ከሚኒያፖሊስ ግድያ በኋላ “ሁሉንም ነገር እየገመገሙ” እንደሆነ ትራምፕ ተናገሩ
የአሜሪካው ፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕ አስተዳደራቸው በሚኒያፖሊስ ያለውን ሁኔታ እየገመገመ እንደሆነ ተናገሩ።
ፕሬዚደንቱ ይህን ያሉት ቅዳሜ እለት በሚኒያፖሊስ የ37 ዓመቱ ነርስ አሌክስ ፕሪቲ በኢሚግሬሽን መኮንኖች በተተኮሰበት ጥይት ከተገደለ በኋላ በተነሳ ተቃውሞ ሰበብ ነው።
ትራምፕ እሁድ ዕለት ለዎል ስትሪት ጆርናል ሲናገሩ ፕሪቲን ተኩሶ የገደለው መኮንን ስለወሰደው እርምጃ ትክክለኛነት በተደጋጋሚ ቢጠየቁም ቀጥተኛ መልስ ሳይሰጡ ቀርቷል።
በምትኩ አስተዳደራቸው “ሁሉንም ነገር እየገመገመ እንደሆነ እና ከውሳኔ ጋር እንደሚመጡ” ተናግረዋል።
ትራምፕ ለጋዜጣው ሲናገሩ ማንኛውንም ዓይነት ተኩስ እንደማይወዱ እና ማንም ቢሆን በጣም ኃይለኛ እና ሙሉ ጥይት የጎረሰ ሽጉጥ ታጥቆ ወደ ተቃውሞ መሄዱ ደስ እንደማይላቸው . . . ይህም ጥሩ ነገር እንደማያስከትል ተናግረዋል።
አስተዳደራቸው ቀደም ብሎ ፕሪቲን የገደለውን መኮንን የተከላከለ ሲሆን፣ የአገር ውስጥ ደኅንነት ኃላፊ ክሪስቲ ኖም፣ ፕሪቲ የተገደለው "ሽጉጡን ሲያሳይ" እንደነበር ተናግረዋል።
የአካባቢው ባለሥልጣናት ግን ይህን አስተባብለዋል።
ባለሥልጣናቱ የሟች ሽጉጥ በሕጋዊ መንገድ የተመዘገበ እንደሆነ ገልጸው፤ የተተኮሰበትም መሣሪያውን ከተነጠቀ በኋላ እንደሆነ ተናግረዋል።