ቻይና በምያንማር የነበሩ 11 የአንድ የወንጀል ቡድን አባላትን በሞት ቀጣች
ቻይና በምያንማር የማጭበርበሪያ ካምፖችን የሚመራ የማፍያ ቡድን አስራ አንድ አባላትን በሞት መቅጣቷ ተዘገበ።
የዢጂያንግ ግዛት ፍርድ ቤት ግድያ፣ ሕገ ወጥ እስር ፣ ማጭበርበር እና ቁማርን ጨምሮ በፈፀሟቸው ወንጀሎች ሚንግ በተባለው የማፍያ ቡድን አባላት ላይ የሞት ቅጣቱን ያስተላለፈው ባለፈው መስከረም ወር ላይ ነበር።
ሚንግ የተባለው ቡድን በቻይና ድንበር አቅራቢያ ላይ የምትገኘውን የምያንማሯን ላውኬንግ ከተማን ከሚያስተዳድሩ በርካታ ቡድኖች መካከል አንደኛው ነው።
የወንጀል ቡድኑ ከዓለም ተነጥላ በድኅነት አረንቋ ውስጥ የምትገኘውን ከተማ የቁማር እና የወሲብ ንግድ ማዕከል አድርጓታል።
የዚህ ቡድን አባላት በቁጥጥር ሥር ውለው ለቻይና ተላልፈው የተሰጡት እንደ አውሮፓውያኑ 2023 የአካባቢው ታጣቂዎች በእርስ በርስ ጦርነት ውስጥ ያለችውን ከተማ ከተቆጣጠሩ በኋላ ነበር።
በምያንማር በሚካሄደው የማጭበርበር ወንጀል በሺዎች የሚቆጠሩ ቻይናዊያን ሠራተኞች ወጥመድ ውስጥ ገብተዋል።
እነዚህ ዜጎች ከመላው ዓለም ተታለው ወደ ማጭበርበሪያ ካምፖች እንዲገቡ ከተደረጉ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች መካከል ናቸው።
ባለፈው ዓመትም ለትወና ሥራ ወደ ታይላንድ ካመራ በኋላ ወደ ምያንማር የማጭበርበሪያ ካምፕ የተወሰደው ቻይናዊ የፊልም ተዋናይ በቻይና ኢንተርኔት ሲፈለግ ነበር።
እንዲህ ዓይነት ታሪኮች ስጋት ውስጥ የከተታት ቤይጂንግም የምያንማር ወታደሮች አጭበርባሪ ወንበዴዎችን እንዲቆጣጠሩ ስትጠይቅ ነበር።
ይህንንም ተከትሎ የምያንማር ወታደሮች ከታጣቂዎች ጋር ግጭት ውስጥ ከገባ በኋላ ከተማዋ በድጋሚ በቡድኑታጣቂዎች እጅ ገብታለች።
እንደ ቻይና ከፍተኛ ፍርድ ቤት ከሆነ የሚንግ የወንጀል ቡድን በማጭበርበር እና በቁማር ከ2015 እስከ 2023 ባሉት ዓመታት ውስጥ ከ1.4 ቢሊዮን ዶላር በላይ ገንዘብ አግኝቷል።
ከዚህም በተጨማሪ በፈፀሙት ወንጀል ምክንያት ለ14 የቻይና ዜጎች ሞት እንዲሁም በሌሎች በርካታ ሰዎች ላይ ጉዳት ማድረሱን ፍርድ ቤቱ ገልጿል።