ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በኔዘርላንድስ ተፈላጊ የሆነውን ኤርትራዊ ሕገወጥ የሰዎች አዘዋዋሪን ኢትዮጵያ አሳልፋ ሰጠች
ኔዘርላንድስ በዓለም አቀፍ ወንጀሎች በጥብቅ የምትፈልገው ኤርትራዊው ሕገወጥ የሰዎች አዘዋዋሪ ተወልደ ጎይቶም ከኢትዮጵያ ተላልፎ ተሰጣት።
ተወልደ ጎይቶም በቅፅል ስሙ ወሊድ በሊቢያ በሺዎች የሚቆጠሩ ስደተኞችን በመዝረፍ እና በማሰቃየት ጭካኔ የተሞላባቸው አረመኔያዊ የሆኑ ሕገወጥ የሰዎች ዝውውር ንግድ በመፈጸም ወንጀል በአምስት ክሶች የኢትዮጵያ ፍርድ ቤት የጥፋተኝነት ውሳኔ አሳልፎበት ነበር።
በዚህም በ18 ዓመት ጽኑ እስራት እንዲቀጣ ተወስኖበታል።
ተወልደ ጥፋተኛ በሚል የተፈረደበት አማኑኤል ይርጋ ዳምጤ በሚል ስም እንደሆነ ዘ ጋርዲያን ውሳኔውን አስመልክቶ አውጥቶት በነበረበት ፅሁፍ የዘገበ ሲሆን፣ ተጎጂዎች ግን ሐሰተኛ ማንነት እንደሆነ ተናግረዋል።
በኔዘርላንድስ ጥያቄ መሰረት የ38 ዓመቱን ሕገወጥ የሰዎች አዘዋዋሪውን ኢትዮጵያ ለኔዘርላንድስ አሳልፋ የሰጠች ሲሆን፣ ግለሰቡም መስከረም 25/2015 ዓ.ም. ሺፖል አየር ማረፊያ መድረሱንም የኔዘርላንድ ዐቃቤ ሕግ አስታውቋል።
ኔዘርላንድስ ተወልደ ኤርትራውያን ስደተኞችን በከፍተኛ መጠን ሕገወጥ በሆነ መልኩ በማጓጓዝ በርካታ ኢ-ሰብዓዊ ተግባራት እንዲፈጸምባቸው እና በስደተኞች ወንጀልም ዓለም አቀፍ ዋና ተጠርጣሪ ነው ብላለች።
ወደ አውሮፓ ለመድረስ የሚሞክሩት ስደተኞች በሊቢያ ካምፖች ውስጥ በነበሩበት ወቅት ድብደባ፣ ረሃብ እና መደፈሮችን ጨምሮ አሰቃቂ ጥቃት ለዓመታት ተፈጽሞባቸዋል። በዚህም ምክንያት በርካታ ስደተኞች መሞታቸው ይነገራል።
በኔዘርላንድስ የሚገኙ የቤተሰብ አባላትም በእስር ላይ የሚገኙ ስደተኞች ጉዟቸውን እንዲቀጥሉ ለማድረግ ከፍተኛ ገንዘብ እንዲከፍሉ ተወልደን ጨምሮ ሕገወጥ የሰዎች አዘዋዋሪዎቹ አስገድደዋቸዋል።
ስደተኞቹ አውሮፓ ለመድረስ በሜድትራንያን ባሕር ላይ በተጨናነቁና ጥቅም ላይ መዋል ባልነበረባቸው ጀልባዎች የተጓዙ ሲሆን፣ በዚህም በርካታ ስደተኞች ላይመለሱ ጠፍተዋል።
ተወልደ ከአውሮፓውያኑ 2014 አስከ 2020 ባለው ጊዜ ውስጥ ኤርትራውያን ፍልሰተኞችን በሕገወጥ መንገድ በማጓጓዝ ግንባር ቀደም ሚና ተጫውቷል ብሏል።
