ማረጥ ከመርሳት በሽታ ጋር የሚመሳሰል የአእምሮ ለውጥ እንደሚያመጣ ጥናት ጠቆመ

ማረጥ አልዛይመርስ ከተሰኘው የመርሳት በሽታ ጋር የሚመሳሰል የአአምሮ ለውጥ እንደሚያመጣ በዩናይትድ ኪንግደም የተሠራ ግዙፍ ጥናት ጠቆመ።

ከማስታወስ እና ስሜት ጋር የተያያዙ ግሬይ ማተር የሚባሉ የነርቭ ሥርዓቶች መሳሳት ሴቶች ከወንዶች በላቀ በእርጅና ምክንያት ለሚመጡ መዳከሞች ተጋላጭ እንዲሆኑ እንደሚያደርጋቸው ተመራማሪዎች ይገምታሉ።

125 ሺህ ገደማ የሚሆኑ ሴቶች በጥናቱ የተሳተፉ ሲሆን ከእነዚህ መካከል 11 ሴቶች በኤምአርአይ ጭንቅላታቸው 'ስካን' ተደርጓል።

ሳይኮሎጂካል ሜዲሲን የተባለው ጋዜጣ ላይ የተለጠፈው የጥናቱ ውጤት እንደሚሳየው የሆርሞን መተካት ሕክምናን በማከናወን የግሬይ ማተርን መሳሳት መከላከል አይችልም።

የጥናቱ ከፍተኛ ፀሐፊ የሆኑት የካምብሪጅ ዩኒቨርሲቲዋ ፕሮፌሰር ባርባራ ሳሀኪያን እንደሚሉት "ይህንን ልዩነት ያየንበት የአእምሮ ክፍል ነው በአልዛይመርስ በሽታ ተጠቂ የሚሆነው።"

"ማረጥ ሴቶች ተጋላጭ እንዲሆኑ ሊያደርግ ይችላል። ሙሉ ሙሉ ምስሉን ባያሳየንም ለምን ሴቶች ከወንዶች እጥፍ በእርጅና ምክንያት ለሚመጡ የአእምሮ መዳከሞች ይጋለጣሉ? የሚለውን ያብራራል።"

የአእምሮ ለውጡ ሂፖካምፐስ የተባለው ለማስታወስ እና ለመማር በሚጠቅመው የአእምሮ ክፍል ላይ የሚከሰት ነው። አልፎም ኢንቶርሂናል ኮርቴክስ የተባለውን ለትውስታ እና አካባቢን ለመዳሰስ የሚጠቅመው ክፍልም ለውጥ ሊመጣበት ይችላል።

በተጨማሪ አንቴሪዬር ሲንጉሌት የተባለው ከትኩረት እና ከስሜት ጋር የተገናኘው የአእምሮ ክፍልም ለውጥ ሊያስተናግድ ይችላል።

ዋይት ማተር እና ግሬይ ማተር ለአእምሮ እና የአከርካሪ አጥንት እጅግ አስፈላጊ የሚባሉ የነርቭ ሥርዓት ክፍሎች ናቸው።

የእንግሊዝ ጤና አገልግሎት መመሪያ እንደሚለው የሆርሞን መተካት ሕክምና የማረጥ ምልክት ሆኖ ሊታይ ይችላል።

አጥኚዎቹ እንደሚሉት ማረጥ እና የሆርሞን መተካት ሕክምና አአምሮ፣ የማስታወስ አቅም እና ስሜት ላይ ያላቸው ተፅዕኖ ምንድነው የሚለው ተጨማሪ ምርምር ይሻል።

ጥናቱ የሆርሞን መተካት ሕክምና ላይ ያሉ ሴቶች የአእምሮ ጤናቸው ደካም ሊሆን እንደሚችል አሳይቷል።

ከጥናቱ አሳታሚዎች መካከል አንደ የሆኑት ዶክተር ክሪስቴል ላንግሊ ከማረጥ ጋር ተያይዘው የሚመጡ ሌሎች ተግዳሮቶች እንዳሉ መዘንጋት የለብንም ይላሉ።

"ሁላችንም በማረጥ ላይ ያሉ ሴቶች ለሚያሳዩ ለአካላዊው ለውጥ ብቻ ሳይሆን ለአእምሮ ጤናቸውም ልናስብ ይገባል። በዚህ ሒደት ውስጥ እንዳሉ መናገር እና እርዳታ ጠየቅ የሚያሳፍር ነገር አይደለም።"