ኢትዮጵያ አሳልፋ የሰጠችው ኤርትራዊ ሕገ ወጥ የሰዎች አዘዋዋሪ ኔዘርላንድስ ውስጥ 20 ዓመት ተፈረደበት

ኢትዮጵያ ከሦስት ዓመት በፊት ለኔዘርላንድስ አሳልፋ የሰጠችው ተወልደ ጎይቶም የተባለው ኤርትራዊ ሕገ ወጥ የሰዎች አዘዋዋሪ በአገሪቱ ፍርድ ቤት ከፍተኛ የሆነው የ20 ዓመት እስራት ተፈረደበት። ጉዳዩን የተመለከተው የኔዘርላንድስ ፍርድ ቤት ግለሰቡ እና ግብረ አበሮቹ ስደተኞች ላይ "ጨካኝ፣ ኃይል የተሞላበት እና ስብእናን የሚያዋርድ" ድርጊቶችን ፈጽመዋል ብሏል።

ፍርድ ቤቱ አማኑኤል ዋሊድ በሚል መጠሪያም የሚታወቀው የ42 ዓመቱ ተወልደ ጎይቶም ላይ የፍርድ ውሳኔውን ያስተላለፈው ትናንት ማክሰኞ ጥር 19/2018 ዓ. ም. ነው። ፍርድ ቤቱ የጥፋተኝነት ውሳኔውን ያስተላለፈው፤ ግለሰቡ ሜዲትራኒያን ባሕርን አቋርጠው ወደ አውሮፓ ለመግባት የሚጥሩ ስደተኞችን የሚያሰቃይ እና በኔዘርላንድስ ከሚገኙ ቤተሰቦቻቸው ገንዘብ የሚቀበል የወንጀል ድርጅት ሲመራ እንደነበር በመረጋገጡ ነው።

ተወልደ ከሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውር ጋር በተያያዘ ሲፈረድበት ይህ የመጀመሪያው አይደለም። ኢትዮጵያ ውስጥ በቀረቡበት ተያያዥ አምስት ክሶች ጥፋተኛ ተብሎ የ18 ዓመት እስር ተፈርዶበት ነበር። ጥቅምት 2015 ዓ. ም. ላይ ደግሞ ለኔዘርላንድስ ተላልፎ ተሰጥቷል።

ተወልደ፤ ኔዘርላንድስ ውስጥ በነበረው የፍርድ ሂደት ላይ ምስክሮች የጠቀሱት አደገኛው የሰዎች ዝውውር መረብ መሪ እርሱ እንዳልሆነ በመግለጽ ተከራክሯል። ይህ የወንጀል መረብ ቡድን ስደተኞችን ከሊቢያ ወደ አውሮፓ፣ ከዚያም ጥገኝነት ወደሚጠይቁባት ኔዘርላንድስ ሲያጓጉዝ የነበረ ነው።

ጉዳዩን የተመለከተው ፍርድ ቤት ግን የተከሳሹን መከላከያ ውድቅ አድርጓል። ግለሰቡ በሚመራው መረብ የተጠለፉ ስደተኞች ሊቢያ በሚገኙ ካምፖች ውስጥ ታስረው መቆየታቸውን እንዲሁም ለቤተሰቦቻቸው ደውለው ገንዘብ እንዲያስልኩ መገደዳቸውን ፍርድ ቤቱ ገልጿል። " ወደ አውሮፓ መተላለፊው ገንዘብ ሲከፈል ብቻ ነበር ስደተኛው ከካምፑ እንዲወጣ እና ጉዞውን እንዲቀጥል የሚፈቀድለት" ሲሉም አስረድቷል።

ዋና ዳኛ ረኔ ሜላርድ፤ በተፈጸሙት ወንጀሎች ባህሪ እና ስፋት የተነሳ ጉዳዩ "በተለየ ሁኔታ እጅግ ከባድ" እንደሆነ መናገራቸውን የዜና ወኪሉ አሶሺየትድ ፕሬስ ዘግቧል።

"በአንድ በኩል የኔዘርላንድስን እና የአውሮፓን የኢሚግሬሽን ፖሊሲ በከፍተኛ ሁኔታ በመጣሱ፣ በሌላ በኩል ደግሞ በተለይ አንተ እና ግብረ አበሮችህ በስደተኞች ላይ በፈጸማችሁት ጭካኔ የተሞላበት እና አዋራጅ ድርጊት" ሲሉ ጉዳዩን ከባድ ያደረጉትን ምክንያቶች ጠቅሰዋል።

