ኢራን በፍጥነት ወደ ድርድር ካልመጣች “ከባድ ጥቃት” እንደሚጠብቃት ትራምፕ አስጠነቀቁ
ኢራን ከአሜሪካ ጋር በአስቸኳይ ስምምነት ላይ ካልደረሰች ከአሜሪካ የሚገጥማት ቀጣዩ ጥቃት ከዚህ በፊት ከነበረው “በጣም የከፋ ይሆናል” ሲሉ ፕሬዝዳንት ትራምፕ አስጠነቀቁ።
ፕሬዝዳንቱ በማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ላይ ባሰፈሩት ማስጠንቀቂያ ወደ ባሕረ ሰላጤው ያሰማሩትን ግዙፍ የጦር አውሮፕላን ጫኝ መርከብን እና ሌሎችንም በመጥቀስ፣ አስፈላጊ ሲሆን “በፍጥነት እና በአደገኛ ሁኔታ” የሚሰጣቸውን ተልዕኮ ለመፈጸ ምዝግጁ መሆናቸውን ተቁመዋል።
በቬንዙዌላ ላይ የወሰዱትን እርምጃ ያነሱት ትራምፕ፤ ኢራን ጊዜው እየሄደባት እንደሆነ እና የኒውክሌር መረሃ ግብሯን በተመለከተ በፍጥነት “ወደ ድርድር ጠረጴዛ” ትመጣለች ብለው ተስፋ እንደሚያደርጉ አመልክተዋል።
ቀደም ሲል “ወደ ድርድር መጥተው ከስምምነት እንዲደርሱ ነግሬያቸው ነበር፤ ነገር ግን አልመጡም” በማለት ባለፈው ሰኔ ወር ላይ የተፈጸመው የአየር ጥቃት መከተሉን ገልጸዋል።
የኢራኑ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ለአገራቸው መገናኛ ብዙኃን ምንም ዓይነት ንግግር አንዳልተጀመረ፤ ነገር ግን ከአቀራራቢ አገራት ጋር ግንኙነት መጀመሩን ጠቁመዋል።
ይህ የትራምፕ ማስጠንቀቂያ የተሰማው አብርሃም ሊንከን የተባለው ግዙፍ የጦር መርከብ እና በርካታ ተዋጊ መርከቦች ከተለያዩ አቅጣጫዎች ባለፈው ሳምንት ተነስተው ወደ መካከለኛው ምሥራቅ ከደረሱ በኋላ ነው።
ኢራን ውስጥ ከተከሰተው ተቃውሞ ጋር በተያያዘ የፀጥታ ኃይሎች ተቃዋሚዎችን መግደላቸውን የሚቀጥሉ ከሆነ ከባድ ጥቃት እንደሚፈጽሙ ትራምፕ ሲዝቱ ቆይተው ተቃውሞው ጋብ ብሏል።
አሁን ደግሞ የኢራን ባለሥልጣናት በተደጋጋሚ ያስተባበሉትን እና ለሰላማዊ አገልግሎት ብቻ ነው የሚውል ነው የሚሉትን የኒውክሌር ግንባታቸውን በተመለከተ በፍጥነት ወደ ድርድር ቀርበው ካተልስማሙ እርምጃ እንደሚወስዱ ዝተዋል።
አሜሪካ በኢራን ላይ ጥቃት ምትፈጽም ከሆነ በምትሰጠው የአጸፋ ምላሽ ቀጣናዊ ግጭት ሊከሰት ይችላል የሚል ስጋት በባሕረ ሰላጤው አገራት ዘንድ ተጠናክሯል። በዚህ ሳቢያም የነዳጅ ዋጋ ጭማሪ ታይቶበታል።