"ከአምልኮ እስከ ግብይት"- ታሪካዊ የዋጋ ክብረ ወሰኑን መስበር የቀጠለው ወርቅ

በሰው ልጆች ታሪክ ውስጥ ጉልህ ሚና ከተጫወቱ የከበሩ ማዕድኖች መካከል ወርቅ በግንባር ቀደምነት ይጠቀሳል። ወርቅ የሃብት፣ የክብር፣ የውበት፣ የማንነትም መገለጫ ተደርጎ ይወሰዳል።

በተለያዩ የዓለም ሥልጣኔዎች ወርቅ ማዕከላዊውን ቦታ ይዞ ዘመናትን ተሻግሯል።

በተለያዩ ባህሎች ወርቅ ዘመን የማይሽረው እና መተኪያ የሌለው ሃብት ነው።

ወደ ጥንታዊ ግብፅ ብናቀና፤ ወርቅ 'የአማልክት አካል' ተብሎ ከኃያልነት እና ከመንፈሳዊነት ጋር ይተሳሰራል። የጥንታዊ ግብፅ የንጉሥ ቱታንክሀሙን የፊት ጭምብል የተሠራውም ከወርቅ ነው።

በኢንካ ሥልጣኔ ወርቅ 'የፀሐይ እንባ' የሚል መጠሪያ ተሰጥቶት ይመለክ ነበር። በጋና የአሻንቲ ሥልጣኔ ውስጥም ወርቅ ጉልህ ቦታ አለው።

በአክሱም ሥልጣኔ ዘመን ከወርቅ ሳንቲም እየተሠራ ለዓለም አቀፍ መገበያያነት ይውል እንደነበር ታሪክ ይመሰክራል። እስከዛሬም ድረስ በተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች በዓመት በዓሎች፣ በሠርግ እና በሌሎችም ክንውኖች በወርቅ ደምቆ መታየት የተለመደ ነው።

በሕንድ ፓድማናባስዋሚ ቤተ መቅደስ የሚገኙ መንበሮች ከወርቅ ነው የተሠሩት።

በሒንዱይዝም ወርቅ 'የእውነት እና ሞትን ድል የመንሳት' ምልክት ይባላል። ወደ ሜሶፖታሚያ እና አሲሪያ ሥልጣኔ ስንሄድ ደግሞ ወርቅ በተለምዶ 'የአስማት ጥበብ' ከሚባለው ጠልሰም ጋር ይተሳሰራል።

በዘመናዊ ሥልጣኔ ወርቅ መገበያያ፣ ሃብት ማከማቻ፣ የዓለም አቀፍ ፖለቲካ እና ምጣኔ ሃብት 'ሙቀት መለኪያ' ልንለው እንችላለን።

በባለሃብቶች ዘንድ ወርቅ እና ሌሎችም የከበሩ ማዕድናት አስተማማኝ ንብረት ተደርገው ይወሰዳሉ። ብሔራዊ ባንኮች ያላቸው የወርቅ ክምችት መጠንም የአገራት ምጣኔ ሃብት መለኪያ ከሚባሉት ይጠቀሳል።

የወርቅ ፍለጋ እና ክምችት በመላው የዓለም ጥግ እንደቀጠለ ነው።

የማዕድን ማውጣት ቴክኖሎጂ እየተሻሻለ ከመምጣቱ ጋር በተያያዘ ከ1950 ወዲህ አብዛኛውን የዓለም የወርቅ ክምችት ማግኘት ተችሏል።

ዓለም አቀፉ የወርቅ ንግድ ማኅበር፤ በሰው ልጆች ዘንድ እስካሁን ድረስ ጥቅም ላይ የዋለው 216,265 ቶን ወርቅ ብቻ ነው ይላል።

ይህ የወርቅ መጠን ከሦስት እስከ አራት የኦሊምፒክ መዋኛ ገንዳዎችን ይሞላል።

ወርቅ በተለይም ባለፉት ጥቂት ዓመታት ዋጋው በከፍተኛ ሁኔታ እየናረ መጥቷል። ጉልህ ፖለቲካዊ ክስተቶችን እየተከተለም በታሪክ ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ የዋጋ ጭማሪ አሳይቷል።

