ከሱዳኗ ኤል-ፋሸር ጭፍጨፋ ያመለጠው የሕክምና ባለሙያ ምስክርነት

በሱዳን ኤል-ፋሸር ከተማ በሚገኘው አገልግሎት እየሰጠ በነበረው የመጨረሻው ሆስፒታል በሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ኃይሎች (አርኤስኤፍ) ከተፈፀመ ጭፍጨፋ ያመለጠ አንድ ሰው ተስፋውንና ደስታውን ማጣቱን ይገልጻል።

"ባልደረቦቼን አጥቻለሁ" ሲል በሳዑዲ የእናቶች ሆስፒታል የላብራቶሪ ቴክኒሻን የሆነው አብዱ-ራቡ አህመድ ለቢቢሲ ተናግሯል።

"ፊታቸው ላይ ሁልጊዜ ፈገግታ እመለከት የነበሩ ሰዎችን አጥቻለሁ... የሰውነቴን ወይም የነፍሴን ትልቅ ክፍል እንዳጣሁ ይሰማኛል"

ከኤል-ፋሸር በስተ ምዕራብ 70 ኪ.ሜ. ርቀት ላይ ከሚገኝ የተፈናቀሉ ሰዎችን እያነጋገረን ነበር፤ ይህም ከ18 ወራት ከበባ በኋላ በጥቅምት ወር የመጨረሻ ሳምንት በሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ኃይል የተቆጣጠረው አካባቢ ነበር።

እአአ በሚያዝያ 2023 በፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ እና ሱዳን ጦር መሪዎች መካከል የተከሰተው የሥልጣን ሽኩቻ ወደ የእርስ በርስ ጦርነት ከተቀየረ በኋላ ጋር ውጊያ እየተካሄደ ነው።

በሳዑዲ ሆስፒታል ቢያንስ 460 ታካሚዎችና አጋሮቻቸው ላይ የተፈፀመው ግድያ በስፋት ከተፈጸሙት የጭካኔ ድርጊቶች መካከል እና በጣም አስደንጋጭ ከሆኑት ዘገባዎች አንዱ ነው። አንዳንዶቹ ጭፍጨፋዎች በፈጥኖ ደራሹ ተዋጊዎች የተቀረጹ እና በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ የተለጠፉ ናቸው።

የዓለም ጤና ድርጅት ባወጣው መግለጫ፣ በተዘገበው ግድያ እንዲሁም አራት ዶክተሮች፣ አንድ ነርስ እና አንድ ፋርማሲስት በድምሩ ስድስት የጤና ባለሙያዎች በመጠለፋቸው "በእጅጉ መደንገጡን" ገልጿል።

ፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ የኤል-ፋሸር ሆስፒታሎች በሙሉ እንደተተዉ በመግለጽ ክሶቹን ሐሰተኛ መረጃ ናቸው በሚል ውድቅ አድርጓቸዋል። በሆስፒታሉ ግቢ ውስጥ ሴት በጎ ፈቃደኞች ታካሚዎችን ሲንከባከቡ የሚያሳይ ቪዲዮ በመቅረጽ ክሱን አጣጥሏል።

በታዊላ የሚኖር ፍሪላንስ ጋዜጠኛ ለቢቢሲ ቃለመጠይቆችን ሰብስቧል።

አብዱ-ራቡ አህመድ ከጦርነቱ መጀመሪያ ጀምሮ የሕንፃዎቹን ክፍሎች ያወደሙ እና ዶክተሮችን፣ ነርሶችን እንዲሁም ታካሚዎችን ያቆሰሉ ተከታታይ የታንክ እና የድሮን ድብደባዎች ቢኖሩም በሳዑዲ ሆስፒታል ውስጥ መስራት መቀጠሉን ነግሮታል።

የፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ እገዳ እየተጠናከረ ሲሄድ የሕክምና ባለሙያዎች ትንሽ መጠን ያለው ምግብ እንደሚያገኙ እና አንዳንድ ጊዜም እህል በአፋቸው ሳይዞር ይሠሩ እንደነበር ይናገራል።

