ትራምፕ ያቋቋሙት የሰላም ቦርድ የተባበሩት መንግሥታትን አላስፈላጊ ያደርገዋል?

"በጋራ ሁላችንም ለአስርታት የዘለቀውን መከራ ለማስቆም፤ ጥላቻ እና ደም መፋሰስን ለመግታት እንዲሁም ለመላው ዓለም ውብ እና ዘላቂ ሰላም ለማምጣት ቆመናል።"

ይህ የአሜሪካው ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ በዳቮስ የምጣኔ ሀብት ፎረም ላይ የሰላም ቦርድ ሲሉ የሰየሙትን ድርጅት ሲያቋቁሙ ያሰሙት ንግግር ነው።

ሰላም የራቃት እና መከራ የበዛባት ዓለም ትራምፕን ማመን የምትፈልግ ትመስላለች።

ነገር ግን ለታዛቢዎች እና ለፖለቲካ መሪዎች ይህ ትራምፕ ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ የተፈጠረውን ዓለም አቀፍ ሥርዓት ለማወክ እና በእሳቸው ተፅዕኖ ሥር ያለ አሠራር ለመዘርጋት ያላቸውን ፍላጎት የሚያሳይ ነው።

"ማንም እንዲጫወትብን አንፈልግም" ሲሉ የፖላንዱ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶናልድ ተስክ በማኅበራዊ ሚድያቸው ጽፈዋል።

በአውሮፓ የትራምፕ ትልቁ ደጋፊ የሆኑት የሃንጋሪው መሪ ቪክተር ኦርባን በበኩላቸው "ትራምፕ ካሉ ሰላም አለ" ብለዋል።

ለመሆኑ በትራምፕ የሚመራው ቦርድ ምንድነው? የተባበሩት መንግሥታትንስ ሊገዳደረው ይችላል?

የቦርዱ ሊቀ-መንበር ሥልጣን

ሐሳቡ የተፀነሰው ባለፈው የአውሮፓውያኑ ዓመት በጋዛ ያለውን ጦርነት ለማስቆም በሚደረገው ጥረት ነው። በወቅቱ የጋዛ ጦርነት ለማስቆም የቀረበውን ሐሳብ የተባበሩት መንግሥታት የፀጥታው ምክር ቤት ደግፎት ነበር።

አሁን ይህ ሐሳብ ወደ ታላቅ፣ ግዙፍ እና ዓለም አቀፍ ዕቅድ አድጓል። የሚያጠነጥነው ደግሞ በትራምፕ ዙሪያ ነው።

ሾልኮ የወጣው የቦርድ መመሪያ ረቂቅ እንደሚያሳየው ትራምፕ ከሥልጣን ቢወርዱም የቦርዱ የሕይወት ዘመን ሊቀ-መንበር ሆነው ይቆያሉ።

በመመሪያው መሠረት ያላቸው ሥልጣን ሰፊ ነው። አባል እንዲሆኑ የፈለጓቸውን ሀገራት መጋበዝ ወይም አለመጋበዝ ይችላሉ። በቦርዱ የሚመሩ ሌሎች ድርጅቶችን መፍጠር ይችላሉ። አልፎም ከኃላፊነት መውረድ ከፈገሉ አሊያም መምራት ካልቻሉ ተተኪያቸውን የሚመርጡት እሳቸው ራሳቸው ናቸው።

ሀገራት የቦርዱ አባል ለመሆን ለመጥራት የሚከብድ 1 ቢሊዮን ዶላር መክፈል አለባቸው።

በዚህ የአውሮፓውያን ዓመት በርካታ ጉዳዮች ተከስተዋል። ባለፉት ጥቂት ሳምንታት ብቻ አሜሪካ የቬንዙዌላውን ፕሬዝደንት በቁጥጥር ሥር አውላለች። ትራምፕ በኢራን ላይ ወታደራዊ እርምጃ ለመውሰድ ዝተዋል። በሌላ በኩል ግሪንላንድን ለመቆጣጠር ማሰባቸው በአውሮፓ ትልቅ ድንጋጤን ፈጥሯል።

የቦርዱን መመሥረት ለመታደም 19 ሀገራት ወደ ዳቮስ አቅንተው ነበር። ከአዘርባጃን እስከ አርጀንቲና፤ ከቀድሞው ሶቪየት ኅብረት እስከ ገልፍ ባሕረ-ሰላጤ ሀገራት ተገኝተዋል። ብዙዎች ቦርዱን ለመቀላቀል "ተስማምተዋል።"

