"ከጓደኞቼ ግማሾቹ ተገድለዋል"፡ ግጭት ትምህርት ቤታቸው ድረስ የተከተላቸው ታዳጊዎች

መንትዮቹ ማካሪም እና ኢክራም እንደየትኛውም መደበኛ ቀን ወደ ትምህርት ቤት አቀኑ። 18 ዓመት የሆናቸው እህትማማቾች ትምህርት ላይ ሳሉ "ለየት ያለ ድምጽ" ሰሙ።

ማካሪም ድምጹን ስትሰማ እንግሊዘኛ እየተማረች ነበር። ኢክራም ደግሞ ሳይንስ ክፍለ ጊዜ ላይ ነበረች።

በሱዳን የሚገኘው ትምህርት ቤታቸው ጥቃት እየተፈጸመበት ነበር።

ማካሪም በድንጋጤ ትከሻዋ "እንደጎበጠ" ታስታውሳለች። ክፍሏ ውስጥ ያለች ተማሪ ከተኩስ ለማምለጥ መሬት ላይ ተኛች።

"ግድግዳውን ተጠግተን ተደበቅን። አጠገቤ ያለችው ልጅ ትከሻዬ እየደማ መሆኑን ነገረችኝ" ትላለች ማካሪም።

የተለያየ ክፍል ውስጥ የነበሩት እህትማማቾች በትርምሱ ውስጥ ለመገናኘት ሞከሩ።

ኢክራም እህቷን ስትፈልጋት ወደ ሆስፒታል እንደተወሰደች አላወቀችም ነበር።

ከሌሎች የተጎዱ ተማሪዎች ጋር ማካሪም ወደ ሆስፒታል የተወሰደችው በአካባቢው ነዋሪዎች ነው።

በኤል-ኦቤይድ ከተማ አምቡላንስ ስለሌለ በግል መኪና እና በጋሪ ተማሪዎቹ ወደ ሕክምና ተወሰዱ።

ኢክራም እህቷን መፈለግ አቁማ ወደ ቤት እንድትሄድ ተማሪዎች እና መምህራን ነገሯት።

ማካሪም ከሆስፒታል ስትመለስ ነበር በሕይወት እንዳለች ቤተሰቦቿ ያወቁት።

"በር ላይ ተቀምጬ ጠበቅኳት። ከሩቅ ስናያት ሁላችንም ማልቀስ ጀመርን" ትላለች ኢክራም።

ኢክራም በጥቃቱ አልተጎዳችም። ነገር ግን እንግሊዝኛ መምህራቸው እና 13 ተማሪዎች ተገድለዋል። የተጎዱት ተማሪዎች ቁጥርም ከፍተኛ ነው።

አቡ አሲታ የሴቶች ትምህር ቤት በሰሜን ኮርዶፋን ግዛት የሚገኝ ሲሆን፣ ወደ 300 ተማሪዎች አሉት።

የግዛቱ አስተዳዳሪዎች እንደሚሉት ጥቃቱ የተፈጸመው በሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ኃይሎች (አርኤስኤፍ) ነው።

አርኤስኤፍ ስለቀረረበት ክስ ምላሽ አልሰጠም። ከቢቢሲ ለቀረበለት ጥያቄም አስተያየት ለመስጠት አልፈቀደም።

በትምህርት ቤቱ ላይ የደረሰው ጥቃት ሆነ ተብሎ የተፈጸመ ስለመሆኑ ግልጽ አይደለም።

ማካሪም እንደምትለው ግማሽ ያህል ጓደኞቿ ሲሞቱ የተቀሩት ተጎድተዋል።

ማካሪም ትከሻዋ እና ጭንቅላቷ ቢጎዳም ከሆስፒታል ወጥታለች። ከሰባት ቀናት በኋላ ከፍተኛ የራስ ምታት ስለገጠማት ሲቲ ስካን ተደረገላት። ጭንቅላቷ ውስጥ አነስተኛ የብረት ፍንጣሪ እንደቀረም ታወቀ።

"በጣም ስለሚያመኝ ብዙ ሕመም ማስታገሻ እወስድ ነበር" ትላለች።

በሱዳን የእርስ በርስ ጦርነት ከ150 ሺህ በላይ ሰዎች ሲሞቱ፤ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ተፈናቅለዋል።

የተባበሩት መንግሥታት እንዳለው በጦርነቱ ሳቢያ 17 ሚሊዮን ከሚሆኑ ዕድሜያቸው ለትምህርት የደረሰ ታዳጊዎች መካከል 13 ሚሊዮኑ ከትምህርት ገበታቸው ተስተጓጉለዋል።

