ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በኢንተርፖል ይፈለግ የነበረው ሕገ ወጥ የሰዎች አዘዋዋሪ ሊቢያ ውስጥ ተያዘ
የሊቢያ መዲና ትሪፖሊ ባለስልጣናት በሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውር በኢንተርፖል ይፈለግ የነበረውን ግለሰብ በቁጥጥር ሥር ማዋላቸውን አስታወቁ።
በተባበሩት መንግሥታት እውቅና ያላው የሊቢያ መንግሥት አብድ አል-ራሃማን አል-ሚላድ በቁጥጥር ሥር እንደዋለ ይፋ ያደረገው ትናንት ነበር።
ቢጃ ተብሎ የተሚታቀው ይህ ግለሰብ ከሁለት ዓመታት በፊት የተባበሩት መንግሥታት የጸጥታው ምክር ቤት ማዕቀብ ጥሎበት ነበር።
አብድ አል-ራሃማን አል-ሚላድ ሰዎችን በሕገ ወጥ መንገድ በሊቢያ በኩል ወደመዳረሻዎቻቸው ይልክ ነበር። በተለያዩ ምክንያቶችም ሰደተኞችን አስሮ ያሰቃይ ነበር።
ከቅርብ ዓመታት ወዲህ መዳረሻቸውን አውሮፓ ማድረግ ለሚሹ አፍሪካውያንን ሊቢያ መሸጋገሪያ አገር ሆናለች።
የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች ስደተኞች በሊቢያ ከፍተኛ የሆነ ስቃይ እና ጥቃት ይደርስባቸዋል ይላሉ።
የአል-ሚላድ በቁጥጥር ሥር መዋል ከተሰማ በኋላ በሊቢያ የፈረንሳይ ኤምባሲ "ሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውርን ለመከላከል በሚደረገው ጥረት ይህ መልካም ዜና ነው" ብሏል።
አል-ሚላድ በኢንተርፖል ብቻ ሳይሆን በሊቢያ መንግሥት ጭምር ይፈለግ ነበር። በሊቢያ የሚገኙ ሚሊሻዎች አል-ሚላድ በቁጥጥር ሥር እንዳይውል ከለላ ሲሰጡ ቆይተዋል። በዚህም አል-ሚላንድን መያዝ ከባድ ሆኖ መቆየቱ ተነግሯል።
አብድ አል-ራሃማን አል-ሚላንድ ማነው?
እንደ ተባበሩት መንግሥታት መረጃ ከሆነ አል-ሚላንድ በሰሜን-ምዕራብ ሊቢያ በምትገኘው ዛዊያ ከተማ ያለውን ወደብ ይቆጣጠራል። በስፍራውም በስተደኞች ላይ ተደጋጋሚ የሆነ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ይፈጸማል።
እአአ 2017 ላይ የተባበሩት መንግሥታት አል-ሚላንድ እና ሌሎች የእርሱ ቡድን አባላት ሆነ ብለው የጦር መሳሪያ በመጠቀም የስደተኞች ጀልባ እንድትሰምጥ አድርገዋል ብሏል።
በዚዋያ ከተማ የስደተኞች ማጎሪያ ከፍቶ ስደተኞች አስሮ ያሰቃይ ነበር። ከሕገ ወጥ የሰው ልጆች ዝውውር በተጨማሪም በሕገ ወጥ የነዳጅ ንግድ ላይ ተሰማርቶ እንደነበረ ተጠቁሟል።
ባለፈው ዓመት መጋቢት ወር ላይ ዓለም አቀፉ የስደተኞች ድርጅት እንዳለው፤ ከአውሮፓውያኑ 2014 ጀምሮ ከ20 ሺህ ያላነሱ ስደተኞች በሜደትራኒያን ባህር ሰጥመው ሞተዋል።