የሚኒሶታ የኮንግረስ አባል
የሆኑት ኢልሃን ኦማር በማዘጋጃ ቤት ሳሉ ‘ምንነቱ ባልታወቀ ፈሳሽ’ ጥቃት እንደተፈጸመባቸው የግዛቱ ፖሊስ አስታወቀ።
ከታዳሚዎች አንደኛው ስሪንጅ
በመጠቀም ምንነቱ ያልታወቀውን ፈሳሽ ኤልሃን ኦማር ላይ እንደረጨ ተገልጿል።
ኢልሃን ኦማር ጉዳት ሳይደርስባቸው
“ወደፊት እንቀጥላለን. . . የሚኒሶታ ነዋሪዎች ጠንካራ ነን” በማለት ንግግር ማድረጋቸውን ሲቀጥሉ፤ ግለሰቡን ፖሊሶች ከማዘጋጃ ቤቱ አስወጥተዋል።
ኢልሃን በኤክስ ገጻቸው
“ደኅና ነኝ። ብርቱ ሰው ስለሆንኩ እንዲህ ያለ ትንሽ ነገር አያናውጠኝም፤ ሥራዬንም አያሰናክለኝም። ጉልበተኞች እንዲያሸንፍ አልፈቅድም”
ብለዋል።
ኢልሃን ላይ ጥቃት የሰነዘረው ግለሰብ
ከማዘጋጃ ቤቱ ሲወጣ “እርስ በራሳችን እያጣላችን ነው” ሲል ተደምጧል።
በክፍሉ ውስጥ የነበረ የቢቢሲ ዘጋቢ እንደታዘበው
በኤልሀን ላይ የተረጨው ፈሳሽ ጠንካራ ሽታ ያለው ኬሚካል ነው።
የሚኒሶታ ከንቲባ “በሚኒያፖሊስ ጥቃት
እና ማስፈራራት ቦታ የላቸውም። ሰዎችን ሳንጎዳ የተለያየ ሐሳብ ማራመድ እንችላለን” ሲሉ ድርጊቱን አውግዘዋል።
የስደተኞች ጉዳይ መሥሪያ ቤት የፀጥታ ባልደረቦች በሚኒሶታ
እየወሰዱ ባለው እርምጃ ምክንያት ከፍተኛ ሕዝባዊ ተቃውሞ ተነስቷል።
ሁለት አሜሪካውያን መገደላቸውን ተከትሎ በሚኒሶታ ግዛት የሚወሰደው እርምጃ "በጥቂቱ ረገብ እንደሚል" ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ተናግረዋል።
በማዘጋጃ ቤቱ ውስጥ የነበረው ጃኩሊን ጎስሊንግ “ከኤልሃን ረዳቶች
አንዱ የሆነ ሰው ማስታወሻ ሊያቀብላት ነበር የመሰለኝ” ብሏል።
ሌላ በክፍሉ የነበረ
ታዳሚ አልፍሬድ ፍላወርስ ጁንየር “በማዘጋጃ ቤቱ ንግግሯን በመቀጠሏ ጀግንነቷን አደንቃለሁ” ብሏል።
እአአ በ2019 ኢልሃን የመጀመሪያዋ ሶማልያዊ-አሜሪካዊት፣ የመጀመሪያዋ አፍሪካ የተወለዱ አሜሪካዊት
እና የመጀመሪያዋ ሙስሊም አሜሪካዊት የኮንግረስ አባል ሆነው ተመርጠዋል።
ኢልሃን ጥቃት የደረሰባቸው ወደ 100 ሰዎች በተገኙበት የማዘጋጃ ቤት ስብሰባ ላይ ነው።
በሚኒሶታ ታኅሣሥ መግቢያ ላይ ረኔ ጉድ
የተባለችው የ37 ዓመት ሴት በስደተኞች ጉዳይ መሥሪያ ቤት የፀጥታ ባልደረቦች ስትገደል ባለፈው ሳምንት ደግሞ አሌክስ ፕሬቲ የተባለው
ግለሰብ መገደሉ ከፍተኛ ቁጣ አስነስቷል።
ሕዝባዊ ተቃውሞ ያስነሳው የአሌክስ ግድያ ዴሞክራቶች እና ሪፐብሊካኖችም ጭምር አስቆጥቷል።
የትራምፕ አስተዳደር የሚወስደውን እርምጃ ለማርገብ የወሰነውም ለዚህ ነው።
ሰኞ ዕለት የአገር ውስጥ ደኅንነት መሥሪያ ቤት በሚኒሶታ የሚወሰደውን እርምጃ የሚመሩት የድንበር ጥበቃ ኃላፊ ግሪጎሪ ቦቪኖ ከግዛቱ ለቅቀው እንዲወጡ ወስኗል።
የትራምፕ የድንበር ጉዳዮች ሹመኛ ቶም ሆማን ግሪጎሪ ቢቪኖን ተክተው ወደ ሚኒሶታ አቅንተዋል።
ኤልሃን በማዘጋጃ ቤት ባደረጉት ንግግር የስደተኞች እና ጉምሩክ ክፍል “ከሥራ መታገድ አለበት”
ብለዋል። የአገር ውስጥ ደኅንነት ጸሐፊ ክርስቲ ኖም “ከሥራ ተባረው በሕግ ይጠየቁ” ሲሉም አክለዋል።
“መናገራችንን እንቀጥላለን።
እኔን አድምጡኝ። ትርክቱን እንዲቆጣጠሩ አትፍቀዱላቸው” በማለት ኤልሃን ተናግረዋል።
ትራምፕ እና ኤልሃን ለረዥም ጊዜ የቆየ ቁርሾ አላቸው። ትራምፕ በሚኒሶታ እርምጃ እየወሰዱ
ያሉት ለኤልሃን ካላቸው ጥላቻ ተነስተው ነው የሚሉም አሉ።
ትራምፕ “ኤልሃን መታሰር አለባት። ወደ ሶማሊያ ትመለስ። ከዓለም የከፋው አገር ነው። ሶማሊያ
ሄዳ አገሯን ታላቅ ታድርግ” ማለታቸው ይታወሳል።
ሚኒሶታ አብዛኞቹ የሶማሊያ ስደተኞች የሚኖሩባት ግዛት ናት።
ትራምፕ በሚኒሶታ ግዛት ያሰማሯቸውን 3,000 የስደተኞች ኦፊሰሮች እንዲያስወጡ ጫናው በርትቷል።
ትራምፕ ከፎክስ ኒውስ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ በሚኒሶታ ያሰማሩትን ኃይል ተከላክለዋል።
"በሺዎች የሚቆጠሩ ወንጀለኞችን ከግዛቱ አስወጥተናል። የወንጀል ቁጥሩ ከፍተኛ ነበር። ቶም ሆማን በቦታው ይገኛል። የሚወሰደውም እርምጃ ይረግባል" ሲሉም ምላሽ ሰጥተዋል።