሽ ሰጥተዋል።

"[የድርድርን] ጉዳይ በተመለከተ ወደፊት አጠቃላይ ተለዋዋጭ ሁኔታዎችን አይቶ የድርጅቱ የበላይ አመራር ውሳኔ የሚያሳልፍበት ጉዳይ ነው የሚሆነው። አሁን ባለንበት ሁኔታ ገና ሥራዎችን እየሠራን ነው የምንገኘው" ብለዋል።