የአቡ ሲታ ትምህርት ቤት ጥቃት ከደረሰበት በኋላ ለዕድሳት ለሦስት ወራት ተዘግቷል።

ማካሪም እና ኢክራም ጓደኞቻቸው እና መምህራቸው ወደተገደሉበት ትምህር ቤት መመለስ ከብዷቸው ነበር።

"ጓደኞቼ ወደ ትምህርት ቤት ተመልሰው ሲያበረታቱኝ እኔም ለመሄድ ወሰንኩ" ትላለች ኢክራም።

ወደ ትምህር ቤት መመለስ ግን ብዙ አሰቃቂ ትውስታዎችን ቀስቅሶባታል።

ኢክራም "ጥቃት የተፈጸመበትን ቦታ ላለማየት ዐይኔን ጨፍኜ አልፋለሁ" ትላለች።

የትምህርት ቤቱ አስተዳዳሪ ኢማን አሕመድ ለተማሪዎቹ የሥነ ልቦና ድጋፍ መሰጠቱን ትገልጻለች።

የተጎዱ ተማሪዎች ፈተና ለመውሰድ እንዳይቸገሩ አልጋ እና ነርስ ተዘግጅቷል።

በከተማው ላይ አሁንም ድረስ የሰው አልባ አውሮፕላን (ድሮን) ጥቃት ቢፈጸምም ቢቢሲ ትምህርት ቤቱን ሲጎበኝ ተማሪዎች እየሳቁ እና እየተጫወቱ ነበር።

የትምህርት ቤቱ አስተዳዳሪ እንደምትናገረው፤ ተማሪዎቹ የደረሰባቸውን ችለው ትምህርታቸውን ለመቀጠል ወስነዋል።

"አልበገር ባይነታቸውን ያሳያል። ያጣነውን ነገር ለማካካስም ወስነዋል" ትላለች።

አምና ከተማው ከአንድ ዓመት ተኩል በላይ በአርኤስኤፍ ኃይሎች ከበባ ሥር ስለነበር ትምህርት መከታተል ቀላል አልነበረም።

አሁን አንጻራዊ መረጋጋት ቢኖርም ትምህርት ቤቶች የተፈናቃዮች መጠለያ ሆነዋል። የከተማው የሰብአዊ እርዳታ ኮሚሽነር እንዳሉት በከተማው ወደ 1 ሚሊዮን የሚጠጉ ነዋሪዎች ተፈናቅለዋል።

ወደ መጠለያነት ከተለወጡ ትምህርት ቤቶች በአንዱ የምትማረው ኢብቲሳም አሊ እንደምትለው ትምህርት ቤቱ በተፈናቃዮች ስለተሞላ እንደልብ መንቀሳቀስ አይቻልም።

"መፀዳጃ ቤት እንኳን መሄድ ቀላል አይደለም" ትላለች።

የሰሜን ኮርዶፋን የትምህርት ሚኒስትር ዋሊድ አሕመድ አል-ሐሰን እንደሚሉት፤ ተፈናቃዮች በትምህር ቤት መስፈራቸው ችግር ቢፈጥርም "የጦርነት ዳፋ ነው"።

ማካሪም እና ኢክራም አሁን 19 ዓመት ሞልቷቸዋል። የደረሰባቸው ሰቆቃ እንዳለ ሆነ ተስፋ አልቆረጡም።

ኢክራም የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቷን አጠናቃ በኤል-ኦቤይድ ዩኒቨርስቲ እንግሊዝኛ እያጠናች ነው።

በጥቃቱ የተገደለችው መምህሯ የፋቲያ ካሊል ኢብራሒምን ፈለግ ተከትላለች።

የጓደኞቿ ሞት የፈጠረባት ቁጭት ትምህርቷ ላይ እንድትጠነክር ገፋፍቷታል።

"እነሱ ሊያሳኩ ያልቻሉትን ማሳካት እንዳለብን አምናለሁ" ትላለች።

ማካሪም ጉዳቷን እንዳከሙላት ሐኪሞች ሁሉ ሐኪም መሆን ትመኛለች። ሆኖም ሕክምና ለማጥናት የሚያበቃ ውጤት አላመጣችም።

ጭንቅላቷ ውስጥ ያለው የብረት ፍንጣሪ የፈጠረው ሕመም እንዳታጠና እንዳደረጋት ትናገራለች። የብረት ቁራጩን በቀዶ ሕክምና ማስወገድ አይቻልም።

"አንድ ሰዓት ብቻ አጥንቼ አንድ ሰዓት ማረፍ አለብኝ፤ ከባድ ነው" ትላለች።

ዶ/ር ታሪክ ዞቢር እንደሚሉት ጭንቅላት ውስጥ የሚቀር የብረት ፍንጣሪ በሰዎች ላይ የሚያደርሰው ሕመም እንደየሰዉ ይለያያል።

አንዳንዶች ያለ ሕመም ሲኖሩ፤ የጡንቻ መሸማቀቅ የሚገጥማቸው ሰዎች ግን ቀዶ ሕክምና ያስፈልጋቸዋል።

ማካሪም ሕመሙ የሚብስባት ክረምት ላይ እንደሆነ ትናገራለች። የሕመም ማስታገሻም ትወስዳለች።

ሕክምና ለማጥናት የሚወሰደውን ፈተና በድጋሚ ለመውሰድ ቆርጣ ተነስታለች።

"የሚያስፈልገውን ውጤት እንደማመጣ አምናለሁ። ስለወደፊቱ ብሩህ ተስፋ አለኝ" ትላለች።