ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ከሪክ ማቻር መከሰስ በኋላ ደቡብ ሱዳን ወደ እርስ በርስ ጦርነት ትመለስ ይሆን?
የደቡብብ ሱዳን ተቃዋሚዎች የፕሬዝዳንት ሳልቫ ኪር መንግሥት በአውሮፓውያኑ 2018 ከተቀዳሚ ምክትል ፕሬዝዳንት ሪክ ማቻር ጋር የተፈራረመውን የሰላም ስምምነት በጣሰ መልኩ በቁም እስር ውስጥ እንዲቆዩ በማድረጉ እና ክስ በመመሥረቱ ተቃውሟቸውን እያሰሙ ነው።
ከሥልጣን የታገዱት እና በቁም እስር ውስጥ የቆዩት ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዚዳንት ሪክ ማቻር ከሰኞ ዕለት ጀምሮ ከሌሎች ተከሳሾች ጋር በመሆን ችሎት ፊት ቀርበዋል።
ማቻር በቁም እስር ውስጥ እንዲሆኑ ከተደረገ ወዲህ ለመጀመርያ ጊዜ ለሕዝብ የታዩት ሰኞ ዕለት ችሎት ሲቀርቡ ነበር።
የተቀዳሚ ምክትል ፕሬዚዳንቱ እና አብረዋቸው የተከሰሱ ግለሰቦች የፍርድ ቤት ውሎ በአገሪቱ ብሔራዊ ቴሌቪዥን በቀጥታ ተላልፏል።
የማቻር ፖለቲካ ፓርቲ ተቃዋሚው የሱዳን ሕዝቦች ነጻነት እንቅስቃሴ/ተቃዋሚ በእርሳቸው እና ሌሎች 20 ሰዎች ላይ የቀረበውን የነፍስ ማጥፋት፣ የአገር ክህደት እና በሰብዓዊነት ላይ የተፈጸመ ወንጀል ክስ ውድቅ አድርጓል።
ክሱ የተመሰረተው ባለፈው ዓመት በአገሪቱ ሰሜን ምሥራቅ አካባቢ ኑዌሮች በሚበዙበት የዋይት አርሚ ታጣቂ ቡድን ላይ ከተፈጸመ ጥቃት ጋር በተያያዘ ነው።
የፕሬዝዳንት ሳልቫ ኪር ውሳኔ አገሪቱን ወደ አዲስ የእርስ በርስ ጦርነት እንድትገባ በር ከፋች ነው የሚሉት ተቃዋሚዎች "የሥርዓት ለውጥ ማድረግ የሚያስችል" እንቅስቃሴ ውስጥ መሆናቸውን ይናገራሉ።
ተቃዋሚው የሱዳን ሕዝቦች ነጻነት እንቅስቃሴ/ተቃዋሚ (Sudan People's Liberation Movement In Opposition) ፓርቲ መስከረም 5/2018 ዓ.ም. የኪር መንግሥትን "ሕጋዊነት የሌለው" ሲል ፈርጇል።
ይህ የመጣው የደቡብ ሱዳን ፍትሕ ሚኒስቴርመስከረም 1/2018 ዓ.ም. በቁም እስር ላይ የሚገኙት የደቡብ ሱዳን ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዝዳንት ሪክ ማቻርን በነፍስ ማጥፋት፣ በአገር ክህደት እንዲሁም በሰብዓዊነት ላይ በተፈጸሙ ወንጀሎች መከሰሳቸውን ይፋ ካደረገ በኋላ ነው።
ኪር ከክሱ በኋላ ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዝዳንት የነበሩት ማቻርን ከሥልጣናቸው መነሳታቸውን ወዲያው አስታውቀዋል።
የደቡብ ሱዳን መንግሥት ማቻር እና ሰባት አጋሮቻቸውን ተመሳሳይ ክስ እንደሚቀርብባቸው በመግለጽ ባለፈው ዓመት መጋቢት ወር ላይ በጦሩ እና በኔዌር ታጣቂዎች መካከል ግጭት እንዲቀሰቀስ "በማቀነባበር" ወንጅሏቸዋል።
የሱዳን ሕዝቦች ነጻነት እንቅስቃሴ/ተቃዋሚ ክሶቹ "ፖለቲካዊ እና የሌለውን የሚፈልጉ" ናቸው በማለት ውድቅ ያደረገ ሲሆን፣ በተጨማሪ የሥልጣን ክፍፍል ስምምነቱን የጣሰ ብሎታል።
ተንታኞች የማቻር ክስ ዕጣ ፈንታቸውን የሚወስን ብቻ ሳይሆን ከአውሮፓውያኑ 2013 እስከ 2018 ድረስ የዘለቀውን የእርስ በእርስ ጦርነት ያስቆመውን የሰላም ስምምነትም የሚበይን ይሆናል ብለዋል።
እንዴት እዚህ ደረስን?
