ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የተባበሩት መንግሥታት የደቡብ ሱዳን ሠራዊት አዛዥ "ማንንም እንዳትምሩ" በሚል ያስተላለፉትን ትዕዛዝ አወገዘ
የተባበሩት መንግሥታት አንድ የደቡብ ሱዳን ከፍተኛ ወታደራዊ አዛዥ "ህጻናት፣ አረጋውያን እና ንጹሃንን" ጨምሮ "ማንንም እንዳትምሩ" በሚል ያስተላለፉት ትዕዛዝ እጅጉን እንዳሳሰበው ገለጸ።
የደቡብ ሱዳን ሠራዊት ምክትል ዋና አዛዥ የሆኑት ጄነራል ጆንሰን ኦሉኒ፤ ይህንን ያሉት ወታደሮችን በታጣቂዎች ወደ ተያዙ አካባቢዎች እያሰማሩ በነበረበት ወቅት ነው።
በደቡብ ሱዳን የተባበሩት መንግሥታት ተልዕኮ ዋና ኃላፊ፤ "እጅግ ተጋላጭ የሆኑትን [የማህበረሰብ ክፍሎችን] ጨምሮ በሲቪሎች ላይ ጥቃት እንዲፈጸም የሚቀሰቅስ ንግግር እጅግ አጸያፊ እና አሁኑኑ መቆም ያለበት ነው" ብለዋል።
በወታደራዊ አዛዡ ትዕዛዙ የተሰጣቸው 'አግዌሌክ' የተባሉት የሚሊሻ ኃይሎች ወደ ጆንግሌይ ግዛት እየተላኩ ነበር። ከሥልጣን የታገዱት የደቡብ ሱዳን ምክትል ፕሬዝዳንት ሪክ ማቻር አጋር የሆኑ ኃይሎች ባለፉት ሳምንታት በርካታ አካባቢዎችን ተቆጣጥረዋል።
ማቻር በአሁኑ ወቅት በነፍስ ግድያ፣ በአገር ክህደት እና በሰብአዊነት ላይ በሚፈጸሙ ወንጀሎች የተመሰረተባቸው ክስ በመታየት ላይ ይገኛል። የቀድሞው ምክትል ፕሬዝዳንት ግን የቀረቡባቸውን ውንጀላዎች ውድቅ አድርገዋል።
የአገሪቱ ሠራዊት፤ በጆንግሌይ ግዛት በሚገኙ ሦስት አውራጃዎች ውስጥ በሚገኙ ታጣቂ ኃይሎች ላይ የሚያካሂደውን ጥቃት ከመክፈቱ አስቀድሞ ሁሉም ሲቪሎች፣ የተባበሩት መንግሥታት ሠራተኞች እና ሌሎች የረድኤት ድርጅቶች አካባቢውን ለቀው እንዲወጡ አዟል።
ባለፈው ሳምንት የአገሪቱ የጦር አዛዥ ወታደሮቻቸው በሰባት ቀናት ውስጥ "አመፁን እንዲደመስሱ" ትዕዛዝ ሰጥተው ነበር።
ፌስቡክ ላይ በተለጠፈ አንድ ቪዲዮ ላይ ወታደራዊ አዛዡ ኦሉኒ፤ "ማንንም እንዳትምሩ፤ አረጋውያን፣ ሕጻናት፣ ወፎች ወይም አንድም ቤት ቆሞ እንዳይገኝ" ሲሉ ይደመጣሉ።
በደቡብ ሱዳን የተባበሩት መንግሥታት የሰብአዊ መብት ኮሚሽን፤ በጆንግሌይ ግዛት እየተካሄደ ባለው ውጊያ "እጅግ መደናገጡን" ገልጿል። በአካባቢው የሚገኙ ሲቪሎች ወደ ረግረጋማ ቦታዎች እየሸሹ መሆኑን ከአይን እማኞች መረዳቱን ጠቅሷል።
እንደ የተባበሩት መንግሥታት ገለጻ፤ እየተባባሰ ባለው ግጭት የተነሳ ከ180,000 በላይ ሰዎች ከመኖሪያቸው ተፈናቅለዋል።
ኮሚሽኑ እሁድ ዕለት ከጄኔቫ ባወጣው መግለጫ፤ "ጁባ ውስጥ የሚገኝ አንድም ከፍተኛ ፖለቲካዊ ወይም ወታደራዊ አመራር በጆንግሌይ ከፍተኛ የሆነ ወንጀል እንዲፈጸም የተደረገውን ግልጽ ቅስቀሳ ላያውቅ አይችልም" ብሏል።
የኮሚሽኑ ኃላፊ ያስሚን ሶካ፤ "ከውጊያ ውጭ የሆኑ ሰዎች እና አዛውንቶችን ጨምሮ ሲቪሎች እንዲገደሉ የሚቀሰቅስ ቋንቋ፤ 'ማንንም እንዳትምሩ' ከሚል ንግግር ጋር ሲደመር አስደንጋጭ ብቻ ሳይሆን እጅግ አደገኛ ነው" ብለዋል።
የአገሪቱ ሠራዊት በበኩሉ ጆንግሌይ ግዛት ውስጥ ባሉት ኒይሮል፣ ኡሮር እና አኮቦ አውራጃዎች የሚኖሩ "ንጹሃን በሙሉ ለደህንነታቸው ሲባል በመንግሥት ቁጥጥር ስር ወደሚገኙት አካባቢዎች በአስቸኳይ እንዲሄዱ ትዕዛዝ መሰጠቱን" ተናግሯል።
ሁሉም የተባበሩት መንግሥታት ተልዕኮ እንዲሁም ሌሎች መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ሠራተኞችም በ48 ሰዓታት ውስጥ አካባቢውን ለቀው እንዲወጡ ትዕዛዝ ተሰጥቷቸዋል።
የተልዕኮው ቃል አቀባይ ለዜና ወኪሉ ሮይተርስ በሰጡት አስተያየት "ውጥረቱን ለማርገብ እና ግጭቶችን ለመከላከል በተሰጠን ስልጣን መሰረት አኮቦ ውስጥ የሚገኙ ሰላም አስከባሪዎቻችን በቦታቸው ይገኛሉ" ብለዋል።
በደቡብ ሱዳን ዋነኛ ተቃዋሚ ቡድን የሆነው የሪክ ማቻር 'ሱዳን ፒፕልስ ሊብሬሽን ሙቭመንት ኢን ኢፖዚሽን' በበኩሉ ኃይሎቹ በቀጣዩ የካቲት ወደ ዋና ከተማዋ ጁባ ይደርሳሉ ብሎ እንደሚጠብቅ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
የአገሪቱ ጦር ግን ተቃዋሚዎቹ ዋና ከተማዋን ለማጥቃት የሚያስችል አቅም እንደሌላቸው በመግለጽ ዛቻውን አጣጥሏል።