"እዚህ ያሉትን እያንዳንዱን እወዳቸዋለሁ" ሲሉ ትራምፕ መሪዎቹን በዐይናቸው እየቃኙ ተናግረዋል።

የቦርዱ አባል ሊሆኑ ይችላሉ ተብለው የተጠበቁ ሀገራት ሁኔታውን እየቃኙ ዳተኝነት ያሳዩ ይመስላሉ።

"ይህ በጣም በርካታ ጉዳዮችን የሚዳስስ ጉዳይ ነው። ከዚህ ባለፈው ፕሬዝደንት ፑቲን ስለ ሰላም የሚመክር ድርጅት አባል ሊሆኑ መቻላቸው ያሳስበናል" ሲሉ የዩናይትድ ኪንግደም (ዩኬ) የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ይቬት ኩፐር ተናግረዋል።

ትራምፕ ሩሲያ ቦርዱን ለመቀላቀል ዝግጁ ናት ቢሉም ሞስኮ ግን "ከአጋር ሀገራት ጋር እየመከረች" መሆኑን አስታውቃለች።

ስዊድን ቦርዱን 'አሁን" እንደማትቀላቀል ስትገልጽ ኖርዌይ ደግሞ "ያልተመለሱ ጥያቄዎች ስላሉ ከዋሺንግተን ጋር እንወያያለን" የሚል ዲፕሎማሲያዊ ምላሽ ሰጥታለች።

ቱርክ እና ኢንዶኔዢያን ጨምሮ ሰባት ሙስሊም ሀገራት ቦርዱን የተቀላቀሉት "በጋዛ ፍትሐዊ እና ዘላቂ ሰላም እንዲመጣ" መሆኑን ግልጽ አድርገዋል።

ነገር ግን ሾልከው የወጡ የቦርዱ መመሪያዎች ጋዛን አይጠቅሱም።

ትራምፕ የኖቤል የሰላም ሽልማት እንደሚገባቸው በተደጋጋሚ ይናገራሉ። በትራምፕ የተተኩት የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዝደንት ባራክ ኦባም በአውሮፓውያኑ 2009 የኖቤል የሰላም ሽልማት አሸናፊ መሆናቸው የሚታወስ ነው።

አንዳንድ የዓለም መሪዎች የትራምፕን ቦርድ አለመቀላቀላቸው ዋጋ ሊያስከፍላቸው እንደሚችል ያውቁታል።

"የወይን እና ሻምፓኝ ምርቱ ላይ 200% ታሪፍ ስጥልበት ይቀላቀላል። አለመቀላቀልም መብቱ ነው" ሲሉ ትራምፕ ስለፈረንሳዩ ፕሬዝደንት ኢማኑኤል ማክሮን ተናግረዋል።

ብዙዎች በዝምታ ያለፉትን ነገር ድምጿን ከፍ አድርጋ የተናገረችው ስሎቬኒያ ብቻ ናት። ጠቅላይ ሚኒስትር ሮበርት ጎሎብ ስጋታቸውን ግልጽ አድርገዋል። "ከሰፊው ዓለም አቀፍ ሥርዓት ጋር የሚጣረስ ነው" ብለዋል።

ትራምፕም ይህን ስጋት በተመለከተ ምላሻቸውን ሰጥተዋል።

"ይህ ቦርድ ሙሉ በሙሉ ሲቋቋም የምንፈልገውን ነገር ማድረግ እንችላለን። ይህን የምናደርገው ከተባበሩት መንግሥታት ጋር በመጣመር ነው" ሲሉ ለታዳሚዎች ተናግረዋል።

ነገር ግን ይህ ምን ማለት እንደሆነ ግልጽ አይደለም።

ይህን ከማለታቸው በፊት በፎክስ ቴሌቪዥን ቀርበው ቦርዱ የተባበሩት መንግሥታትን ሊተካ ይችላል ወይ? ተብለው የተጠየቁት ትራምፕ "ሊተካ ይችላል። የተባበሩት መንግሥታት ይህን ያህል አስፈላጊ ሆኖ አልተገኘም" ብለዋል።

"የተባበሩት መንግሥታት ያለውን አቅም አደንቃለሁ። ነገር ግን አቅሙን አሟጦ አልተጠቀመም። እኔ ያስቆምኳቸውን ጦርነቶች ድርጅቱ ማስቆም ነበረበት።"

አዲሱ የሰላም ሊቀመንበር?