ባለፈው ዓመት መጋቢት ወር ላይ የተፈጠረውን ግጭት ተከትሎ ኪር ተቃዋሚዎች ሥልጣንን ለብቻቸው ለመጠቅለል ይፈልጋሉ ሲሉ የኮነኑትን የተናጠል ውሳኔ ካሳለፉ በኋላ የሱዳን ሕዝቦች ነጻነት እንቅስቃሴ/ተቃዋሚ ሰዎች እንዲደራጁ ጥሪ እያቀረበ ነው።
ከዚህ ግጭት በኋላ የአገሪቱ የፀጥታ ባለሥልጣናት በርካታ የማቻር ደጋፊዎችን በቁጥጥር ስር አውለዋል።
ከእነዚህም መካከል የነዳጅ ሚኒስትሩ ፑት ካንግ ቾል፣ እና የጦሩ ምክትል ሚኒስትሩ ሌተናል ጄነራል ጋብሬል ዱኦፕ ላ የሚገኙበት ሲሆን፣ ቾል ከማቻር ጋር ክስ ሲመሠረትባቸው ከመስከረም 1/2018 ዓ.ም. ጀምሮ ከሥልጣናቸው ታግደዋል።
ተቃዋሚው የሱዳን ሕዝቦች ነጻነት እንቅስቃሴ/ተቃዋሚ የታሠሩት ሰዎች እንዲለቀቁ ካልሆነ ግን ወታደራዊ እርምጃ እንደሚወስድ አስጠንቅቋል።
ቡድኑ የባለሥልጣናቱን መታሰር ተከትሎ የሰላም ስምምነቱ መፍረሱን እና ኪር አባላቱን ከመንግሥት ኃላፊነት እያገለሏቸው ነው ሲል ወንጅሏል።
የሱዳን ጦር እና ለሱዳን ሕዝቦች ነጻ አውጭ እንቅስቀሴ/ተቃውሚ ታማኝ የሆኑ ኃይሎች ባለሥልጣናቱ በቁጥጥር ስር ከዋሉ ጀምሮ በተለያዩ አካባቢዎች ተጋጭተዋል።
የሱዳን ሕዝቦች ነጻ አውጪ/ተቃዋሚ እንቅስቀሴ ምን ምላሽ ሰጠ?
