የኡጋንዳው ፕሬዝዳንት ልጃቸው ኬንያን እወራለሁ በማለታቸው ይቅርታ ጠየቁ

የኡጋንዳው ፕሬዝዳንት ዩዌሪ ሙሴቪኒ ከፍተኛ ወታደራዊ አመራር የሆኑት ልጃቸው የኬንያን መዲና ናይሮቢን እወራለሁ ማለታቸውን ተከትሎ ኬንያውንን ይቅርታ ጠይቀዋል።

ፕሬዝዳንቱ ይቅርታ ከመጠየቃቸው አንድ ቀን ቀደም ብሎ የኡጋንዳ ጦር ምድር ሃይል አዛዥ የነበረው ልጃቸውን ሙሆዚ ካይኒሩጋባን ከኃላፊነቱ አንስተውታል።

ሆኖም ሙሴቪኒ ነገሩን ለማብረድ በሚመስል መልኩ በተመሳሳይ ዕለት ለልጃቸው የሙሉ ጄነራልነት ማዕረግ ሰጥተው አማካሪያቸው አደርገውታውል።

ፕሬዝዳንቱ የሳቸው ተተኪ እንደሚሆን የሚታመነውን የ48 ዓመት ልጃቸውን ነው ከስልጣኑ ያሰናበቱት።

ጄነራል ካይኒሩጋባ በፖለቲካዊ ጉዳዮች እየሰጡ የነበረው አስተያየት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የመጣ ሲሆን በወታደራዊ ስርዓት ውስጥ ሊታይ የማይገባ ተግባር ነው የሚል ትችት ይቀርብባቸው ነበር።

ከሰልጣናቸው ከመሻራቸው በፊት በትዊተር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት ኬንያን የተመለከተ ያልተጠበቀ ጽሁፍ አጋርተዋል።

ሁለት የስልጣን ዘመናቸውን ጨርሰው ከሃላፊነት ከለቀቁት የቀድሞ የኬንያ ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ ጋር በስልክ ተነጋግሬ ነበር ያሉት ጄነራሉ ከስልጣን በመውረዳቸው መጸጸቴን ገልጬላቸዋለሁ ብለዋል።

“ከተወዳጁ ታላቅ ወንደሜ ጋር ያለኝ አንድ ችግር ብቻ ነው። እሱም ለሶስተኛ ዙር አለመወዳደሩ ነው። በቀላሉ ልናሸንፍ እንችል ነበር” የሚል ጽሁፍ በትዊር ገጻቸው ላይ አስፍረዋል።

በሌላ በኩል 600 ሺህ ለሚጠጉ የትዊተር ተከታዮቻቸው ባሰፈሩት ሌላ መልዕክት “እኔ እና ጦሬ ናይሮቢን ለመያዝ ሁለት ሳምንት አይወስድብንም” ብለዋል።

ታዲያ ይህ የትዊተር መልዕክት ሰውየው “ሃላፊነት የጎደላቸው” እና ከጎረቤት ሀገራት ጋር ያለውን ግንኙነት የሚያሻክሩ ናቸው የሚል ትችት እንዲቀርብባቸው አድርጓል።

ጄነራሉ ትንሽ ቆየት ብለው “ብዙም አትጨነቁ” የሚል ጽሁፍ በትዊተር ገጸቻው ላይ አስፍረዋል።

“አባቴ እንዳትሞክረው ስላለኝ የኬንያን ጦር የመደብደቡን ሃሳብ ትቼዋለሁ! ስለዚህ በኬንያ የምትገኙ ሰዎች አትጨናነቁ!” ብለዋል።

የቀድሞ የምድር ጦር አዛዡ የሙሴቪኒ ልጅ ኢትዮጵያን የተመለከቱ የተለያዩ አስተያየቶች በትዊተር ገጻቸው ላይ ሲያሰፍሩ ታይተዋል።

የኬንያ መንግስት በሰውየው አስተያየት የሰጠው ምላሽ ባይኖርም የኡጋንዳ ውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ “ከወንድም ጎረቤት ሀገራት ጋር ያለን ጠንካራ ግንኙነት” ይቀጥላል ብሏል።

ከኬንያው ፕሬዝዳንት ዊሊያም ሩቶ ጋር የተነጋገሩት የአወዛጋቢው ጦር መሪ አባት ሙሴቪኒ በልጃቸው የትዊተር ጽሁፍ “እጅግ ማዘናቸውን” ገልጸዋል።

“የቀድሞ የምድር ጦር አዣዥ በጄኔራል ሙሆዚ የጻፉት የትዊተር መልዕክት በተመለከተ ኬንያውያን ወንድም እና አህቶቻችንን ይቅርታ እጠይቃለሁ። አንድ ወታደራዊም ይሁን መደበኛ መሪ በወንድም ሀገራት ላይ ጣልቃ መግባት ወይም አስተያየት መስጠት የተገባ አይደልም” ብለዋል ሙሴቪኒ።

ጨምረውም ከሰራው “ስህተት” ባሻገር ለልጃቸው የሙሉ ጄነራልንት ማዕረግ መስጠታቸው አሳውቀው ምክንያቱን ሲገልጹ አሁንም “በርካታ መልኩ በጎ አስተዎጾ” ሊያደርግ ይችላል ብለዋል።

“ጄነራል ሙሆዚ ቆራጥ የፓን አፍሪካኒዝም አቀንቃኝ ነው” ሲሉ አክለዋል።

ልጃቸው በኬንያና የትግራይ ኃይሎችን በመደገፍ ከሚሰጧቸው አስተያየቶች ባሻገር ሩሲያ በዩክሬን ላይ የፈጸመችውን ወረራ ሲደግፉም ታይተዋል።

በሌላ በኩል ወደ ጠቅላይ ሚኒስትርነት እየመጡ ለሉት ጣሊያናዊቷ ጆርጅ ሜሎኒ “የማይፈሩ እና እውነተኛ” በመሆናቸው ጥሎሽ እንደሆነ የሚታመን 100 ከብቶችን እሰጣለሁ ብለው ነበር።

“የአውሮፓ ሴቶች የሚወዱት አበባ እንደሆነ አውቃለሁ። ይሄ ግን ፈጽሞ ሊገባኝ አልቻለም። በኛ ባህል የተወደደች ሴት የሚበረከትላት ላም ነው” ሲሉ በትዊተር ሰሌዳቸው ያሰፍሩት መልዕክት መነጋገሪያ ነበር።