የወርቅ ዋጋ ለመጀመሪያ ጊዜ ከ5,000 ዶላር አለፈ

የአሜሪካ እና የሰሜን አትላንቲክ ጦር ቃልኪዳን (ኔቶ) ውጥረትን ተከትሎ የወርቅ ዋጋ ለመጀመሪያ ጊዜ ከ5,000 ዶላር በላይ ሆነ።

እአአ በ2025 የወርቅ ዋጋ በአንድ ጊዜ ከ60% በላይ ጨምሮ እንደነበር አይዘነጋም።

ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ግሪንላንድን ለመጠቅለል ማቀዳቸው የፋይናንስ ዘርፉ ላይ አለመረጋጋት አስከትሏል።

ካናዳ ከቻይና ጋር የንግድ ስምምነት የምትፈርም ከሆነ 100% ታሪፍ እንደሚጥሉ የዛቱት ያሳለፍነው ቅዳሜ ነበር።

በባለሃብቶች ዘንድ ወርቅ እና ሌሎችም የከበሩ ማዕድናት አስተማማኝ ንብረት ተደርገው ይወሰዳሉ።

ያለፈው ሳምንት አርብ የብር ዋጋ ለመጀመሪያ ጊዜ ከ100 ዶላር በላይ ሆኗል። ባለፈው ዓመት የብር ዋጋ 150% ጨምሮ ነበር።

ከፍተኛ የዋጋ ንረት፣ የአሜሪካ ዶላር መዳከም እንዲሁም የአሜሪካ ብሔራዊ ባንክ የወለድ መጠንን በድጋሚ መቀነሱ የከበሩ ማዕድናት ተፈላጊነት እንዲጨምር ምክንያት ከሆኑ ጉዳዮች መካከል ይጠቀሳሉ።

የዩክሬን እና ጋዛ ጦርነት፣ አሜሪካ የቬንዝዌላ ፕሬዝዳንት ኒኮላስ ማዱሮን በቁጥጥር ሥር ማዋሏም የወርቅ ዋጋ እንዲንር አድርገዋል።

ዓለም አቀፉ የወርቅ ንግድ ማኅበር እንደሚለው፤ በሰው ልጆች ዘንድ እስካሁን ድረስ ጥቅም ላይ የዋለው 216,265 ቶን ወርቅ ብቻ ነው።

ይህ የወርቅ መጠን ከሦስት እስከ አራት የኦሊምፒክ መዋኛ ገንዳዎችን ይሞላል።

የማዕድን ማውጣት ቴክኖሎጂ እየተሻሻለ ከመምጣቱ ጋር በተያያዘ ከ1950 ወዲህ አብዛኛውን የዓለም የወርቅ ክምችት ማግኘት ተችሏል።

የአሜሪካ ጂኦሎጂካል ሰርቬይ መረጃ እንደሚያሳየው፤ ተጨማሪ 64,000 ቶን ወርቅ ማውጣት የሚቻል ቢሆንም በቀጣይ ዓመታት በብዛት ጥቅም ላይ የሚውለው ብረት ይሆናል።

የኤቢሲ ሪፋይነሪ ኃላፊ ኒኮላስ ፍራፔል "የወርቅ ባለቤት መሆን ቦንድ ወይም የኩባንያ ድርሻ እንደመግዛት አይደለም። ወርቅ መረጋጋት በራቀው ዓለም ቋሚ ንብረት ነው" ይላሉ።

ከ1979 ወዲህ የወርቅ ከፍተኛ ዓመታዊ ሽያጭ የተመዘገበው በ2025 ነው።

የትራምፕ ታሪፍን ጨምሮ ሰው ሠራሽ አስተውሎት የፈጠረው ስጋት እና ሌሎችም ዓለም አቀፍ ክስተቶች ወርቅ በተከታታይ ዋጋው እንዲንር አድርገዋል።

'ሜታል ፎከስ' የተባለው የጥናት ተቋም ባለሙያ የሆኑት ኒኮስ ካቪልስ "የአሜሪካ ፖሊሲ የፈጠረው መደናገር ዋነኛው ምክንያት ነው ብዬ አምናለሁ" ሲሉ ያብራራሉ።

ከምጣኔ ሃብት አለመረጋጋት በተጨማሪ ባለሃብቶች የወለድ መጠን ሲቀንስ የሚፈጠርባቸው ስጋት የወርቅ ዋጋ እንዲጨምር ከሚያደርጉ ዋነኛ ምክንያቶች መካከል ይጠቀሳሉ።

የአሜሪካ ብሔራዊ ባንክ ዘንድሮ ሁለት ጊዜ የወለድ መጠን እንደሚቀንስ ይጠበቃል።

'ፔፐርስቶን' በተባለው የጥናት ተቋም ተመራማሪ የሆኑት አሕመድ አሲሪ "ገንዘብን በቦንድ ግዢ ማስቀመጥ ዋጋ ቢስ እየሆነ መጥቷል። ስለዚህም ብዙዎች ወርቅን ይመርጣሉ" በማለት ያስረዳሉ።

ወርቅ እያከማቹ ያሉት ባለሃብቶች ብቻ ሳይሆኑ ብሔራዊ ባንኮችም ጭምር ናቸው።

ወርልድ ጎልድ ካውንስል ይፋ ባደረገው መረጃ መሠረት፤ አምና በብሔራዊ ባንኮች የተከማቸው ወርቅ በመቶ ቶኖች ይለካል።

የሜታል ፎከስ ተቋም ባለሙያው ኒኮስ ካቪልስ "የአሜሪካ ዶላር ያለው ዋጋ ሲወርድ ሌላኛው አማራጭ ወርቅ ነው" ይላሉ።

የኤቢሲ ሪፋይነሪ ኃላፊ ኒኮላስ ፍራፔል በበኩላቸው ዘንድሮ የወርቅ ዋጋ ቢጨምርም "እንደ አዲስ እየተዋቀረ ያለው ዓለም አቀፍ ገበያ" ዋጋው እንዲቀንስ ሊያደርግ የሚችልበትም ዕድል እንዳለ ይናገራሉ።

ወርቅ በባለሃብቶች ከሚሰጠው ዋጋ ጎን ለጎን የተለያዩ ማኅበረሰቦች ባህላዊ መገለጫ ተደርጎ ይወሰዳል።

በዓመት በዓሎች፣ በሠርግ እና በሌሎችም ክንውኖች በወርቅ ደምቆ መታየት የተለመደ ነው። ለምሳሌ በሕንዳውያን ዲዋሊ ክብረ በዓል ላይ በርካቶች በወርቅ ያጌጣሉ።

የሞርጋን ስታንሊ አሐዝ እንደሚያሳየው ከሆነ በአሜሪካ 3.8 ትሪሊዮን የሚያወጣ የወርቅ ይዞታ ያለው በሕንዳውያን ዘንድ ነው። ይህም ከጠቅላላ የአገር ውስጥ ምርት 88.8% ይሸፍናል።

በቻይና ወርቅ መግዛት ከመልካም ዕድል ጋር ይተሳሰራል። በቻይናውያን አዲስ ዓመት አካባቢ የወርቅ ፍላጎት የሚጨምር ሲሆን፤ ቻይና በዓለም የወርቅ ገበያ ቀዳሚዋ ሸማች አገርም ናት።