ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ለሱዳኑ አርኤስኤፍ የሚሰጠው የጦር መሣሪያ አቅርቦት እንዲቋረጥ አሜሪካ ዓለም አቀፍ ጥሪ አቀረበች
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ በኤል-ፋሸር በጅምላ ግድያ የተከሰሰው ለሱዳኑ የፈጥኖ ደራሽ ኃይሎች (አርኤስኤፍ) የጦር መሣሪያ አቅርቦትን እንዲቋረጥ ዓለም አቀፍ እርምጃ እንዲወሰድ ጥሪ አቅርበዋል።
በካናዳ በተደረገው የቡድን 7 የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ስብሰባ መዝጊያ ላይ ሩቢዮ አርኤስኤፍ በሲቪሎች ላይ ግድያ፣ አስገድዶ መድፈር እና ወሲባዊ ጥቃትን ጨምሮ ስልታዊ ጭካኔዎችን ፈጽሟል ብለዋል።
የሱዳን ጦር የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ ከአፍሪካ አገራት የተላኩ የጦር መሣሪያዎችን እና ቅጥረኞችን በመስጠት አርኤስኤፍን እያስታጠቀች ነው ሲል ከሷል። የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ እና አርኤስኤፍ እነዚህን ክሶች በተደጋጋሚ ውድቅ አድርገዋል።
አርኤስኤፍ ከ2023 ጀምሮ በመሪዎች መካከል የተፈጠረው የስልጣን ሽኩቻ ወደ የእርስ በርስ ጦርነት ከተቀየረበት ጊዜ ጀምሮ ከሱዳንን ጦር ጋር እየተዋጋ ይገኛል።
የሩቢዮ አስተያየት እስካሁን ድረስ በትራምፕ አስተዳደር ስለሱዳን ጦርነት እና ስለአርኤስኤፍ ድርጊቶች በግልጽ ከተነገሩት መካከል ጠንካራው ቢሆንም ምን ያህል ተጽዕኖ እንደሚኖረው ግን ግልጽ አይደለም።
ሁለቱ ወገኖች ባለፈው ሳምንት በአሜሪካ የተደገፈውን የሰብአዊነት ስምምነት ቢቀበሉም ስምምነቱ በአርኤስኤፍ ተጥሷል።
ኤል-ፋሸር ከ18 ወራት ከበባ በኋላ በአርኤስኤፍ ቁጥጥር ስር የገባ በመሆኑ አብዛኘው የምዕራብ ዳርፉር ክልል ውስጥ ያሉትን ከተሞች ቡድኑ ይቆጣጠራል።
ጭፍጨፋ እንደተፈጸመበት ከሚነገርበት ከተማ ጥቂቱ ሕዝብ ብቻ መሸሹ ታውቋል። አስከሬኖች እና በደም የተበከለ መሬት መኖሩን የሳተላይት ምስሎች ያሳያሉ።
በሰፊው የዳርፉር ክልል ውስጥ ያሉ አረብ ያልሆኑ ቡድኖች በአርኤስኤፍስ ኢላማ መደረጋቸውን እና ይህም እንደ የዘር ማጥፋት ይቆጠራል ሲሉ አሜሪካ እና የሰብአዊ ቡድኖች ገልጸዋል።
ሩቢዮ በኤል-ፋሸር እጅግ አስፈሪ በሆነው የአርኤስኤፍ ድርጊት ሴቶችና ህጻናት ኢላማ ሆነዋል ብለዋል።
ሩቢዮ "በሴቶች፣ በህፃናት እና በንፁሃን ዜጎች ላይ እጅግ አስፈሪ የሆኑ የፆታዊ ጥቃት እና የጭካኔ ድርጊቶችን እየፈጸሙ ነው። እናም በፍጥነት መቆም አለበት" ሲሉ ለጋዜጠኞች ገልጸዋል።
"ለማስቆም የምንችለውን ሁሉ እናደርጋለን። አጋር አገራት ከእኛ ጎን እንዲሆኑ አበረታተናል።"