የሱዳን ሕዝቦች ነጻነት እንቅስቃሴ/ተቃዋሚ ክሶቹ የፈጠራ ናቸው በማለት ውድቅ አድርጓል።
አክሎም የኪር ፓርቲ ተቋማትን በመጠቀም የፖለቲካ ተቃዋሚዎችን እያስወገደ እና የአንድ ፓርቲ አገዛዝን እያጠናከረ ነው ሲል ይወነጅላል።
የፓርቲው ምክትል ሊቀመንበር ሬዝ ሙኦች "እነዚህ ክሶች የሰላም ስምምነቱን ለመጣስ ታቅዶ. . . የተፈጠሩ ናቸው" ብለዋል።
የፓርቲው ቃል አቀባይ ፓል ማይ ዴንግ ደግሞ የሰላም ስምምነቱን አንቀጽ 5.3 በመጥቀስ የማቻርን መታገድ ሕጋዊነት የሌለው ብለዋል።
ናሽናል ሳልቬሽን ፍሮንት የተሰኘው የአማፂያን ቡደን በቅርቡ ከሱዳን ሕዝቦች ነጻነት እንቅስቃሴ/ተቃዋሚ ጋር ጥምረት የፈጠረ ሲሆን፣ ክሱን "የብሔር ጥቃትን ፍትሐዊ አድርጎ ያቀረበ" ብሎታል።
መስከረም 6/2018 ዓ.ም. የፖለቲካ ተንታኙ ከዚህ በፊት የፕሬዝዳንቱ ቃል አቀባይ የነበሩት ጄምስ ጋትዴት ዳክ ላምፑር ፕሬዝዳንት ኪር ማቻርን "በግዳጅ ጡረታ እንዲወጡ ሊያደርጓቸው" እና "ከሥልጣን ከመውረዳቸው በፊት. . . . የሥልጣን ውርሳቸው፣ ሀብታቸውን ለመከላከል" በቤተሰብ አባላቶቻቸው ሊተኳቸው ይፈልጋሉ ብለዋል።
መከፈፋፈሉ የኪርን መንግሥት ይፈትናል?
የሱዳን ሕዝቦች ነጻነት እንቅስቃሴ/ተቃዋሚ ለወራት በውስጡ በዘለቀው ፍጭት እና መክዳት በመዳከሙ መንግሥትን ለመገዳደር አቅም ያጥረዋል።
ባለፈው ዓመት ሚያዝያ ወር ላይ የአገሪቱ የሰላም ግንባታ ሚኒስትር የሆኑት እና የፓርቲው አባል ፓር ኩኦል የቡድኑ ጊዜያዊ ሊቀመንበር መሆናቸውን አውጀው ነበር።
ኩኦል የሚመሩት አንጃ ከኪር መንግሥት ጋር እየሠራ ሲሆን፣ ከገዢው የሱዳን ሕዝቦች ነጻ አውጪ እንቅስቃሴ ፓርቲ እንዲሁም ከደቡብ ሱዳን የተቃዋሚዎች ጥምረት የማቻር ተተኪ ይሆናሉ በሚል ድጋፍ እንዳላቸው ይነገራል።
የማቻር በቁም እስር ላይ መሆንን ተከትሎ በመቶዎች የሚቆጠሩ የተቃዋሚ ወታደሮች እና ፖለቲከኞች ፓርቲያቸውን በመክዳት መንግሥትን ተቀላቅለዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ኪር፣ ለማቻር ታማኝ የሆኑ ባለሥልጣናትን ከሥልጣን በማውረድ በሌሎች የተቃዋሚ ባለሥልጣናት ተክተዋቸዋል።
የተወሰኑ የሱዳን ሕዝቦች ነጻነት እንቅስቃሴ/ተቃዋሚ አባላት አገሪቱን ለቅቀው የወጡ ሲሆን፣ ቀሪዎቹ ደግሞ ታማኝነታቸውን ለፕሬዝዳንት ኪር በመግለጽ ፊታቸውን በማቻር ላይ አዙረዋል።
ተንታኞች በተቃዋሚ ፓርቲዎቹ መካከል እየተካረረ የመጣው ፍጥጫ ለዓለም አቀፍ አጋር አካላት የሰላም ስምምነቱ ዳግም ተመልሶ ሥራ ላይ ሊውል የማይችል መሆኑን ያሳየ ነው ይላሉ።
ዓለም አቀፍ አካላት ምን አሉ?