አብዛኞቹ የሕክምና ባለሙያዎች የአርኤስኤፍ ታጣቂዎች የመጨረሻውን ጥቃት ሲፈጽሙ ሸሹ።

"ተኩሱ የተጀመረው ከጠዋቱ 12 ሰዓት አካባቢ ነው" ሲል አብዱ-ራቡ አህመድ ተናግሯል።

"ሁሉም ሰላማዊ ዜጎች እና ወታደሮች ወደ ደቡባዊው አቅጣጫ ሄዱ። ነገር ዓለሙ ሁሉ የፍርሃት ነበር፣ እየሸሸን በነበረበት ወቅት ሳይቀር ድሮኖች በቦምብ እየደበደቡን ነበር። እንዲሁም ከባድ መድፍ ነበር፤ ብዙ ሰዎች በቦታው ሲሞቱ አይቻለሁ፤ ሊያድናቸው የሚችል ማንም ሰው አልነበረም።"

አብዱ ራቡ አህመድ ከሸሹት የሕክምና ሠራተኞች መካከል አንዳንዶቹ ከእሱ ጋር በታዊላ ሲደርሱ፣ ነገር ግን ብዙዎቹ በከተማው ሰሜን ምዕራብ በሚገኙ ቦታዎች ታስረዋል ብሏል።

አንዳንዶቹ አርኤስኤፍ እንደ ዋና ከተማ የሚገለገልባት እና በደቡባዊ ዳርፉር ወደምትገኘው ኒያላ ከተማ ተዛውረዋል ሲል ተናግሯል።

"ይህ ከምናውቃቸው የሥራ ባልደረቦች ያገኘሁት መረጃ ነው" ሲል ለቢቢሲ ተናግሯል። በኋላ ላይ በሆስፒታሉ የቀሩ የሕክምና ሠራተኞች መገደላቸውን እንደሰማም አክሏል።

አብዱ ራቡ አህመድ ብዙ ቤተሰቡን አጥቷል፤ በዚያ ቀን አንዲት እህትና ሁለት ወንድሞቹ ተገድለዋል፤ ወላጆቹም ጠፍተዋል።

"በኤል-ፋሸር ውስጥ ስለሚኖሩ ሰዎች ዕጣ ፈንታ በጣም እጨነቃለሁ" ሲል አክሏል።

"ተገድለው ሊሆን ይችላል። እናም [የሱዳን የአየር ኃይል] ድብደባዎችን ለመከላከል እንደ ሰው ጋሻ ሊያገለግሉ ይችላሉ"።

የተጠቀሰው ሆስፒታል እልቂት ዘገባዎች በሁለት የሱዳን የዶክተሮች ቡድን ሪፖርት የተደረገ ሲሆን፣ ቡድኖቹ በመሬት ላይ ያሉትን ምንጮች እና የኤል-ፋሸር አክቲቪስት ኔትወርክን ጠቅሰዋል።

የዬል ዩኒቨርሲቲ የሰብዓዊ ምርምር ላብራቶሪ የሳተላይት ምስሎች ሪፖርቶቹን አረጋግጠዋል።

ምስሎቹ በግልጽ መሬት ላይ ደም እና በሆስፒታሉ ግቢ ውስጥ አስከሬን የሚመስሉ ነጭ አንድ ላይ የተሰባሰቡ ነገሮችን ያሳያሉ።

እአአ ከሕዳር 1 ጀምሮ በተደረገ የሳተላይት ምስል ላይ፣ ነጭ ነገሮች በሆስፒታሉ ግቢ ውስጥ በተቆፈረ ቦታ ላይ ሲቀመጡ ታይተዋል። ከአምስት ቀን በኋላ ሕዳር 6 የተነሳው ምስል ደግሞ፣ እነዚህ ነገሮች በእሳት ተቃጥለው ጭስ ከአካባቢው ሲወጣ ያሳያል።

ቢቢሲ ቬሪፋይ በአቅራቢያው በሚገኘው የኤል-ፋሸር ዩኒቨርሲቲ የሕክምና ላብራቶሪ ሳይንስ ፋኩልቲ የተቀረፀውን ቪዲዮ እውነተኛነት አረጋግጧል። ወለሉ ላይ የተኛ አስከሬን እና አንድ የአርኤስኤፍ ተዋጊ በሕይወት ካሉት ሰዎች መካከል አንዱ ላይ ሲተኩስ ያሳያል።

