ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የአሜሪካ ምርጫ፡ በሐሰት ትዊተሬ ተጠልፏል ያለው ጋዜጠኛ ታገደ
ሲ-ስፓን የተባለው የቴሌቭዥን ጣቢያ የፖለቲካ አርታኢው ባለፈው ሳምንት በሐሰት "ትዊተሬ ተጠልፏል" ማለቱን ካመነ በኋላ አግዶታል።
የፕሬዘዳንት ዶናልድ ትራምፕ እና የተፎካካሪያቸው ጆ ባይደንን ሁለተኛ ክርክር ይመራል ተብሎ የነበረው ጋዜጠኛ ስቲቭ ስከሊ፤ ከትራምፕ አማካሪ ምክር መጠየቁም ተዘግቧል።
ይህ ምክክር ውዝግብ ሲያስነሳ፤ ጋዜጠኛው ትዊተሩ መጠለፉን ተናግሯል። "የሙያ አጋሮቼን ስላሳፈርኩ ይቅርታ እጠይቃለሁ" ብሏል።
በፖለቲካው ታዋቂ የሆነው ጋዜጠኛው፤ በሐሰት የትዊተር አካውንቴ ተጠልፏል የማለቱ ዜና የተሰማው የፕሬዘዳንቱን እና የዴሞክራት እጩውን ክርክር ይመራል በተባለበት ቀን ነው።
ትራምፕ በኮቪድ-19 በመያዛቸው ሁለተኛ ዙር ክርክሩ በበይነ መረብ እንዲካሄድ ሐሳብ ቢቀርብም፤ ትራምፕ ሐሳቡን አልተቀበሉትም።
ትራምፕ ባለፈው ሳምንት ጋዜጠኛው ስቲቭ "መቼም ቢሆን እኔን አይደግፍም" ሲሉ ተችተውታል።
ስቲቭ በምላሹ፤ የቀድሞ የዋይት ሀውስ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አንቶኒ ስካራሙቺን ጠቅሶ፤ "ለትራምፕ መልስ ልስጣቸው" ሲል ትዊተር ላይ ጽፏል።
ስቲቭ ይህንን ትዊት የጻፈው ክርክሩን እንዲመራ መመደቡን ተከትሎ በርካቶች ሲተቹት በመበሳጨቱ እንደሆነ ተናግሯል። ትዊቱን ከለጠፈ በኋላ የጻፈው ነገር ውዝግብ እንዳስነሳ ሲገነዘብ ግን ትዊተሬ ተጠልፎ ነው ብሎ ዋሽቷል።
"ትዊተሬ ተጠልፏል ያልኩት ውሸት ነው። ድርጊቴ ስህተት ነበር" ብሏል።
ትራምፕ ጋዜጠኛው ዋሽቶ እንደነበር ማመኑን ተከትሎ "ልክ ነበርኩ! ስቲቭ መዋሸቱን አምኗል" ብለዋል።
ሲ-ስፓን ጣቢያ ጋዜጠኛው መዋሸቱን ማመኑን ገልጾ፤ "ዜናው አሳዝኖናል። ድርጊቱን አንደግፍም። ጉዳዩ ረገብ እስኪል ከጣቢያው ይርቃል። ከዛ ግን ለጣቢያው ግብዓት የሚሆን ችሎታ እንዳለው ስለምናምን አብሮን ሊቀጥል ይችላል" የሚል መግለጫ አውጥቷል።
ጋዜጠኛው ለ30 ዓመታት ፕሬዘዳንታዊ ክርክር መርቷል። ዘገባዎቹ ሚዛናዊ እንደሆኑም ይነገርለታል።