ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የተባበሩት መንግሥታት የሱዳን የጅምላ ግድያ ፈጻሚዎችን ተጠያቂ የሚያደርግ ምርመራ እንዲካሄድ ወሰነ
የተባበሩት መንግሥታት የሰብአዊ መብቶች ምክር ቤት በሱዳኗ ኤል-ፋሸር ከተማ እንደተፈጸመ የተገለጸውን የጅምላ ግድያ በተመለከተ አዲስ እና ገለልተኛ ምርመራ እንዲካሄድ በሙሉ ድምጽ ወሰነ።
የተመድ የሰብአዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽነር የሆኑት ቮልከር ተርክ፤ "[ያሰማነው] የማንቂያ ደውል አዳማጭ አላገኘም" ሲሉ አርብ ዕለት በተካሄደው አስቸኳይ ጉባኤ ላይ ተናግረዋል።
"በኤል-ፋሸር መሬት ላይ የፈሰሰው ደም ከጠፈር ፎቶግራፍ ተነስቷል። በዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ላይ የተመዘገበው ክሽፈት በግልጽ የማይታይ መሆኑ [ድርጊቱ ያደረሰውን] ጉዳት አይቀንሰውም" ሲሉም ተደምጠዋል።
ከሁለት ዓመት በፊት በሱዳን የእስር በርስ ጦርነት ከተነሳበት ጊዜ ጀምሮ 150,000 ሰዎች ተገድለዋል። 12 ሚሊዮን ሱዳናውያን ደግሞ ከመኖሪያቸው ለመፈናቀል ተገድደዋል።
አዲሱ ምርመራ የኤል-ፋሸሩ ግድያ እንዲፈጸም ማን ትዕዛዝ እንደሰጠ እና ማን እንዳካሄደው የመለየት ኃላፊነት ተጥሎበታል። በምርመራው የሚደረስባቸው ግኝቶች ለዓለም አቀፉ የወንጀል ፍርድ ቤት ሊቀርቡ ይችላል።
የሰብአዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽነር የሆኑት ተርክ፤ የሱዳንን ጦርነት "የሚያቀጣጥሉ" እንዲሁም ከእልቂቱ "የሚያተርፉ" ያሏቸውን ግለሰቦች እና ኩባንያዎች አስጠንቅቀዋል። ይሁን እንጂ ጦርነቱን እየደገፉ ያሉ ሌሎች አገራትን በተመለከተ የተጠቀሰ ነገር አለመኖሩ ቅሬታ አስነስቷል።
የተባበሩት አረብ ኢምሬቶች ለሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ኃይል (አርኤስኤፍ) መሣሪያዎችን በማጓጓዝ ትከሰሳለች። ኢራን ደግሞ ለአገሪቱ ጦር መሣሪያ ታቀርባለች ውንጀላ ቀርቦባታል።
ከዚህም ባሻገር፤ ባጋጠመው የገንዘብ እጥረት ምክንያት በሱዳን የሚያከናውነውን የሰብአዊ ድጋፍ ለማስቀጠል ተግዳሮት ያጋጠመው የተባበሩት መንግሥታት፤ ታማኝ ምርመራ ለማካሄድ አቅም ሊያጥረው ይችላል የሚል ስጋት እየተነሳ ነው።
ለ18 ወራት ከበባ ውስጥ ያሳለፈችው ኤል-ፋሸር ባለፈው ወር በፈጥኖ ደራሹ ኃይል ቁጥጥር ሥር ገብታለች። ኤል-ፋሸር የሱዳን ጦር እና አጋሮቹ በዳርፉት የያዟት ብቸኛ ከተማ ነበረች።
አርኤስኤፍ፤ በከተማዋ እና በሌሎች የዳርፉር አካባቢዎች አረብ ያልሆኑ የማኅበረሰብ ክፍሎችን ዒላማ አድርጓል የሚል ውንጀላ ይቀርብበታል። ቡድኑ ግን ይህንን ክስ አይቀበልም።
የዚህ ጦርነት አንዱ አስከፊ ገጽታ፤ አስከፊ ግፎችን የሚያሳዩ ቪዲዮዎች እና ፎቶዎች በከፍተኛ መጠን በማኅበራዊ ሚዲያ ገጾች ላይ የሚለቀቁ መሆኑ ነው። እነዚህ ቪዲዮዎች ብዙውን ጊዜ የሚቀረጹት ድርጊቱን በሚፈጽሙት ሰዎች ነው።
እነዚህ የዲጂታል ማስረጃዎች ተተንትነው ወንጀል ፈጻሚዎችን ወደ ፍርድ ለማቅረብ እንደሚውሉ ተመራማሪዎች ይናገራሉ።
ላላፉት 20 ዓመታት የሱዳንን ሁኔታ ሲከታተሉ የቆዩት የመንግሥታቱ ድርጅት የእውነታ አፈላላጊ ተልዕኮ አባል ሞና ሪሽማዊ፤ "የሱዳን፤ በተለይም የኤል-ፋሸር ሕዝብ እየተጋፈጠ ያለው ሁኔታ ከዚህ በፊት በጭራሽ ተመልክቼው የማላውቀው ነው" ብለዋል።
በአሁኑ ሰዓት በዳርፉር ያጋጠመው መከራ መጠን ከ20 ዓመት በፊት የጃንጃዊድ ታጣቂዎች በክልሉ የዘር ማጥፋት በፈጸሙበት ጊዜም የበለጠ መሆኑን ከቢቢሲ ኒውስዴይ ፕሮግራም ጋር ባደረጉት ቆይታ ተናግረዋል።
በኤል-ፋሸር የጅምላ ግድያ በመፈጸም የሚከሰሰው አርኤስኤፍ መነሻው በዳርፉት የዘር ማጥፋት የፈጸመው የጃንጃዊድ ታጣቂ ቡድን እንደሆነ አይዘነጋም።
በዚያን ወቅት ጥቃቶቹ ያተኩሩ የነበረው መንደሮች ላይ መሆኑን የሚያስረዱት ሪሽማዊ፤ አሁን ግን አርኤስኤፍ መላ ከተማውን እና በመቶ ሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን ያስጠለሉ የተፈናቃይ ካምፖችን ዒላማ ማድረጉን ገልጸዋል።
"አስከፊ የጅምላ ግድያ፣ መድፈር እና ስቅይት፣ ስወራ፣ የሰዎች መጥፋት [አጋጥሟል]። ይህ ሁሉ የሆነው ከ18ቱ ከቆየው ከበባ እና ርሃብ በተጨማሪ ነው" ሲሉም የሁኔታውን ክብደት ጠቅሰዋል።