ኮሮናቫይረስ ፡ ወገናቸውን ለመታደግ በመረጃና በጥናት የሚተጉት ዶክተር በአሜሪካ

አሜሪካ ውስጥ በዋሽንግተን ዲሲ በተላላፊ በሽታዎች ዙሪያ እየሠሩ የሚገኙት ዶ/ር ገበየሁ ተፈሪ የመጀመሪያ ከፍተኛ ትምህርታቸውን የተከታተሉት በጎንደር የህክምና ሳይንስ ኮሌጅ ነው።

የህክምና ትምህርታቸውን ካጠናቀቁ በኋላ ጋምቤላና አዲስ አበባ ውስጥ ለጥቂት ዓመታት በሙያቸው አገልግለው ወደ አሜሪካ በማቅናት ተጨማሪ የህክምና ትምህርት በመከታተል የውስጥ ህክምና [ኢንተርናል ሜዲሲን] እና በተላላፊ በሽታዎች ተመርቀዋል።

ዶ/ር ገበየሁ በአሁኑ ወቅት አሜሪካ ውስጥ የሚሠሩበት የጤና ተቋም በዋሽንግተን ዲሲ የተለያዩ የህክምና ማዕከላትን ያቀፈ ሲሆን በአካባቢው የተላላፊ በሽታ ጉዳዮችን በተመለከተ አማካሪ ሆነው እየሠሩ ይገኛሉ።

ዶ/ር ገበየሁ ባሉበት የቨርጂኒያ አካባቢ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው የኢትዮጵያና የኤርትራ ማኅበረሰብ አባላት ከመኖራቸው አንጻር በቅርበት ከመስራታቸው በተጨማሪ በሜሪላንድ፣ በዲሲ እና ቨርጂኒያ ውስጥ ከሚገኙት እነዚህ ማኅበረሰቦች በተጨማሪ ሌሎችንም በሙያቸው እያገለገሉ ይገኛሉ።

የዶ/ር ገበየሁ ተፈሪ ዋነኛ ትኩረት በኤችአይቪ፣ ሄፐታይተስ ቢ፣ ሲ እና ሌሎችም ተላላፊ በሽታዎች ላይ ሲሆን፤ የሥራ ኃላፊነታቸውም ከእነዚሁ በሽታዎች ጋር ከመያያዙ በተጨማሪ በአካባቢው ባሉ ዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ በተላላፊ በሽታዎች ላይ በሚደረጉ ጥናቶች ዙሪያ የድርጅቱ ተወካይ በመሆን ይሠራሉ።

ሙያን ለማኅበረሰብ

ሥራቸውን በሚያከናውኑበት ቦታና የተለየ ትኩረት ከሚሰጧቸው በሽታዎች አንጻር ይህ አጋጣሚ "ለማኅበረሰቡ በሙያዬ ብዙ ነገር ማብርከት እንድችል አድርጎኛል" ይላሉ ዶ/ር ገበየሁ።

በዚህም ከሰባት ዓመታት በፊት ማኅበረሰቡን ለማገልገል በማሰብ የእራሳቸውን ድረ ገጽ ጀመሩ። በድረ ገጻቸውም ዶ/ር ገበየሁ ኢትዮጵያውያንና ኤርትራውያንን ሊጠቅሙ ይችላሉ የሚሏቸውን የጤና መመሪያዎችን፣ ማብራሪያዎችንና የተለያዩ መረጃዎችን ወደ አማርኛ በመተርጎም ይጋራሉ።

የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ከተከሰተበት ጊዜ አንስቶ ደግሞ የተለመደውን የህክምና አገልግሎት መረጃዎችን ገታ አድርገው ስለ አዲሱ በሽታ ይጠቅማሉ ብለው ያሰቧቸውን መረጃዎችን በየቀኑ እያጋሩ ይገኛሉ።

ዶ/ር ገበየሁ "በተቻለኝ አቅም ሕዝቡን ለማገልገል የወሰድኩትን መሃላ ለማሳካት እጥራለሁ። ከድረ ገጹ በተጨማሪ በተለያዩ መገናኛ ብዙሃን ላይ በመቅረብ ጠቃሚና ነፍስ አዳን ይሆናሉ ብዬ የማስባቸውን መረጃዎች አካፍላለሁ" ይላሉ።

