በመተከል ዞን ተጨማሪ የሚሊሻ ምልመላ እየተካሄደ መሆኑ ተጠቆመ

በቤንሻንጉል ዞን መተከል ዞን ስር ባሉ ሰባት ወረዳዎች የሚሊሻ ስልጠና መሰጠቱን የክልሉ ኮሙኑኬሽን ኃላፊ አቶ መለሰ በየነ ለቢቢሲ ገለፁ።

አቶ መለሰ እንደገለፁት ከሆነ በቤንሻንጉል ክልል መተከል ዞን አካባቢ አሁን በተደጋጋሚ የሚፈጠሩ የፀጥታ ችግሮችን በመደበኛ የሕግ ማስከበር የሚቻል ስላልሆነ ከመስከረም 11፤ 2013 ዓ. ም ጀምሮ ለሶስት ወራት የሚቆይ የኮማንድ ፖስት ታውጇል።

የኮማንድ ፖስቱ በመከላከያ ሰራዊት የሚመራ ሲሆን፣ የፌደራል እና የክልሉ ፖሊስ በጋራ ሰላም የማስከበሩን ስራ እየሰሩ መሆኑን ገልፀዋል።

በዞኑ ከዚህ ቀደም የነበሩ የሚሊሻ አባላት እንዲሁም አዲስ ምልመላ ተካሂዶ ስልጠናው ላለፉት ሶስት ቀናት መሰጠቱን ኃላፊው ጨምረው ተናግረዋል።

በዞኑ ከሚገኙ ሁሉም ወረዳዎች የተመለመሉት እነዚህ የሚሊሻ አባላት ከሁሉም ብሔር ብሔረሰቦች መመልመላቸውን የሚገልፁት ኃላፊው፣ ከስልጠናውም በኋላ በቂ ትጥቅ አስታጥቆ የፀጥታ መዋቅሩን እንዲደግፉ እንደሚደረግ ተናግረዋል።

ከዚህ ቀደም የሚሊሻ አባል የነበሩና እድሜያቸው ያልገፉ አባላት በአሁኑ ስልጠና ላይም መካተታቸውን የገለፁት አቶ መለሰ፣ እንደየቀበሌው ስፋት ከ15 እስከ 20 የሚሆኑ አዳዲስ አባላት መመልመላቸውን ተናግረዋል።

ምልመላው የብሔር ብሔረሰቦችን ተዋፅኦ የጠበቀ መሆኑንም የገለፁት ኃላፊው፤ ስልጠናው ለተከታታይ ሶስት ቀናት በመከላከያ ሠራዊት አባላት እና ፖሊሶች መሰጠቱን ተናግረዋል።

በአሁኑ ወቅት በመተከል ዞን እየተንቀሳቀሰ የሚገኘው የኮማንድ ፖስቱ ከክልሉ እንዲሁም ከፌደራል ፖሊስ ጋር በጥምረት የሚሰራ ሲሆን፤ ለአካባቢው ሰላም መደፍረስ ዋነኛ ምከንያት ናቸው ተብለው የሚጠረጠሩ ሰዎች በቁጥጥር ስር እየዋሉ መሆኑን አስረድተዋል።

ክልሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን በተገኙበት በአካባቢው የሚፈጠረውን የሰላም መደፍረስ ለመፍታት ምን መደረግ አለበት የሚለውን በተደጋጋሚ ውይይት ማካሄዱንም ኃላፊው ጨምረው ገልፀዋል።

ኮማንድ ፖስቱ ሁለት ዓይነት ሥራዎችን እንደሚሰራ የተናገሩት ኃላፊው፣ ቀዳሚው የሕዝብ ግንኙነት ሥራ መሆንኑ አስረድተዋል።

በሕዝብ ግንኙነት ሥራው የክልል፣ ዞንናወረዳ ከፍተኛ አመራሮች፣ ተሰሚነት ያላቸው ታዋቂ ግለሰቦች፣ የአገር ሽማግሌዎች የሃይማኖት አባቶች፣ ወጣቶች፣ እንዲሁም ሴቶች የተሳተፉበት መድረክ መካሄዱን ገልፀዋል።

በክልል ደረጃ የጦር መሳሪያ እጥረት አለ ያሉት ኃላፊው ፤ ነገር ግን በጣም ተጋላጭ የሆኑ ቀበሌዎችና፣ ጎጦችን በመለየት ለሰልጣኝ ሚሊሻ አባላት መሳርያ ማስታጠቅ መታቀዱንም አክለው ተናግረዋል።

ከዚህ ቀደም ማንነታቸው በማይገለጽ አካላት ተደጋጋሚ ጥቃቶች እየተፈጸሙ በርካታ ንጹሃን ዜጎች በመተከል ዞን ውስጥ ተገድለዋል።

በዞኑ በሚከሰተው የፀጥታ ችግር እጃቸው አለበት የተባሉ እና ኃላፊነታቸውን በአግባቡ ባለመወጣት የተጠረጠሩ ከክልል እስከ ወረዳ ያሉ አመራሮች ላይ ፖለቲካዊ እርምጃ መወሰዱን ይታወሳል።