ከአዲስ አበባ ያመለጠው ኤርትራዊ ሕገ ወጥ የሰዎች አዘዋዋሪ ሱዳን ውስጥ በኢንተርፖል ተያዘ

በሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር በጥብቅ ሲፈለግ የነበረው ኤርትራዊው ኪዳኔ ዘካሪያስ ሀብተማርያም ሱዳን ውስጥ በዓለም አቀፉ የፖሊስ ተቋም ኢንተርፖል ተያዘ።

ኢንተርፖል የኤርትራዊውን ሕገ-ወጥ ሰው አዘዋዋሪ በቁጥጥር ሥር ማዋል የቻለው ያገኘውን መረጃ መሠረት በማድረግ የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች እና ሌሎች አገራት በወሰዱት እርምጃ መሆኑን አስታውቋል።

ከኢትዮጵያ ያመለጠው ኤርትራዊ ሕገ ወጥ ሰው አዘዋዋሪ ሁለት ጊዜ በኢንተርፖል የእስር ማዘዣ ወጥቶበት የነበረ ሲሆን፤ በኔዘርላንድስ በጥብቅ ከሚፈለጉ ዝርዝር ውስጥም ተካቷል።

በኢትዮጵያ ደግሞ በስደተኞች ግድያ እና በሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር ክስ በሌለበት የዕድሜ ልክ እስራት ተፈርዶበታል።

ከጥቂት ዓመታት በፊት ኪዳኔ በቁጥጥር ሥር ውሎ በአዲስ አበባ የፍርድ ሂደቱን እየተከታተለ ሳለ ፍርድ ቤት ቀጠሮ በነበረው ዕለት ማምለጡ የተዘገበው።

ኢንተርፖል ኤርትራዊው በሰዎች ዝውውር፣ በሕገ-ወጥ መንገድ የተገኘ ገንዘብ ሕጋዊ አስመስሎ በመጠቀም፣ ሰዎችን አፍኖ ማስለቀቂያ ገንዘብ በመጠየቅ እና በተያያዥ ወንጀሎች ከአውሮፓውያኑ 2019 ጀምሮ ሲፈልገው እንደቆየ አመልክቷል።

ኢንተርፖል ከወራት በፊት ስለ ተፈላጊው መረጃ ከደረሰው በኋላ ከኢትዮጵያ፣ ከሱዳን፣ ከኔዘርላንድስ፣ ከተባበሩት አረብ ኤምሬቶች፣ ከአውሮፓ የፖሊስ ተቋም-ዩሮፖል እና ከአፍሪካ ኅብረት የተወጣጣ የመርማሪዎች ቡድን በምርመራው መሳተፋቸውን ገልጿል።

የኤርትራዊው ሰው አዘዋዋሪ በቁጥጥር ስር መዋል በመሰል ሕገ-ወጥ ተግባር ላይ ለተሰማሩት ትልቅ ክስረት እንዲሁም ደግሞ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን መታደግ እንደሚያስችል ዓለም አቀፉ የፖሊስ ተቋም ገልጿል።

ኤርትራዊው ኪዳኔ ዘካሪያስ በቁጥጥር ስር ከዋለ በኋላ የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች፣ የኔዘርላንድስ እና የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት ተፈላጊውን በቁጥጥር ስር ለማዋል የተደረገውን የተቀናበረ ዘመቻ አወድሰዋል።

የኢትዮጵያ የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጄኔራል ደመላሽ ገ/ሚካኤል የፀጥታ አካላት ተጠርጣሪውን በቁጥጥር ስር ለማዋል ቀን ከሌት ሰርተዋል፣ ካሉ በኋላ ኤርትራዊው በኢትዮጵያ የዕድሜ ልክ እስራት እንደተፈረደበት አስታውሰዋል።

የኢንተርፖል የፖሊስ ዳይሬክተር ስቴፈን ካቫንጋህ የኤርትራዊው ተፈላጊ በቁጥጥር ስር መዋል አገራት በጋራ ሲሰሩ ሊገኝ የሚችለውን ውጤት ማሳያ ነው ብለዋል።

የኪዳኔ ዘካሪያስ ሀብተማርያም በፖሊስ መያዝን ተከትሎ ሌሎች በሕገ-ወጥ ተግባሩ ተሳታፊ ናቸው የተባሉ ሰዎችም በቁጥጥር ስር ሊውሉ የሚችሉ እንደሚኖሩ ተገልጿል።

ኪዳኔ ዘካርያስ ሀብተማርያም ማነው?

ኪዳኔ ዘካርያስ “የዓለማችን እጅግ አደገኛ እና ጨካኝ ሰው አዘዋዋሪ” በሚል በተደጋጋሚ በሰብአዊ መብት ተሟጋቾች ሲከሰስ ቆይቷል።

ለዓመታት በጦርነት በታመሰችው እና በተለይ ከኢትዮጵያ፣ ከኤርትራ እና ከሶማሊያ የሚነሱ ስደተኞች ወደ አውሮፓ ለመሻገር በሚሞክሩባት ሊቢያ ውስጥ በሺዎች የሚቆጠሩ ስደተኞች ታግተው የሚቆዩበት ካምፕ እንዳለውም ይነገራል።

ከስደተኞቹ እንዲሁም በሌሎች አገራት ከሚኖሩ ቤተሰቦቻቸው በግዳጅ ገንዘብ በመቀበል የሚታወቅ አደገኛ የወንጀል ቡድን መሪ እንደሆነም ይከሰሳል።

ይህ ቡድን ስደተኞችን በመድፈር፣ በማገት፣ በመደብደብ እና አጠቃላይ ሰብአዊ መብታቸውን በመግፈፍ በተፈጸሙ ከባድ በደሎች በርካታ ክሶች ቀርበውበታል።

ይህ ስቃይ የደረሰባቸው ሰዎች እንደሚሉት፤ የሚጠየቁት ገንዘብ ከ5,000 ዶላር እስከ 12,000 ዶላር ይደርሳል።

የስደተኞች ሰብዓዊ መብትን በተመለከተ ንቅናቄ በማድረግ የሚታወቁ የመብት ተሟጋቾች፤ ኪዳኔ “በርካታ ስደተኞች ላይ ላደረሰው በደል በሕግ እንዲጠየቅ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ መረባረብ አለበት” ሲሉ ድምጻቸውን ሲያሰሙ ቆይተዋል።