አክለውም ማኅበረሰቡ በሚረዳው በቋንቋ የሚቀርቡ መረጃዎች እጥረት ይኖራል ብለው ስላመኑ፤ እንዲሁም በተለይ በኮቪድ-19 ዙሪያ የተለያዩ የሚያሳስቱ መረጃዎች በማኅበራዊ ድረ ገጾች እየተስፋፉ በመሆናቸው ይህንን "እንደግል ግዴታዬ በመውሰድ የድርሻዬን ላበርክት ብዬ ነው የጀመርኩት" በማለት ስለሥራው አስፈላጊነት ይናገራሉ።

"ኅብረተሰቡ ለእንደዚህ ዓይነቱ መረጃ አዲስ ነው" የሚሉት ዶ/ር ገበየሁ "በሚዲያ ይወራ እንጂ፣ ስል ተላላፊ በሽታዎች ሥርጭትና ጉዳት፣ ስለቫይረስ መሰረታዊ እውቀት የሌለው ሰው በሚረዳው ቋንቋ መረጃ መቅረብ አለበት ብዬ ነው እያስተማርኩ ያለሁት" ይላሉ።

ትክክለኛ የጤና መረጃ

በዚህ ዘመን የምድራችን አሳሳቢው የጤና ጠንቅ የሆነውና አሜሪካንን ክፉኛ ያጠቃት የኮሮናቫይረስ ልክ እንደ አፍሪካ አሜሪካዊያን እና ሂስፓኒክ ዝርያ እንዳላቸው ማኅረሰቦች በዚያ ያሉ ኢትዮጵያውያንና ኤርትራውያን ማኅበረሰቦችም ተጋላጭ ናቸው ይላሉ ዶ/ር ገበየሁ።

እነዚህ ማኅበረሰቦች አብዛኛዎቹ የተሰማሩበት የሥራ ዘርፍ፣ የሚኖሩባቸው አካባቢዎች፣ የአኗኗር ዘይቤያቸው እንዲሁም ባህላቸው ከሰዎች ጋር የሚያገናኝ በመሆኑ ለበሽታው ያላቸውን ተጋላጭነት ከፍ እንደሚያደርገው ያስረዳሉ።

"ከዚያም በተጨማሪ ወረርሽኙ ያልታሰበ በመሆኑ ከማኅበረሰባችን አንዳንዶች ነቃ ብለው የሚያስፈልገውን እርምጃ ቢወስዱ እንኳን ብዙዎች ግን ከመረጃ ማጣትና ከመዘናጋት የተነሳ ተጠቂ የሆኑ ነው" በማለት አመልክተው ይህንን የመረጃ ክፈተት ለመሙላት በሙያቸው እየጣሩ እንደሆነ ዶ/ር ገበየሁ ይናገራሉ።

ማኅበረሰቦቹ በተለይ ለወረርሽኙ ተጋላጭ የሚሆኑት ከባህላቸውና ከአኗኗራቸው የተነሳ "በስፋት መገናኘታቸው፣ በመደበኛነት መጠያየቃቸው እና በሌሎች የተለያዩ ምክንያቶች ለቫይረሱ በመጋለጣቸው በቫይረሱ የመዛመትና የመሠራጨት ጉልበት የተነሳ ብዙዎችን ጉዳት ላይ ጥላሏል" በማለት ትኩረት የሚሻውን የበሽታው መተላለፊያ መንገድን ትኩረት ይሰጡታል።

ዶክተር ገበየሁ በተለይ በበሽታው ተጠቂ የሆኑት የማኅበረሰቡ ክፍሎት ሰፋ ያለ የቤተሰብ አባላት ያላቸው እንደነበሩ አመልከተዋል።

በሽታውበዓለም ዙሪያ በርካቶችን እየያዘ በሺህዎች የሚቆጠሩትን ለሞት እየዳረገ ሲሄድ በአሜሪካ ሚሊዮኖች በቫይረሱ መያዘቸው እንዲሁም ከ200 ሺህ በላይ የሚሆኑት በበሽታው ሰበብ ሞተዋል።

በሽታውን ለማወቅና እራስን ለመጠበቅ ትክክለኛ መረጃ ማግኘት ጠቃሚ እንደሆነ የሚናገሩት ዶ/ር ገበየሁ እንደሚሉት የተለያዩ ወገኖች እርስበርስ የሚጣረሱና አሳሳች መረጃዎችን በማኅበራዊ ሚዲያዎች በኩል በቀላሉ ስለሚያሰራጩ የሚታመኑ የመረጃ ምንጮችን መጠቀምን ይመክራሉ።