አክለውም፤ "ለተሻለ ሕይወት ከሚጥሩ ደካማ እና ረዳት የሌላቸው ሰዎች የሚቻለውን ያህል ገንዘብ ለመበዝበዝ ስትሉ፤ በድርጊታችሁ ምሕረት የለሽ፣ ሕሊና ቢሶች እና ለሰው ልጅ ክብር ደንታ የሌላችሁ ነበራችሁ" ብለዋል።

በእነዚህ ድርጊቶች ጥፋተኛ የተባለው ተወልደ ጎይቶም ከ20 ዓመት እስራት በተጨማሪ 35,000 ዶላር ካሳ እንዲከፍል ተወስኖበታል። የተላለፈው ፍርድ ላይ የይግባኝ አቤቱታ ለማቅረብ የሁለት ሳምንት ጊዜ እንዳለው ተገልጿል።

የዓለም አቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት በኤክስ ገጹ ባሰፈረው መልዕክት በተሰጠው ውሳኔ መደሰቱን ገልጿል። የስደተኞች መብት ተሟጋች የሆኑ ሦስት ቡድኖችም በጋራ ባወጡት መግለጫ የፍርድ ውሳኔውን እንደሚቀቡት አስታውቀዋል።

ግለሰቡ፤ በዋነኛነት ሊቢያ ውስጥ በሚገኝ ባኒ ዋልዲ የተባለ አካባቢ ላይ የማጎሪያ ካምፕን ሲያንቀሳቅስ የነበረ የወንጀል መረብን ሲመራ እንደበር ያስታወሱት ሦስቱ ቡድኖች፤ ከተጎጂዎቹ መካከል አብዛኛዎቹ ኤርትራውያን እንደሆኑ እና ሌሎችም የምሥራቅ አፍሪካ ዜጎችም እንደሚገኙበት ገልጸዋል።

የተወልደ የፍርድ ሂደት እስካሁን ድረስ ውሳኔ ሳያገኝ የቆየው ግብረ አበሩ እንደሆነ የተገለጸው ኪዳነ ዘካርያስ ኃብተማርያም በተባለው ሌላኛው ተከሳሽ ምክንያት ነው።

ኪዳነ ዘካርያስ ኃብተማርያምም ኢትዮጵያ ውስጥ የፍርድ ሂደቱ እየታየ ሳለ አምልጦ ከአገር ውጥቶ ነበር። ይሁን እንጂ ኢትዮጵያ ውስጥ በሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውር ወንጀል በሌለበት የዕድሜ ልክ እስራት ተፈርዶበታል።

"የዓለማችን እጅግ ተፈላጊ" የሰዎች አዘዋዋሪ ተብሎ የሚጠራው ኪዳነ፤ ባለፈው ታኅሣሥ ላይ ከተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ለኔዘርላንድስ ተላልፎ ተሰጥቷል። በቅርብ ጊዜ ውስጥም በኔዘርላንድስ ፍርድ ቤት የፍርድ ሂደቱ ይጀመራል ተብሎ ይጠበቃል።

ሁለቱ ግለሰቦች በኔዘርላንድስ ጉዳያቸው እየታየ ያለው፤ ዐቃብያነ ሕግ ፈጽመዋቸዋል ከተባሉት ወንጀሎች ውስጥ የተወሰኑት የተከናወኑት አገሪቱ ውስጥ እንደሆነ በመግለጹ ነው። በተለይም በኔዘርላንድስ የሚኖሩ የስደተኞች ዘመዶች በነዚህ አዘዋዋሪዎች ከፍተኛ ገንዘብ እንዲከፍሉ ሲገደዱ እንደነበረም ዐቃብያነ ሕግ ተናግረዋል።

የተወልደ ጠበቆች በበኩላቸው ጉዳዩ "ከኔዘርላንድስ ጋር ግልጽ የሆነ የወንጀል ግንኙነት የለውም" በማለት ተከራክረዋል። ፍርድ ቤቱ ግን መከራካሪያቸውን ውድቅ በማድረግ በሰዎች ዝውውር እና ብዝበዛ ጥፋተኛ ብሏቸዋል።