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እና አምንስቲ ኢንተርናሽናል በማቻር ላይ ክስ መመሥረቱን ተከትሎ ፍትሐዊ የሆነ ፍርድ እንዲሰጥ ጠይቀዋል።
የመንግሥታቱ ድርጅት ቃል አቀባይ ስቴፋን ዱጃሪክ መስከረም 2/2018 ዓ.ም. "የትኛውም የሕግ ሂደት ፍትሐዊነት እና ግልጽነት የሚሉትን ዓለም አቀፍ መስፈርቶችን፣ የሕግ የበላይነትን እና ሰብዓዊ መብቶችን ባከበረ መልኩ የሚያሟላ መሆን አለበት" ብለዋል።
የአፍሪካ ኅብረት፣ ኢጋድ ወይም የአሜሪካ መንግሥት በሁለቱ የፖለቲካ መሪዎች መካከል ውጥረት እንዲረግብ እና ማቻር እንዲለቀቁ ጥረት ሲያደርጉ ቢቆዩም እስካሁን ድረስ ምንም ዓይነት መግለጫ አላወጡም።
ባለፈው ዓመት መጋቢት ወር ላይ በደቡብ ሱዳን የመንግሥታቱ ድርጅት ተልዕኮ አገሪቱ ወደ እርስ በእርስ ጦርነት ልትገባ ጫፍ መድረሷን በመግለጽ አስጠንቅቆ ሁለቱም ወገኖች ከግጭት አባባሽ ድርጊቶች እንዲታቀቡ ጥሪ አቅርቧል።
አሜሪካ በበኩሏ ኪር ማቻርን እንዲለቀቁ ስትጠይቅ የአፍሪካ ኅብረት በበኩሉ ሁለቱም አካላት የሰላም ስምምነቱን እንዲያከብሩ እና ተግባራዊ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርቧል።
ኢጋድ በበኩሉ ማቻር በመታሰራቸው ስጋት እንደገባው ገልጾ በሁለቱ መሪዎች መካከል ንግግር እንዲደረግ ለማመቻቸት ፈቃደኛ መሆኑን ሲገልጽ፣ ኬንያ ውጥረቶች እንዲረግቡ በመጠየቅ መልዕክተኛ ልካለች።
የአፍሪካ ኅብረት የተፈጠረውን ግጭት ለማሸማገል ከፍተኛ የልዑካን ቡድን ወደ ጁባ በሚያዚያ ወር መጀመሪያ ላይ የላከ ቢሆንም ቡድኑ ማቻርን ማግኘት እንዳይችሉ መደረጋቸው ተገልጿል።
ቀጥሎ ምን ሊፈጠር ይችላል?
በማቻር ላይ የተመሠረተው ክስ በደቡብ ሱዳን ጭል ጭል የምትለውን ሰላም ያመጣው ስምምነት ሙሉ በሙሉ መፍረሱን ያሳያል።
በሱዳን ሕዝቦች ነጻነት እንቅስቃሴ/ተቃዋሚ እና በናሽናል ሳልቬሽን ፍሮንት መካከል የተመሠረተው ጥምረት የእርስ በርስ ጦርነት የማገርሸት ዕድሉ ሰፊ መሆኑን ያሳያል።
በተመሳሳይ በእርስ በርስ ጦርነቱ ወቅት ከማቻር ጎን በመሆን የተዋጋው ዋይት አርሚ በአገሪቱ ጦር ቁጥጥር ስር የሚገኙ ትልልቅ ከተሞች ላይ ጥቃት ለመሰንዘር እየተዘጋጀ ነው።
በፕሬዝዳንት ኪር የዲንቃ እና በማቻር የኑዌር ማኅበረሰብ መካከል ዳግም ውጥረት እንዲነግስ እና የእርስ በእርስ ጦርነት ሊቀሰቀስ ይችላል የሚል ፍርሃት ተፈጥሯል።
የዓለም አቀፉ እና የቀጠናው ማኅበረሰቦች ጣልቃ ለመግባት እና ውጥረቱን ለማርገብ አለመቻላቸው ደቡብ ሱዳንን ወደ ጦርነት እንድትገባ እና ባለፉት ሰባት ዓመታት የተሠሩት ሥራዎች ሁሉ እንዲበላሹ ያደርጋል ሲሉ ተንታኞች ስጋታቸውን ገልፀዋል።