ተወልደ በኢትዮጵያ በቁጥጥር ስር የዋለው መጋቢት 2020 ነበር። በሕገወጥ የሰዎች አዘዋዋሪነት በኔዘርላንድስም ሆነ በአውሮፓ በጥብቅ የሚፈለገውና በኋላ ያመለጠው ኤርትራዊው ኪዳነ ዘካርያስ ሃብተማርያም በኢትዮጵያ በቁጥጥር ስር ከዋለ ከአንድ ወር በኋላ ነበር።
ኪዳነ ከሚቀርቡበት በርካታ ክሶች መካከል ግድያ፣ ሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውር እና በሕገ ወጥ መንገድ የተገኘ ገንዘብን ሕጋዊ አስመስሎ መጠቀም የሚሉት ይገኙበታል።
ሁለቱ ሕገወጥ የሰዎች አዘዋዋሪዎች በሊቢያዋ ባኒ ዋሊድ ወይንም በስደተኞች አጠራር "ጎስት ሲቲ" የሚባል አንድ ግቢን ይጋሩ ነበሩ። ስደተኞቹ በዚህች ከተማ መጠነ ሰፊ ሕገወጥነት በመስፈኑ እና በርካታ ስደተኞች በመጥፋታቸውም ነው ይህንን የቅፅል ስም ለከተማዋ የሰጧት።
በርካታ ስደተኞች እንደሚሉት ሁለቱ ሕገወጥ የሰዎች አዘዋዋሪዎች በሺዎች የሚቆጠሩ ስደተኞችን ካሳ ይከፈለን በሚል አስረዋቸው እንደነበር ይናገራሉ።
ነውጠኛ የሚባለው ሕገወጥ የሰዎች አዘዋዋሪው ኪዳኔ በቁጥጥር ስር የዋለው በተባበሩት መንግሥታት አማካኝነት ከሊቢያ ወደ አዲስ አበባ የተመለሰ ኢትዮጵያዊ መንገድ ላይ አይቶት በመጠቆሙ ነበር።
ኪዳነ ከአንድ ዓመት እስር በኋላ የካቲት 2021 ላይ ለፍርድ በቀረበበት ወቅት ውሳኔ ከመተላለፉ በፊት መታጠቢያ ቤት ገብቶ ማምለጡ ይታወሳል።
ግለሰቡ የለበሰውን የእስር ቤት ብርቱካናማ ልብስ መታጠቢያ ቤት ውስጥ ለውጦ እንዳመለጠ የተነገረ ሲሆን፣ ሲጠብቁት የነበሩ ፖሊሶች በቁጥጥር ስር ውለው ምርመራ ተከፍቶባቸው ነበር።
ግለሰሰቡ እስካሁን ያለበት ባይታወቅም፤ የኢትዮጵያ ፍርድ ቤት በስምንት ክሶች ጥፋተኛ ሆኖ አግኝቸዋለሁ በማለት በሌለበት የእድሜ ልክ እስራት ተፈርዶበታል።
ኪዳነ በኔዘርላንድስ ብሔራዊ ተፈላጊ ሰዎች ዝርዝር ውስጥ ዋነኛ ተፈላጊ እንዲሁም በዓለም አቀፍ ደረጃም ተፈላጊ ከሆኑ ሰዎች ዝርዝር ውስጥ ተካትቷል።
የኔዘርላንድስ ዐቃቤ ሕግ ሁለቱን ሕገወጥ የሰው አዘዋዋሪዎችን እና ሌሎች የወንጀል ቡድኑ አባላትን ከስደት ጋር በተያያዙ ወንጀሎች በኔዘርላንድስ ወይም በአውሮፓ ኅብረት አባል አገራት ለፍርድ እንደሚያቀርብ አስታውቋል።
የወንጀል ምርመራው የሚካሄደው ከጣሊያን፣ ከዩሮፖል፣ ከኢንተርፖል እና ከዓለም አቀፉ የወንጀል ፍርድ ቤት ጋር በመተባበር መሆኑም ተገልጿል።
የኔዘርላንድስ ዐቃቤ ሕግ የ38 ዓመቱን ሕገወጥ የሰዎች አዘዋዋሪ ኢትዮጵያ አሳልፋ ለመስጠት ላደረገችው መልካም ትብብር ምስጋናውን አቅርቧል።