አነጋጋሪው ለሴቶች የፊት ውበት በመርፌ እየተሰጠ ያለው የዓሣ የዘር ፍሬ ፈሳሽ

ደቡብ ማንቸስተር በሚገኝ የውበት ክሊኒክ ውስጥ አቢ ወንበር ላይ ተንጋላ ተቀምጣለች። መርፌ ጉንጯ ውስጥ ሲገባ እንደሚያም ተናገረች።

አቢ 29 ዓመቷ ነው። የፊቷ ቆዳ ውስጥ ከሳመን ዓሣ ወይም ታራውት ዓሣ የዘር ፍሬ የተወሰደ ዘረ መል (polynucleotides) ገብቷል።

የሰዎች ዘረ መል ከዓሣ ዘረ መል ጋር ተመሳሳይ ነው።

የዓሣው ዘረ መል የአቢ ቆዳ ውስጥ ከገባ በኋላ ኮላኝ (collagen) እና ኤላስቲን (elastin) የተባሉ ፕሮቲኖችን ለማምረት ይረዳል ተብሎ ይታመናል።

እነዚህ ሁለት የፕሮቲን ዓይነቶች ቆዳ ቅርጹን እንዳይለቅ ይረዳሉ።

አቢ ቆዳዋ አዲስ እና ጤናማ እንዲሆንላት ትፈልጋለች። ቆዳዋ ላይ ያለውን ብጉር እንዲሁም ጠባሳ እንዲያጠፋላትም ትሻለች።

"እነዚህን ችግሮች መቅረፍ ነው የምፈልገው" ትላለች አቢ።

ከዓሣ የዘር ፍሬ የሚወሰደው ዘረ መል ለቆዳ ሕክምና እየዋለ ነው። ይህንን ዘዴ "ተዓምራዊ" ሲሉ የሚገልጹት አሉ።

ታዋቂ ሰዎች ስለ ሕክምናው መናገራቸው የበለጠ ዝነኛ እንዲሆን አስችሏል።

እንግሊዛዊቷ ድምጻዊት ቻሪል ኤክስሲኤክስ በኢንስታግራም ላይ ላሉት 9 ሚሊዮን ተከታዮቿ "ቫይታሚን የመውሰድ ያህል ነው" ስትል የዓሣ ዘረ መልን በቆዳ ውስጥ ማስገባት ያለውን ጠቀሜታ ገልጻለች።

ከዚህ ቀደም የቆዳ የፕላስቲክ ቀዶ ጥገና ሲከናወን ፊለርስ (fillers) በመጠቀም ነበር።

"አሁን የፊለርስ ዘመን አልፏል" ብላለች ድምጻዊቷ።

ኪም ካርዳሺያን እና ክሎዊ ካርዳሺያንም ሕክምናውን ሲያሞግሱ ተደምጠዋል።

ተዋናይቷ ጄኔፈር አኒስተን ከጂሚ ኪሚል ጋር ባደረገችው ቃለ ምልልስ "የሳመን ዓሣ ቆንጆ ቆዳ አልሰጠኝም?" በማለት በጥያቄ መልክ ለውጧን ገልጻለች።

ደርማፎከስ የውበት ሕክምና ውስጥ የምትሠራው ሱዛን ማንስፊልድ እንደምትለው፤ በዕድሜ ምክንያት የሚከሰት የቆዳ ለውጥን መቀልበስ የሚቻልበት ዘመን ላይ ደርሰናል።

የቆዳ እንክብካቤ ተለውጧል። የዓሣ የዘር ፈሳሽ ዘረ መል ቆዳን እንደሚያድስ ጥናቶች እና ሳይንሳዊ ሙከራዎች ይጠቁማሉ።

የቆዳ መጨማተርን እና ጠባሳን ይቀንሳል።

"በሰውነት ውስጥ ያለውን ንጥረ ነገር አጉልቶ ማውጣት ነው ሥራችን። ሕክምናውን ልዩ የሚያደርገውም ይሄ ነው" ትላለች ሱዛን።

ሕክምናው ውድ ነው። አንድ ዙር መርፌ ለመወጋት ከ200 እስከ 500 ፓውንድ ያስከፍላል። ለተከታታይ ሳምንታት መርፌውን መውሰድም ይመከራል።

በየስድት ወይም ዘጠኝ ወር የቆዳ እድሳት ማድረግም ያስፈልጋል።

የአቢ ሐኪም ሔለና ደንክ ናት። ባለፉት 18 ወራት ሕክምናው ታዋቂ እየሆነ መምጣቱን ትናገራለች።

"ግማሽ የሚሆኑት ደንበኞቼ ከፍተኛ ለውጥ እንዳዩ ይናገራሉ። ቆዳቸው ለስላሳ እና ጤናማ ይሆናል። ወጣት ነው የሚመስሉት። የተቀሩት ደንበኞቼ ሰፊ ልዩነት ባያዩም ቆዳቸው አዲስ እንደሆነ ይሰማቸዋል።"