ከሰሞኑ የግሪንላንድን ጉዳይ በተመለከተ አሜሪካ እና የሰሜን አትላንቲክ ጦር ቃልኪዳን (ኔቶ) በገቡበት ውዝግብ ምክንያት የወርቅ ዋጋ ለመጀመሪያ ጊዜ ከ5,000 ዶላር በላይ ሆኗል።

ወርቅ የመሸጫ ዋጋ ክብረ ወሰኑን ሲሰብር ይህ የመጀመሪያው አይደለም። አምና በታሪክ ባልታየ ሁኔታ የወርቅ ዋጋ በአንድ ጊዜ ከ60% በላይ ጨምሮ ነበር።

ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ግሪንላንድን 'እንጠቀልላን' ማለታቸው የፋይናንስ ዘርፉን ማቃወሱን ተንታኞች ገልጸዋል።

ዋጋው የናረው ወርቅ ብቻ አይደለም። የብር ዋጋም በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ከ100 ዶላር በላይ ሆኗል። ባለፈው ዓመት የብር ዋጋ 150% ጨምሮ ነበር።

ከሳምንት በፊት ትራምፕ ግሪንላንድን የመጠቅለል ዕቅዳቸውን በማይደግፉ ስምንት አገራት ላይ ታሪፍ ለመጣል ሲዝቱ የወርቅ እና ብር ዋጋ የቀደመ ክብረ ወሰኑን ሰብሯል።

ትራምፕ የአውሮፓ አገራት ላይ እጥላለሁ ያሉትን ታሪፍ ቢሰርዙም ዛቻቸው የፈጠረው የምጣኔ ሃብት አለመረጋጋት አልረገበም።

ባለፈው ሳምንት ሰኞ የወርቅ ዋጋ በወቄት 4,689.39 ዶላር፣ የብር ዋጋ ደግሞ በወቄት 94.08 ዶላር ገብቷል።

በያዝነው ሳምንት ወርቅ ከ5,000 ዶላር በላይ ሲሸጥ፤ የብር ዋጋ ከ100 ዶላር በላይ ደርሷል።

ለሰሞነኛው የወርቅ ዋጋ መጨመር ዋነኛ ምክንያት የተባሉት ከፍተኛ የዋጋ ንረት፣ የአሜሪካ ዶላር መዳከም እና የአሜሪካ ብሔራዊ ባንክ የወለድ መጠንን በድጋሚ መቀነሱ ናቸው።

የዩክሬን እና የጋዛ ጦርነቶች እንዲሁም አሜሪካ የቬንዝዌላ ፕሬዝዳንት ኒኮላስ ማዱሮን በቁጥጥር ሥር ማዋሏም የወርቅ ዋጋ እንዲንር አድርገዋል።

እየተባባሰ በመጣው ጂኦ-ፖለቲካዊ ውጥረት ምክንያት ባለፈው ሳምንት የአውሮፓ የስቶክ ገበያ መዋዠቁ ተዘግቧል።

እአአ በ2025 ታኅሣሥ ወር ላይ ወርቅ ከ4,400 ዶላር በላይ መሸጡ በወቅቱ ክብረ ወሰን የሰበረ ተብሎ ነበር።

የአሜሪካ ብሔራዊ ባንክ በ2026 ዓመታዊ የወለድ መጠኑን ይቀንሳል መባሉ ወርቅን ጨምሮ የሌሎችም የከበሩ ማዕድናትን ዋጋ ከፍተኛ አድርጓል።

የአሜሪካ ብሔራዊ ባንክ ዘንድሮ ሁለት ጊዜ የወለድ መጠን እንደሚቀንስ ይጠበቃል።

ከምጣኔ ሃብት አለመረጋጋት በተጨማሪ ባለሃብቶች የወለድ መጠን ሲቀንስ የሚፈጠርባቸው ስጋት የወርቅ ዋጋ እንዲጨምር ከሚያደርጉ ዋነኛ ምክንያቶች መካከል ይጠቀሳሉ።