አቡዳቢ የአርኤስኤፍ ዋና የጦር መሳሪያ አቅራቢ እንደሆነች እና በዓለም አቀፍ ሚዲያዎች በተደረጉ ምርመራዎች ተደርሶበት በተባበሩት መንግስታት መረጋገጡን የሚያሳይ ማስረጃ ቢኖርም፤ ሩቢዮ አገሪቱን በይፋ ከመተቸት ተቆጥበዋል።
የትራምፕ አስተዳደር ከተባበሩት አረብ ኤምሬትስ እንዲሁም ከግብፅ እና ከሳዑዲ አረቢያ ጋር በመሆን ጦርነቱን ለማስቆም እየሠራ ነው። "ቋድ" በመባል የሚታወቁት አገሮች የሱዳን ጦር መንግስት አጋሮች ናቸው።
"በዚህ በጋዜጣዊ መግለጫ ላይ የማንንም ስም ማንሳት አልፈልግም። ምክንያቱም የምንፈልገው ጥሩ ውጤት ማግኘት ነው" ሲሉ ሩቢዮ ተናግረዋል። ነገር ግን በግልጽ "[በጦር መሳሪያ አቅራቢነት] የሚሳተፉ ወገኖች እነማን እንደሆኑ እናውቃለን… ለዚህም ነው ሌሎች አገሮች የቋድ አካል የሆኑት" ብለዋል።
በመስከረም ወር ቋድ ለሦስት ወራት የሚቆይ የሰብዓዊ ተኩስ ማቆም ስምምነት እና ለዘጠኝ ወራት የሚቆይ የሲቪል አገዛዝ ሽግግር ሃሳብ አቅርቧል።
አርኤስኤፍ ኤል-ፋሸርን እስኪይዝ ድረስ ጠብቆ የተኩስ ማቆም ስምምነት ላይ መድረሱን አስታውቋል። የሱዳን ጦር በቋድ ውስጥ የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ መገኘትን እንደሚቃወም ቢናገርም ስምምነቱን እንደሚያጤን ተናግሯል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ጦርነቱ ምንም አይነት መቀዛቀዝ አላሳየም።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ግድያዎቹን በተመለከተ የተወሰኑ አካላትን ለመውቀስ የተደረገውን ሙከራ ውድቅ አድርገዋል። ይህ የተሳሳተ ሲሆን ጥቃቶቹ ስልታዊ ናቸው ብለዋል።
በቢቢሲ ስለሚከሰተው የጭካኔ መጠን ሲጠይቃቸውም አሜሪካ ከኤል-ፋሸር እንደሚሸሹ የሚጠበቁ በሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ሞተዋል ወይም በተመጣጠነ ምግብ እጥረት ምክንያት ለመሸሽ አልቻሉም የሚል ሃሳብ አላት ብለዋል።
አርኤስኤፍ የራሱ የጦር መሳሪያ ማምረቻ ተቋማት ስለሌሉት በውጭ ድጋፍ ላይ ተመስርቷል። በመሆኑም የጦር መሳሪያ የሚያቀርቡ አገሮች ድጋፋቸውን እንዲያቆሙ ጥሪ አቅርበዋል።
አርኤስኤፍ ሃሳቡን ባወገዘበት ረጅም መግለጫ "ወገንተኛ መግለጫ" ሲል ጠርቶታል።
ቡድን ከውጭ ወገኖች ድጋፍ ያገናል መባሉን በተደጋጋሚ ክዶ፤ የሰራዊቱን የተኩስ አቁም ስምምነት ውድቅ ማድረግ ለመሸፈን የሚደረጉ ሙከራዎችን እንደማይቀበል ተናግሯል።
"ሁሉንም የተኩስ አቁም ጥረቶች ውድቅ ያደረገው እና ለመሳተፍ ፈቃደኛ ያልሆነው ወገን ከአሸባሪው እስላማዊ ንቅናቄ ጋር የተቆራኘው ሠራዊት ነው" ሲል ገልጾ "ሰራዊታችንም በይፋ አጽድቆ ምላሽ ሰጥቷል። እስከ ዛሬ ድረስ ከአሜሪካ ወገን ምንም አይነት ምላሽ አላገኘንም። ስለዚህ ሌላኛው ወገን የት ነው? ምላሹስ ምንድን ነው?"