የሱዳን ዶክተሮች ኔትወርክ ቃል አቀባይ ዶ/ር ሞሐመድ ኤልሼክ ለቢቢሲ እንደተናገሩት ይህ ሕንፃ ለሳዑዲ ሆስፒታል እና ለታካሚዎች አገልግሎት እየሰጠ ነበር።

አርኤስኤፍ የታገቱትን የጤና ባለሙያዎች ለመልቀቅ ገንዘብ ሲጠይቅ እንደነበር አስረድተዋል።

በዩኬ ውስጥ ለኤን ኤች ኤስ የሚሰሩት ዶ/ር ኤልሼክ "ከስድስቱ የታገቱ የሕክምና ባለሙያዎች መካከል አንደኛው ቤተሰቡ 30,000 ዶላር ማስለቀቂያ ገንዘብ ከፍሏል። እና አሁን በሰላም ወደ ታዊላ ከተማ ደርሷል" ብለዋል።

አክለውም "ሌላው ተገድሏል" ካሉ በኋላ ቡድኑ ስለ ቀሪዎቹ አራት ሰዎች ዕጣ ፈንታ ምንም መረጃ እንደሌለው ተናግረዋል።

አርኤስኤፍ ወደ ሳዑዲ ሆስፒታል ሲቃረብ ታካሚ የነበረው ሞሐመድ አብዱ-ቴያ፣ መሬት ከመተኛት በስተቀር ሌላ ምንም ማድረግ አይልቻለም ሲል የነበረውን ሁኔታ ይገልጻል።

ነገር ግን የመጨረሻው የአርኤስኤፍ ጥቃት በደረሰበት ጠዋት ከከተማው በእግር መሸሽ ችሏል።

አብዱ-ቴያ በጋርኒ ኬላ አካባቢ የአርኤስኤፍ ወታደሮች አስቁመዋቸው እንደፈተሿቸው እንዲሁ አብረውት የነበሩት ሁለቱ ሰዎች መወሰዳቸውን እርሱ ግን መለቀቁን ይናገራል።

"አልደበደቡኝም፣ ነገር ግን በጉዳቴ ምክንያት ብዙ የጠየቁኝ ይመስለኛል። 'ወታደር መሆንህን እናውቃለን፣ በመንገድ ላይ ትሞታለህ። ስለዚህ ሂድ' አሉኝ።"

አርኤስኤፍ ወደ ጋርኒ መድኃኒት ማምጣታቸውን የሚናገረው አብዱ-ቴያ ነገር ግን "በጣም ብዙ ሰዎች ተጎድተው ነበር፤-በየሰዓቱ ሁለት ወይም ሦስት ሰዎች ይሞታሉ" ብሏል።

"በደረስንበት ቀን ተሽከርካሪዎች መጥተው ሰዎችን ወደማይታወቁ ቦታዎች ወሰዱ። በአካል ደህና የሚመስል ማንኛውም ወጣት ተወሰደ።"

አብዱ-ቴያ "መኪና ካላቸው ሰዎች" ጋር ወደ ታዊላ መሄድ ችሏል።

ተሳፋሪዎችን 500,000 የሱዳን ፓውንድ ወይም 830 የአሜሪካን ዶላር አስከፍለው ቤተሰቦቻቸው ጋር ደውለው ገንዘብ እንዲልኩላቸው የስልካቸውን ኢንቴርኔት እንዳበሩላቸው ይናገራል። "ከእነሱ ጋር ሄድን፤ ምንም አልነበረንም። ዕቅድ እንኳን አልነበረንም።"

ብዙ ልጆች ከወላጆቻቸው ውጪ ወደ ታዊላ የተፈናቃዮች መጠለያ ደረሱ። የአስራ አምስት ዓመቷ ኢማን ከእነዚህ ውስጥ አንዱ ነበረች።

ለቢቢሲ እንደተናገረችውአባቷ በኤል-ፋሸር በተደረገ ድሮን ጥቃት ተገድሏል፤ እናቷና ወንድሟ ደግሞ ሲሸሹ በፈጥኖ ደራሽ ኃይሎች ተይዘዋል።

"ያልሞቱ ሰዎችን በሙሉ [አርኤስኤፍ] ተሽከርካሪ በላያቸው ላይ ነዱባቸው" ብላለች። "ንብረቶቻችንን ወስደው ሁላችሁም ወታደሮች ናችሁ ብለውናል። ወንድሜን ደበደቡትና በሰንሰለት አነቁት።