ለዚህም መፍትሄው "እንደ ዓለም ጤና ድርጅትና በየአገሩ ያሉ ተመሳሳይ ተቋማትን ምክር መከተሉ ተመራጭ ነው" የሚሉት ዶ/ር ገበየሁ፤ የሚወጡ መረጃዎችን በተመለከተም በመረዳትና ተግባራዊ በማድረጉ በኩል ልዩነቶች እንዳሉ ይናገራሉ።

ከመረጃዎች አንጻር "በህክምናው ዘርፍ በተሰማሩ ሰዎች መካከል ልዩነት አለ። ሥራችን በተላላፊ በሽታዎች ላይ ያተኮርንና በሌላ ዘርፍ የተሰማሩ ሐኪሞች እንኳን ነገሮችን የመረዳት ሁኔታው የተለያ ሊሆን ይችላል። ለዚህ ነው ማኅበረሰቡ የሚያገኘው መረጃ በሚገባው ቋንቋና ከመሆኑ በተጨማሪ ትክክለኛ መሆኑን ማረጋገጥ ያስፈልጋል" ይላሉ።

ስለዚህም ዶ/ር ገበየሁ እንደሚሉት ዋና ነገር መሆን ያለበት "ለማኅበረሰቡ የሚደርሰው መረጃ በሙያው ላይ በተሰማሩ ሐኪሞች መሆን አለበት" ባይ ናቸው። "በተላላፊ በሽታ የተጠቁ ህሙማን የሚከታተሏቸውን ወይም የሚያክሟቸውን ባለሙያዎች ምክርን መከተል በሽታውን ለመካላከልና ከበሽታው ለመዳን ትልቅ አስተዋጽዖ አለው" ይላሉ።

የወርሽኞች ስጋት

"ኮቪድ-19 ስም እና በሽታው አዲስ ይምሰል እንጂ በየተላላፊ በሽታዎች ቁጥጥር ዘርፍ የቆየ ቫይረስ ነው" የሚሉት ዶ/ር ገበየሁ፤ ከኤችአይቪ አንስቶ የተለያዩ በሽታዎችን እያጠኑ ላሉ እሳቸውን ለመሰሉ ባለሙያዎች አዲስ አይደለም።

ተላላፊ በሽታዎች ላይ የተለየ ትኩረት አድረገው የሚሰሩት ዶ/ር ገበየሁ በሽታ አምጪ የሆኑ ቫይረሶች ባህሪያቸው አንዱ ከአንዱ ሊለያይ እንደሚችል ይናገራሉ። በዚህ ዘርፍም የተላላፊ በሽታዎችን ባህሪያትን ለማወቅ እና ለማዳን የሚረዱት ጥናቶች በሰዎች ላይ ብቻ ሳይሆን በአካባቢው ባሉ እንስሳት ላይ ጭምር እንደሆነ ይናገራሉ።

"ኮሮናቫይረሶች ከሰው ጋር አብረው የኖሩ ናቸው። በአጠቃላይ ወደ አራት የሚደርሱ አሉ። ከጥንት ጀምሮ ሰው ላይ ተራ ጉንፋንና የመሳሰሉ የጤና ዕክሎችን የሚያስከትሉ ናቸው። እነርሱም ገዳይ አይደሉም" ይላሉ።

ይሁንና ኮሮናቫይረስም [ኮቪድ-19] ምንም እንኳን በርካቶችን ለሞት ቢዳርግም ከሌሎቹ ጋር ተመሳሳይነት እንዳለው የሚናገሩት ዶ/ር ገበየሁ "በጣም ገዳይ የሆነ ቫይረስ ሰዎችን ገድሎ አብሮ ይከስማል" በማለት ሞትን በሚያስከትሉ ቫእረሶች መካከል ያለውን ልዩነት ያስረዳሉ።

ጨምረውም አደገኛ ወይም ገዳይ የሚባል ቫይረስ አብዛኛውን ጊዜ የሚይዘውንና የሚገድለውን ገድሎ አብሮ የሚሞት መሆኑን አመልክተው፤ ለእንዲህ አይነት ቫይረሶች ክትባትና መድኃኒት ለማግኘት ፈታኝ ነው ይላሉ።