የጂ7 የጋራ መግለጫ በሱዳን የተከሰተውን ጦርነት አውግዞ፤ በጦር ሠራዊቱ እና በአርኤስኤፍ መካከል የተፈጠረው ጦርነት "በዓለም ላይ ትልቁን የሰብአዊ ቀውስ" እንዳስከተለ ተናግሯል።
እስካሁን ድረስ ከ150 ሺህ በላይ ሰዎች ሲገደሉ፤ ወደ 12 ሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎች ለመፈናቀል ተገደዋል።
በዚህ ሁለት ዓመት የእርስ በርስ ጦርነት ወቅት ወደ አገሪቱ የሚገቡ የጦር መሳሪያዎችን በተመለከተ የተለያዩ ባለሙያዎች ሃሳባቸውን ሰጥተዋል።
አምነስቲ ኢንተርናሽናል በሰርቢያ፣ በሩሲያ፣ በቻይና፣ በቱርክ፣ በየመን እና በተባበሩት አረብ ኤምሬትስ የተመረቱ የጦር መሳሪያዎች በሱዳን ውስጥ ጥቅም ላይ እየዋሉ መሆናቸውን የሚያሳይ ማስረጃ እንዳገኘ ተናግሯል።
መሣሪያው በተባበሩት አረብ ኤምሬትስ፣ በቻድ፣ ከዚያም ወደ ዳርፉር እንደሚያቀና በተባበሩት መንግስታት ባለሙያዎች የተወጣጠ ቡድን አሳውቋል።
በተለይም የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ ለአርኤስኤፍ የጦር መሳሪያ እና ድጋፍ በመስጠት ተከሳለች። አርኤስኤፍ ደግሞ የተባበሩት አረብ ኤምሬትን ለሕገወጥ የወርቅ ሽያጭ ገበያ አድርጎ ተጠቅሟል የሚል ክስ ቀርቦበታል።
ሩቢዮ ረቡዕ ዕለት እንደተናገሩት ከሆነ ለአርኤስኤፍ የሚሰጠው እርዳታ "ለአርኤስኤፍ የሚደርሰውን መሣሪያ ብቻ የሚመለከት ሳይሆን በግዛታቸው እንዲያልፍ የሚፈቅዱ አገሮችም የሚጨምር ነው" ብለዋል።
በግጭቱ ውስጥ የሌሎች ተዋናዮችን ተሳትፎ "መቀነስ" እንደማይፈልጉም ተናግረዋል። "ይህም ኢራናውያንን ሊያካትት ይችላል፣ ቢያንስ ገንዘብ እና የጦር መሳሪያዎች ወደ ሌላኛው ወገን ያደርሳሉ" ሲልሉ ስለሱዳን ጦር ገልጸዋል።
ሁሉም ወገኖች እነዚህን ክሶች ይክዳሉ።
ከሁለት ሳምንት በፊት የእንግሊዝ መንግስት በብሪታንያ የተመረቱ የጦር መሳሪያዎች በአርኤስኤፍ እጅ ውስጥ እየገቡ እና ለጥቃት መፈጸሚያነት እየተጠቀሙባቸው ነው የሚል ክስ ከቀረበበት በኋላ ከህግ አውጪዎቹ ተቃውሞ ደርሶበታል።
አንድ የፓርላማ አባል "ኤምሬት አርኤስኤፍን እያስታጠቀች እንዳልሆነ እስክታረጋግጥ ድረስ ወደ አገሪቱ የሚላከው የጦር መሳሪያ መቆም አለበት" ሲሉ ባቀረቡት ጥያቄ መሰረት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኢቬት ኩፐር "ዩናይትድ ኪንግደም ማንኛውንም የጦር መሳሪያ ዝውውር መከላከልን ጨምሮ በጦር መሳሪያ ሽያጭ ላይ እጅግ በጣም ጠንካራ ቁጥጥር አላት። ይህንን በጣም በቁም ነገር መያዛችንን እንቀጥላለን" ሲሉ መልሰዋል።
ከ2004 ጀምሮ በአርኤስኤፍ ዋነኛ መሠረት በሆነው ዳርፉር ላይ የተባበሩት መንግስታት የጦር መሳሪያ ማዕቀብ ቢጥልም ማዕቀቡ በመላው አገሪቱ እንዲሆን ከሰብአዊ መብቶች ቡድኖች የቀረበው ጥሪ ምላሽ አላገኘም።