በአሁኑ የትራምፕ እንቅስቃሴ 193 አባል ሀገራት ያሉት የመንግሥታቱ ድርጅት የሰላም አማካሪነት ሚናውን ያጣ ይመስላል።

ዋና ፀሐፊው አንቶኒዮ ጉቴሬዝ በአውሮፓውያኑ ጥቅምት 2016 በፀጥታው ምክር ቤት ከተሾሙ በኋላ "ሰላም ለማምጣት የሚደረግ ዲፕሎማሲ" ለማጠናከር ቃል ገብተው ነበር።

ላለፈው አስር ዓመት ድርጅቱ የሚያደርገው ጥረት በፀጥታው ምክር ቤት ሲገታ ታይቷል። ድምፅን በድምፅ የመሻር መብት ያላቸው ዩናይትድ ስቴትስን ጨምሮ ሌሎች ኃያላን ሀገራት እና ጦርነት የሚያቀነባብሩ ተዋናዮች ለመንግሥታቱ ድርጅት ፈተና ሆነዋል።

"ይህ የተባበሩት መንግሥታት እና የፀጥታው ምክር ቤት ውድቀት ማሳያ ነው" የሚሉት የድርጅቱ የቀድሞ ሠራተኛ ማርቲን ግሪፊትስ "የትራምፕን ጦርነት ለማስቆም የሚያደርጉትን ጥረት ልንቀበለው ይገባል" ይላሉ።

ነገር ግን የቀድሞው የተባበሩት መንግሥታት ሰብዓዊ ገዳዮች ምክትል ዋና ፀሐፊ "ካለፉት 80 ዓመታት ውድቀት ልንማር የሚገባው አካታችነትን ነው። የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ተወካይ መሆን ያለባቸው የትራምፕ ጓደኞች ብቻ አይደሉም" ይላሉ።

ጉቴሬዝ በቅርቡ በሰጡት አስተያየት "በሕግ የበላይነት የሚያምኑ እንዳሉ ሁሉ፤ ይህ በኃይል ሕግ መተካት አለበት ብለው የሚያስቡ አሉ" ብለዋል።

ትራምፕ ስምንት ጦርነቶችን አስቁሚያለሁ ብለው ስለሚሉት ጉዳይ በቢቢሲ የተጠየቁት ዋና ፀሐፊው "የተኩስ አቁሞች ናቸው" የሚል ምላሽ ሰጥተዋል።

ከእነዚህም መካከል በሩዋንዳ እና ኮንጎ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ መካከል የተደረሰው የተኩስ አቁም ስምምነት ወዲያውኑ ፈርሷል።

ካምቦዲያ እና ታይላንድ አሁንም በድንበር ይገባኛል ጉዳይ እየተወቃቀሱ ይገኛሉ። ሕንድ ደግሞ ከፓኪስታን ጋር በተደረሰው ስምምነት የትራምፕ ሚና እምብዛም ነው ትላለች።

በኢራን እና በእስራኤል መካከል የነበረው የ12 ቀናት ጦርነት እንዲቆም ያደረገው ትራምፕ ጣልቃ ገብተው የአየር ጥቃት በመፈጸማቸው ነው።

ትራምፕ በፈጠሩት ተጽእኖ በጋዛ ያለው ጦርነት ቆሞ የፍልስጤማዊያን ስቃይ እንዲቀንስ ቢያደርጉም አሁንም እስራኤል ጥቃቶችን እየፈጸመች እንዳለ ይዘገባል።

የትራምፕ የሰላም ቦርድ ቅርፅ እየያዘ እየመጣ ባለበት በአሁኑ ወቅት የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታኒያሁ የቦርዱ አባል መሆን አጨቃጫቂ ሆኗል።

አንዳንድ የትራምፕ ተቺ የሆኑ ሰዎችም ቢሆን ፕሬዝደንቱ የፀጥታው ምክር ቤትን ሊገዳደሩ መቻላቸው ትክክለኛ እርምጃ ነው ይላሉ።

ትራምፕ የተባበሩት መንግሥታትን ስጋት ላይ የሚጥል ድርጅት ለማቋቋም እያቀዱ ያሉበት ጊዜ ከጉቴሬዝ የሥልጣን ማብቂያ ጊዜ ጋር ተገጣጥሟል። ዋና ፀሐፊው ሁለተኛ የሥልጣን ዘመናቸውን በዚህ የአውሮፓያን ዓመት መገባደጃ ላይ ያጠናቅቃሉ።

የዩክሬንን ጦርነት በአንድ ቀን አስቆማለሁ ሲሉ የዛቱት ትራምፕ፤ በአንድ ዓመት የሥልጣን ቆይታቸው ሰላም ማምጣት ቀላል ጉዳይ እንዳልሆነ ተረድተው ይሆናል።

በመካከለኛው ምሥራቅ የሚሰማው የጥይት ድምፅ "አነስተኛ" መሆኑን አድንቀው በዩክሬንም "በቅርቡ ሰላም ይመጣል" ሲሉ ተደምጠዋል።

ራሳቸውን የዓለም የሰላም ሊቀ-መንበር አድርገው የሚቆጥሩት ትራምፕ "እነሆ ለዓለማችን ሰላም" ሲሉ ጠንከር ያለ ንግግር አሰምተዋል።