እንደምሳሌም ሳርስ ቁጥር አንድ የተሰኘው ቫይረስ የሚጠቅሱት ዶ/ር ገበየሁ፤ ይህ በሽታ ተከስቶ ጉዳት አድርሶ በመክሰሙ ክትባት ቢዘጋጅም በሽታው እንደጠፋ የቀረ።

የተላላፊ በሽታዎችን በሚያጠኑና በሚያክሙ ባለሙያዎች ዘንድ አሳሳቢውና አስፈሪው ነገር "እየደጋጋሙ የሚመላለሱ ወረርሽኞች ናቸው" ይላሉ፤ ምክንያቱንም ሲያስቀምጡ እንዲህ አይነት ወረርሽኞች ባህሪያቸው የሚጨበጥ አለመሆኑን ይናገራሉ።

በተለያዩ ቫይረሶች መካከል የሚፈጠር መዛመድም አደገኛ ውጤትን ሊያስከትል እንደሚችል የሚናገሩት ዶ/ር ገበየሁ "በሙያችን 'ቫይረስ ሴክስ' የሚባል ነገር አለ። ሁለት ቫይረሶች እርስ በእርስ 'ጄኔቲክ ኮድ' [የዘረመል አወቃቀር ይዘት] በመቀያየር አዲስ ቫይረስ ይፈጥራሉ ወይም ልጅ ይወልዳሉ እንላለን።"

ለምሳሌ ይህ ኮቪድ-19 ከሜርስ ጋር ቢገናኝና ዘረመል ቢለዋወጡ አደገኛ ውጤትን ሊያስከትሉ ይችላሉ፤ ምክንያቱም ሜርስ ገዳይ ነው የጎደለው ከሰው ወደ ሰው መተላለፍ ብቻ ነው። ኮቪድ-19 ደግሞ ነባርና አደገኛ የጤና እክል ያለው ሰው ካልሆነ በስተቀር የመግደል አቅሙ ደካማ ነው። ሆኖም ግን ከሰው ሰው የመተላለፍ አቅሙ በጣም ፈጣን ነው።

"ለዚህም ነው ሁለቱ ቢገናኙና የባህሪይ መወራረስ ቢፈጠር በጣም አደገኛ ቫይረስ ሊወልዱ/ሊፈጥሩ ይችላሉ" ብለው ዶ/ር ገበየሁ በቫይረሶች መካከል የሚኖር መዛመድ አንደኛው ከሌላኛው አደገኛ ባህሪዎችን በመውሰድ አደገኛ ውጤትን ሊያስከትሉ እንደሚችሉ ያስረዳሉ።

ዶክተር ገበየሁ እንደሚሉት ለሰው ልጆች ጤና ጠንቅ የሆኑ ቫይረሶች በአንድ ስያሜ የተለያዩ ሊሆኑ ይችላሉ። "ለዚህ ጥሩ ምሳሌ የሚሆነው ኤችአይቪ ነው" የሚሉት ዶክተሩ፤ "ብዙ ሰው አንድ ዓይነት ኤችአይቪ ያለ ይመስለዋል" ይላሉ።

ነገር ግን "ሁለት አይነት የኤችአይቪ ዓይነቶች ያሉ ሲሆን፤ አንደኛው በአራት የሚከፈል ሲሆን ከእነርሱ መካከል ደግሞ አንደኛው 14 ዝርያዎች ያሉት የቫይርስ ዓይነት ነው" በማለት ከዚህ ሁሉ ዓመታት በኋላ እንኳን መድኃኒት ማግኘት አስቸጋሪ የሆነው በዚህ የቫይረሶቹ አይነት መብዛት እንሆነ ያመለክታሉ።

ሲያጠቃልሉም በዚህ ዘመን የተከሰተውን ወረርሽኝን በተመለከተ በሽታው እየቀነሰ አለመሆኑ ብቻ ሳይሆን እየተስፋፋ መሆኑ ብዙ ሰዎች ላይ ፍርሃትን እንደሚፈጥር የሚጠቅሱት ዶ/ር ገበየሁ፤ በዚህም ሳቢያ በሰዎች ዘንድ የተፈጠረውን ፍርሃት በመጠቀም ትክክለኛ ያልሆኑ መረጃዎች ሊስፋፉ ስለሚችሉ የመጠንቀቅን አስፈላጊነት ያሰምሩበታል።