ቻይና የዘጠኝ ወር ሕፃን ላይ ትኩስ ቡና የደፋን ግለሰብ ለማደን ወደ አውስትራሊያ ፖሊስ ላከች

ቻይና ከሁለት ዓመት በፊት በአንድ ሕፃን ላይ የፈላ ቡና በመድፋት ከባድ ጉዳት እንዳደረሰ የተጠረጠረን ግለሰብ ለማደን የሚደረገውን ጥረት ለማገዝ ወደ አውስትራሊያ የፖሊስ ቡድን ላከች።

የዘጠኝ ወሩ ሕፃን ጥቃት የተፈፀመበት ቤተሰቦቹ በአውስትራሊያዋ ብሪዝበን ከተማ ደቡባዊ ክፍል በሚገኝ ፓርክ ውስጥ እየተዝናኑ በነበሩበት ወቅት ነው።

ሕፃኑ በተደፋበት ትኩስ ቡና ፊቱ እና ከንፈሮቹ ላይ ከፍተኛ የቃጠሎ ጉዳት ደርሶበታል።

ተጠርጣሪው ማንነቱ በፖሊስ ከመለየቱ በፊት አገሪቷን ለቆ የወጣ ሲሆን አሁን ላይ ቻይና ውስጥ እንደሚገኝ ባለሥልጣናት ገልፀዋል።

በአውስትራሊያ የቻይና አምባሳደር የሆኑት ሺያው ቺየን ማክሰኞ ዕለት የፖሊስ ቡድኑ የምርመራ ሥራውን ለማገዝ ወደ ብሪዝበን ከተማ እንደሚሰማራ ገልጸዋል።

"ይህን ችግር ለመፍታት እና አስፈላጊውን እርምጃ ለመውሰድ ቁርጠኛ ነን" ብለዋል ሺያው በካንቤራ ለጋዜጠኞች ሲናገሩ።

ቡድኑ፣ በትክክል ምን እንደተፈጠረ፣ እንዴት እንደተከሰተ እንዲሁም ሁለቱ ወገኖች እንዴት አብረው መስራት እንደሚችሉ ለማየት ከአውስትራሊያ ባለሥልጣናት ጋር እንደሚሰሩም አምባሳደሩ ተናግረዋል።

የኩዊንስላንድ ፖሊስ እና የአውስትራሊያ ፌደራል ፖሊስ በጋራ በሰጡት መግለጫም የቻይና ባለሥልጣናት ልዑካን ድጋፍ እያደረጉ እንደሆነ በመግለፅ ተጠርጣሪው ያለበትን ቦታ ለማወቅ እያደረጉት ላለው ትብብር ምስጋና አቅርበዋል።

ቻይና ከአገሪቷ ውጭ ወንጀል የፈፀሙ ዜጎቿን ተጠያቂ የምታደርግበት ሕግ እንዳላትም የጋራ መግለጫው ጠቅሷል።

33 ዓመቱ አንደሆነ የተገለፀው ተጠርጣሪው ከባድ የአካል ጉዳት በማድረስ የእስር ማዘዣ ወጥቶበታል። ይህ ክስ በአውስትራሊያ ሕግ የእድሜ ልክ እስር ሊያስቀጣ የሚችል ነው።

ፖሊስ እንደገለፀው ተጠርጣሪው "ከቦታ ቦታ እየተዘዋወረ" የሚሰራ ሰራተኛ ሲሆን ከአውሮፓውያኑ 2019 እስከ 2024 ባሉት ጊዜያት ብቻ ለበርካታ ጊዜ ወደ አውስትራሊያ ተጉዟል። እዚያም በቪክቶሪያ ግዛት እና በኒው ሳውዝ ዌልስ እንደቆየ ተገልጿል።

በሕፃኑ ላይ የተፈፀመው ጥቃት በአውስትራሊያ ከፍተኛ ቁጣ ቀስቅሷል።

ሕፃኑ ነሐሴ 2024 ላይ ጥቃቱ ከተፈፀመበት በኋላ በነበሩት ሳምንታት ውስጥ ብዙ ጊዜ የቆዳ ቀዶ ሕክምና ተደርጎለታል።

ከሦስት ወር በኋላም ቤተሰቦቹ ልጃቸው አሁንም በትከሻው እና በአገጩ አካባቢ እና ሌሎች የአካል ክፍሎቹ ላይ ጠባሳ ቢኖረውም እንደሚንቀሳቀስ ተናግረዋል።

ለሕፃኑ መታከሚያ ከ230 ሺህ ዶላር በላይ በኦንላይን ተሰብስቦለታል።