"እናቴን ሊመቱ ፈልገው ነበር። እሷም 'ሂዱ፣ ወደ እናንተ እመጣለሁ' አለችን።" ወደ ተሽከርካሪ ገብተን ሄድን። ወንድሜ ወደ ተሽከርካሪው እንዲገባ አልፈቀዱልንም። ትተናቸው ሄደናል።"

ኢማን አምልጣለች ነገር ግን ሌሎች እንደሷ ማምለጥ ያልቻሉ ሴቶችን ተመልክታለች።

"አንዳንድ ሴቶችን ወሰዱ። በተሽከርካሪዎቻቸው ከወሰዷቸው በኋላ አንዳንዶቹን በቢላ ወጉዋቸው። እናቶቻቸው ምንም ማድረግ በማይችሉበት ውስጥ ሌሎቹም ተወስደዋል።"

የተረፉ ሴቶች የቡድን መደፈርን እና የወጣት ሴቶችን መጥለፍ አስፈሪ ታሪኮችን ተናግረዋል።

ሌላኛዋ የ14 ዓመቷ ታዳጊ ሳማር በጋርኒ ኬላ በተፈጠረው ሁከት እናቷ እንዳጣች እና አባቷም እንደተያዘ ተናግራለች።

በኤል-ፋሸር ወደሚገኘው የሕፃናት ሆስፒታል እንደተወሰደ ተነግሯታል።

ያ ሕንፃ እንደ አርኤስኤፍ የማጎሪያ ማዕከል ሆኖ ሲያገለግል እንደነበር ተዘግቧል። እንዲሁም የዬል ተመራማሪዎች የሳተላይት ምስሎች ግልጽ የሆኑ የአስከሬን ክምችቶች እንዲሁም የጅምላ መቃብር ሊሆኑ የሚችሉ የመሬት ቁፋሮዎች የግድያ ማስረጃዎችን የሚያሳዩበት ቦታ ነው።

አርኤስኤፍ እነዚህን ክሶች ለመቃወም ቪዲዮዎችን አውጥቷል። በኤል-ፋሸር የሚገኘው የሕፃናት ሆስፒታል ታካሚዎችን ለመቀበል ዝግጁ መሆኑን አስታውቋል።

አንደኛው ቪዲዮ አንድ ሰው በበሩ ውጭ ቆሞ በሆስፒታል ጽዳት ውስጥ ያሉ ዶክተሮችን ያሳያል።

"እነዚህ የሕክምና ባለሙያዎችና ካድሬዎች፣ ታጋቾች አይደሉም" ይላል ሰውዬው። "እንደ ጦርነት ታጋቾች አንወስዳቸውም። ነፃ ናቸው። ሕክምና የመስጠት ነፃነት አላቸው።"

በቪዲዮው ውስጥ ራሱን የሚያስተዋውቀው ሌላ ሰው፣ በኤል-ፋሸር ዩኒቨርሲቲ የሕፃናት ሕክምና እና የሕፃናት ጤና ተባባሪ ፕሮፌሰር ዶ/ር ኢስሃቅ አብዱል ማህሙድ እንደሆነ ይናገራል። "የሕክምና አገልግሎት የሚያስፈልገውን ማንኛውንም ሰው ለመርዳት እዚህ አለን።

"ከፖለቲካ ወጥተናል። ወታደሮችም ሆኑ [ሲቪሎች] እነሱን ለመርዳት ዝግጁ ነን።"

የሱዳን ዶክተሮች ኔትወርክ ዶ/ር ኤልሼክ የአርኤስኤፍ ቪዲዮዎችን ፕሮፓጋንዳ ናቸው ሲሉ ውድቅ አድርገውታል።

በታዊላ የሚገኘው የሳዑዲ ሆስፒታል የላቦራቶሪ ቴክኒሻን አብዱ አህመድ ያየውን ያውቃል፤ ብዙ ነገር አይቷል።

"ከተከሰተው ሁሉ እና ካየሁት ነገር ሁሉ በኋላ ወደ ኤል-ፋሸር የመመለስ ተስፋ የለኝም" ይላል። ትንሽ ተስፋ ቢኖርም እንኳ፣ ፊት ለፊቴ የሆነውን አስታውሳለሁ"።