ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ሩዋንዳ የተሰረዘውን የስደተኞች ስምምት በተመለከተ ዩናይትድ ኪንግደም ላይ ክስ መሰረተች
ዩናይትድ ኪንግደም ውስጥ የሚገኙ ጥገኝነት ጠያቂዎችን ተቀብላ ለማስተናገድ ከአገሪቱ መንግሥት ጋር የገባችው ስምምነት የተሰረዘባት ሩዋንዳ፤ በውሉ መሠረት ሊከፈለኝ ይገባ ነበር ያለችው ገንዘብ እንዲፈጸምላት በፍርድ ቤት አቤቱታ አቀረበች።
የሩዋንዳ መንግሥት ክሱን የመሰረተው ኔዘርላንድስ ውስጥ በሚገኘው ቋሚ የግልግል ፍርድ ቤት ነው። የአገሪቱ መንግሥት፤ ዩናይትድ ኪንግደም የተወሰኑ ጥገኝነት ጠያቂዎችን ወደ ሩዋንዳ ለመላክ በስምምነት የገባችውን ቃል ልትፈጽም አልቻለችም ሲል ተከራክሯል።
ከዚህ ቀደም የነበረው ወግ አጥባቂ መንግሥት በተፈራረመው ስምምነት ላይ ዩናይትድ ኪንግደም፤ ሩዋንዳ ለምትቀበላቸው ጥገኝነት ጠያቂዎች ማስተናገጃ እንዲሆን የአገሪቱን ኢኮኖሚ ለመደገፍ የሚውል ገንዘብ ለመክፈል ተስማምታለች።
ይሁን እንጂ የአሁኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ኪር ስታርመር ወደ ሥልጣን በመጡበት የአውሮፓውያኑ 2024 ስምምነቱን አቋርጠውታል። የዩናይትድ ኪንግደም የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴር "ወደፊት" ለሩዋንዳ "እንዲከፈል ተይዞ የነበረው" 220 ሚሊዮን ፓውንድ "እንደማይከፈል" ገልጿል።
የመሥሪያ ቤቱ ቃል አቀባይ፤ "የቀደመው መንግሥት ሲከተል የነበረው የሩዋንዳ ፖሊሲ ከፍተኛ የሆኑ የግብር ከፋዮች ጊዜ እና ገንዘብ እንዲባክን አድርጓል" ብለዋል። "ብሪታኒያውያን ግብር ከፋዮችን ለመጠበቅ የያዝነውን አቋም በጽኑ እንከላከላለን" ሲሉም አክለዋል።
የሩዋንዳ መንግሥት በጉዳዩ ላይ አስተያየት እንዲሰጥ ከቢቢሲ ለቀረበለት ጥያቄ ምላሽ አልሰጠም። የአገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒቴር ስለ ጉዳዩ መረጃ ለማግኘት የሩዋንዳ ጋዜጣ በሆነው 'ኒው ታይምስ' ላይ የወጣ ጽሑፍን ጠቁሟል።
ጋዜጣው ላይ የወጣው ጽሑፍ፤ የቀረበው አቤቱታ "አንድ በስምምነት የተገባ ቃልን አፈጻጸም የሚመለከት" እንደሆነ ያስረዳል።
የበፊቱ ወግ አጥባቂ መንግሥት ይህንን የሩዋንዳ ፖሊሲ ለማስፈጸም 700 ሚሊዮን ገደማ ፓውንድ ወጪ አድርጓል። ከዚህ ገንዘብ ውስጥ 290 ሚሊዮን ፓውንድ ያህሉ ለሩዋንዳ መከፈል የነበረበት ነው።
የአገራቱ ስምምነት በአስተኛ ጀልባ ወደ ኢንግላንድ ለመግባት የሚሞክሩ ስደተኞችን ለማገድ ያለመ ነበር። ስምምነቱ ተግባራዊ መሆን ከጀመረ በኋላ ወደ ሩዋንዳ የተመለሱት አራት ፈቃደኛ ሰዎች ብቻ ናቸው።
በ2024 የተካሄደውን አጠቃላይ ምርጫ የሌበር ፓርቲ ካሸነፈ ከጥቂት ጊዜያት በኋላ ጠቅላይ ሚኒስትር ኪር ስታርመር፤ ዕቅዱን "የሞተ እና የተቀበረ" ሲሉ ገልጸውታል።
የሩዋንዳ እና ዩናይትድ ኪንግደም ስምምነት ውሉን ማቋረጥ የሚያስችል አንቀጽን የያዘ ነው። አንቀጹ "እያንዳንዱ ወገን ለሌላኛው ወገን በጽሑፍ ማስጠንቂያ በመስጠት ስምምነቱን ሊያቋረጥ ይችላል" ይላል።
የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴር በአውሮፓውያኑ ታኅሣሥ 2024 እንደገለጸው፤ በስምምነቱ መሠረት ተጨማሪ 100 ሚሊዮን ፓውንድ ክፍያ እንዲፈጸም ይጠበቃል። ክፍያው በ2025-26 እና በ2026-27 የበጀት ዓመታት 50 ሚሊዮን ፓውንድ በማስተላለፍ የሚፈጸም ነበር።
በተጨማሪም ሚኒስቴሩ 300 ሰዎች ወደ ሩዋንዳ በሚዘዋወሩበት ወቅት 120 ሚሊዮን ፓውንድ ለመክፈል ተስማምቶ እንደነበር ተገልጿል።