ትራምፕ በሚኒሶታ የሚወሰደው እርምጃ "ረገብ እንደሚል" አስታወቁ

ስደተኞች ላይ በሚፈጸመው ወከባ ምክንያት ተቃውሞ በተነሳበት ሚኒሶታ ግዛት የሚወሰደው እርምጃ "በጥቂቱ ረገብ እንደሚል" ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ አስታወቁ።

በሚኒሶታ ሕዝባዊ ተቃውሞ ተባብሶ ሲቀጥል ሁለት አሜሪካውያን ተገድለዋል። ትራምፕ ከፎክስ ኒውስ ጋር ባደረጉት ቆይታ "ሁለቱም [ግድያዎች] መጥፎ ናቸው። ዋናው ነጥብ መጥፎ መሆናቸው ነው" ብለዋል።

ታኅሣሥ መግቢያ ላይ ረኔ ጉድ የተባለችው የ37 ዓመት ሴት በስደተኞች ጉዳይ መሥሪያ ቤት የፀጥታ ባልደረቦች ስትገደል ባለፈው ሳምንት ደግሞ አሌክስ ፕሬቲ የተባለው ግለሰብ መገደሉ ከፍተኛ ቁጣ አስነስቷል።

ሕዝባዊ ተቃውሞ ያስነሳው የአሌክስ ግድያ ዴሞክራቶች እና ሪፐብሊካኖችም ጭምር አስቆጥቷል።

የትራምፕ አስተዳደር የሚወስደውን እርምጃ ለማርገብ የወሰነውም ለዚህ ነው።

ሰኞ ዕለት የአገር ውስጥ ደኅንነት መሥሪያ ቤት በሚኒሶታ የሚወሰደውን እርምጃ የሚመሩት የድንበር ጥበቃ ኃላፊ ግሪጎሪ ቦቪኖ ከግዛቱ ለቅቀው እንዲወጡ ወስኗል።

የትራምፕ የድንበር ጉዳዮች ሹመኛ ቶም ሆማን ግሪጎሪ ቢቪኖን ተክተው ወደ ሚኒሶታ አቅንተዋል።

ቶም ሆማን ከሚኒሶታ አገረ ገዢ ቲም ዋልዝ፣ ከከንቲባ ጄኮብ ፍሬይ እና ከፀጥታ ባልደረቦች ጋር መወያየታቸውን በማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው አስታውቀዋል።

ጡረታ የወጡ ወታደሮች በሚታከሙበት ሆስፒታል ውስጥ የጽኑ ሕሙማን ክፍል ነርስ የነበረውን አሌክስ ግድያ "በጣም አሳዛኝ ክስተት" ሲሉ ትራምፕ ገልጸዋል።

አሌክስ "አገር በቀል አሸባሪ" በሚል መፈረጁን ይስማሙበት እንደሆነ በጋዜጠኞች ተጠይቀው "ያንን አልሰማሁም" ሲሉ መልሰዋል። አክለውም "መሣሪያ መያዝ አልነበረበትም" ብለዋል።

የአገር ውስጥ ደኅንነት ጸሐፊ ክርስቲ ኖም በበኩላቸው አሌክስ የተገደለው "ሽጉጥ እያወዛወዘ" ስለነበር ነው ብለዋል። በሕጋዊ መንገድ በአሌክስ ስም የተመዘገበውን መሣሪያ ከተቀማ በኋላ እንደተገደለም ገልጸዋል።

የፀጥታ ባልደረቦች የተኮሱበት መሣሪያውን አልሰጥም ስላለ "ራሳቸውን ለመከላከል" በሚል እንደሆነ ገልጸውም "በቦታው የተገኘው በሰላማዊ መንገድ ተቃውሞውን ለመግለጽ ሳይሆን ነውጥ ለማስነሳት ነበር" ብለዋል።

ትራምፕ በሚኒሶታ ግዛት ያሰማሯቸውን 3,000 የስደተኞች ኦፊሰሮች እንዲያስወጡ ጫናው በርትቷል።

ትራምፕ ከፎክስ ኒውስ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ በሚኒሶታ ያሰማሩትን ኃይል ተከላክለዋል።

"በሺዎች የሚቆጠሩ ወንጀለኞችን ከግዛቱ አስወጥተናል። የወንጀል ቁጥሩ ከፍተኛ ነበር። ቶም ሆማን በቦታው ይገኛል። የሚወሰደውም እርምጃ ይረግባል" ሲሉም ምላሽ ሰጥተዋል።

ስደተኞችን ወደ መጡበት አገር በመመለስ ላይ የተሰማሩት የዋይት ሀውስ አማካሪ ስቴፈን ሚለር ከሲኤንኤን ጋር ባደረጉት ቆይታ "ዋይት ሀውስ ለአገር ውስጥ ደኅንነት መሥሪያ ቤት በሰጠው መመሪያ መሠረት ተጨማሪ ኃይል ወደ ሚኒሶታ የተላከው ለማምለጥ የሞከሩ ወንጀለኞችን ለመያዝ ነው" ብለዋል።

የአሜሪካ የጉምሩክ እና ድንበር ጥበቃ "ይሄንን ፕሮቶኮል ለምን እንዳልተከተለ" ምርመራ እንደሚደረግም ገልጸዋል።

ከሪፐብሊካን ፓርቲ አመራሮች የተወሰኑት የአሌክስ ግድያ ላይ ምርመራ እንዲካሄድ ጠይቀዋል። የቨርሞንት አገረ ገዢ ፊል ስኮት እና የነብራስካ ሴናተር ፒት ሪካትስ ተቃውሟቸውን ከገለጹት መካከል ይጠቀሳሉ።

የነብራስካ ሴናተር ፒት ሪካትስ "አገሪቱ አስደንጋጭ ነገር ነው የተመለከተችው። በጉዳዩ ላይ ምርመራ መደረግ አለበት" ሲሉ በኤክስ ገጻቸው ጽፈዋል።