በ2024 አጋማሽ ላይ አንድ ግራም ወርቅ 2,600 ዶላር ይሸጥ ነበር። የመካከለኛው ምሥራቅ አለመረጋጋት እና የትራምፕ አስተዳደር የጣላቸው ታሪፎች በፈጠሩት ስጋት የወርቅ ዋጋ በአንድ ዓመት ውስጥ ወደ 4,420 ዶላር ከፍ ብሏል።

ከ2025 ታኅሣሥ በፊት በነበሩት 11 ወራት ብቻ የወርቅ ዋጋ ከ68 በመቶ በላይ ጭማሪ አሳይቷል።

በ2025፤ የብር መሸጫ ዋጋ በግራም 69.44 ዶላር (ከቀደመው ዓመት የ138% ጭማሪ የታየበት) ሲደርስ ፕላቲኒየም ደግሞ በ17 ዓመታት ውስጥ ከፍተኛ የሆነ ዋጋ በማስመዝገብ ወርቅን በልጦ ነበር።

በ2025 ጥቅምት ወር ላይ ወርቅ ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ ዋጋው ከ4 ሺህ ዶላር በላይ መግባቱ አነጋጋሪ ሆኖ ነበር።

በወቅቱ ትራምፕ በተለያዩ አገራት ላይ ታሪፎችን መጣላቸውን ካሳወቁ ወዲህ ወርቅ ከ25% በላይ ዋጋው ንሯል።

የአምናው የአሜሪካ እና ቻይና የንግድ ጦርነት የወርቅን ዋጋ በወቄት 3,357 ዶላር አድርሶታል።

በወቅቱ በወርቅ ዋጋ ላይ የተስተዋለውን ጭማሪ ከዐሥርታት በፊት በኢራን አብዮት ምክንያት ከተከሰተው ጭማሪ ጋር ተንታኞች ሲያነጻጽሩት ነበር።

ከኅዳር 1979 እስከ ጥር 1980 ድረስ የወርቅ ዋጋ 120% ጨምሮ ነበር።

ከ1979 ወዲህ የወርቅ ከፍተኛ ዓመታዊ ሽያጭ የተመዘገበው በ2025 ሲሆን፤ የዚህ ሳምንት ዋጋ ደግሞ የአምናውንም ክብረ ወሰን ሰብሯል።

ለወርቅ ዋጋ መጨመር ምክንያት የሆነው የትራምፕ የታሪፍ ዛቻ ብቻ አይደለም። ሰው ሠራሽ አስተውሎት (ኤአይ) በተለያዩ ዘርፎች ገናና እየሆነ መምጣቱ የፈጠረው ስጋትም ተጠቃሽ ነው።

በሌላ በኩል ደግሞ እየተለወጠ ያለው የዓለም አገራት ፖለቲካዊ አሰላለፍ እና አዳዲስ የንግድ ስምምነቶች የወርቅ ዋጋ እንዲያሽቆለቁል ሊያደርጉ እንደሚችሉ የሚተብዩ ባለሙያዎች አሉ።

ወርቅ በዓለም እጅግ አዋጭ የሚባለው የኢንቨስትመንት ዓይነት ነው።

ለወትሮው የምጣኔ ሃብት ምስቅልቅል ሲፈጠር ወርቅ አስተማማኝ እና ቋሚ የሃብት ማከማቻ መንገድ ተደርጎ ይወሰድ ነበር።

በተለይም ትራምፕ ለሁለተኛ ጊዜ ሥልጣን ከያዙ በኋላ ግን የወርቅ አስተማማኝነት ላይ ጥያቄዎች መነሳታቸው አልቀረም።

የገበያ መዋዠቅ ሲፈጠር ብዙዎች ወርቅ ለማከማቸት ስለሚሞክሩ ዋጋው እየናረ ይሄዳል።

በዓለም አቀፍ ገበያ ላይ ማንኛውም ዓይነት ማሽቆልቆል ሲታይ እንደ አማራጭ የሚወሰደው ወርቅ ይሆናል።

በተቃራኒው ዓለም አቀፍ የገበያ መዋዠቅ የወርቅ ዋጋ እንዲረክስም ሊያደርግ ይችላል።

በአውሮፓውያኑ 2020 የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ባስከተለው የምጣኔ ሃብት መዳከም የተነሳ ወርቅ ዋጋው አሽቆልቁሎ እንደነበር አይዘነጋም።