አቢ በሕክናው ደስተኛ ናት። "መርፌውን መወጋት ያማል" ብትልም ባየችው ውጤት ተደስታለች።

በሕክምናው ምክንያት ዐይኗ ሥር በልዞ የነበረው አካባቢ ነጥቷል።

ሕክምናው ጤናማ እንደሆነ ቢገለጽም፤ እጅግ በተጋነነ ሁኔታ መታየት እንደሌለበት እና ሳይንሱ የጠራ ውጤት እስከሚያመጣ መታገስ እንደሚያሻ ባለሙያዎች ያስጠነቅቃሉ።

በአውስትራሊያ የቆዳ ሐኪም የሆኑት ዶ/ር ጆን ፓግሊሮ እንደሚሉት፤ የሰው ልጆች ዘረ መል መሠረት የሆነው ኒውክታይድስ (nucleotides) በዓሣ ዘረ መል ምክንያት ሊሰባበር ይችላል።

"አስተማማኝ መረጃ የለንም። እንደ ሕክምና ባለሙያ ውጤታማነቱ እስከሚታወቅ ዓመታት እንደሚወስድ መግለጽ እፈልጋለሁ። ታማኝ ጥናቶች ሕክምናው አስተማማኝ እና ደኅንነቱ የተጠበቀ መሆኑን ማረጋገጥ አለባቸው። ይሄ ደግሞ ገና አልሆነም።"

ኒው ዮርክ የምትኖረው ሻርለት ቢርክሊ 31 ዓመቷ ነው። ሕክምናውን ያደረገችው ለሰርጓ ብላ ነበር።

ከአንድ ዓመት በፊት ሕክምናውን አድርጋ ወዲያው ኢንፌክሽን ያዛት። ቆዳዋ ጠቁሮ፣ ዐይኗ ሥርም በለዘ።

"የገጠመኝ ነገር ከፈለግኩት በተቃራኒው ነበር። የጎንዮሽ ጉዳቶች አሉት። የቆዳ መቅላት፣ ማበጥ እና መበለዝ ይጠቀሳሉ። እነዚህ ጉዳቶች ጊዜያዊ ናቸው" ትላለች።

አንዳንዶች አለርጂ ይገጥማቸዋል። የዓሣው ዘረ መል በተገቢው መንገድ ቆዳቸው ውስጥ ላይገባም ይችላል።

ዘለግ ላለ ጊዜ የሚዘልቅ የቆዳ መበለዝ አልያም ኢንፌክሽን ሊያጋጥም ይችላል።

እንደ ዩናይትድ ኪንግደም ባሉ አገራት ሕክምናውን የሚሰጡ የውበት ክሊኒኮች ቢኖሩም እንደሌሎች ሕክምና ሰጪዎች ቁጥጥር አይደረግባቸውም።

የአሜሪካ የምግብ እና መድኃኒት ቁጥጥርም ፈቃድ አልሰጠውም።

"ለምን ራሴን እንደዚያ አሰቃየሁ? ብዬ አስባለሁ" ትላለች ሻርለት።

ከደረሰባት ጉዳት ለማገገም በሺዎች የሚቆጠር ገንዘብ አውጥታለች።

ሕክምናው 10 ወራት ቢያልፈውም አሁንም ድረስ ቆዳዋ ላይ ያለው ጠባሳ አልጠፋም። ከዚህ በኋላ መቼም ቢሆን ሕክምናውን እንደማትደግመው ትናገራለች።

የኮስሞቲክ ቀዶ ሕክምና ቁጥጥር እንዲደረግበት ንቅናቄ የሚያደርገው 'ሴቭ ፌስ' ኃላፊ አሽተን ኮሊንስ እንደምትለው፤ ሕክምናው ደኅንነቱ የተጠበቀ ቢሆንም እንኳን በሕክምና ባለሙያዎች እና ዕውቅና ባላቸው ሕክምና መስጫዎች መከናወን ያለበት ነው።

"በአግባቡ ሙከራ ያልተደረገባቸው ምርቶች ናቸው ገበያ ላይ ያሉት። ይህ ደግሞ በእጅጉ አሳሳቢ ነው" ትላለች።

የብሪቲሽ ኮሊጅ ኦፍ ኤስተቲክ ሜድስን ፕሬዝዳንት ዶ/ር ሶፊ ሾተር "ቁጥጥር ስለሌለ ማንም ሰው የትኛውንም ምርት ሊጠቀም ይችላል። ይሄ አስጊ ነው" ይላሉ።

ተፈጥሯዊ ገጽታ እንዲኖራቸው ለሚፈልጉ ታካሚዎቻቸው ሕክምናውን ቢሰጡም፤ ሌሎች አማራጮች እንዳሉ ሳይጠቅሱ ግን አያልፉም።

ለተለያዩ ሰዎች የሚያስፈልገው ሕክምና የተለያየ እንደሆነ ያሰምሩበታል።