በመከላከያ ሠራዊት እና በትግራይ ኃይሎች መካከል ግጭት መካሄዱን ዲፕሎማቲክ ምንጮች ተናገሩ

በኢትዮጵያ መንግሥት እና በትግራይ ኃይሎች መካከል ግጭት መካሄዱን የፈረንሳይ ዜና ወኪል ኤኤፍፒ እና ሮይተርስ የደኅንነት እና የዲፕሎማቲክ ምንጮችን ጠቅሰው ዘገቡ።

በሰሜን ኢትዮጵያ የአማራ እና ትግራይ ክልል አዋሳኝ አካባቢዎች ከዚህ ሳምንት መጀመሪያ አንስቶ ግጭቶች እየተካሄዱ መሆናቸውን የሚያመለክቱ ዜናዎች እየተሰሙ ቢሆንም ተጨባጭ መረጃ ማግኘት አዳጋች ሆኖ ቆይቷል።

ግጭቶች የተቀሰቀሱት ጸለምት በሚባለው የአማራ እና የትግራይ ክልሎች በይገባኛል በሚወዛገቡበት እና በአማራ ክልል ቁጥጥር ሥር በሚገኛው አካበቢ መሆኑን ያመለከተው የዜና ወኪሉ፤ አንድ የደኅንነት ምንጭ "ሁኔታው እየተባባሰ እየሄደ ነው" ሲሉ እንደነገሩት ገልጿል።

በተጨማሪም ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ ዲፕሎማሲያዊ ምንጭ ለኤኤፍፒ እደንተናገሩት የትግራይ ኃይሎች "ከኢትዮጵያ ሠራዊት እና ከአማራ ሚሊሻዎች" ጋር እየተዋጉ ነው።

ምንጩ አክለውም "ባለፉት ቀናት ግጭቶች እንደነበሩ የተረጋገጠ ነው፤ ነገር ግን ዛሬ [ሐሙስ] ስላለው ሁኔታ የምናውቀው ነገር የለም" ብለዋል።

የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የምሥራቅ አፍሪካ ጉዳዮች አማካሪ አቶ ጌታቸው ረዳ ረቡዕ ዕለት በማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ላይ "ህወሓት ውስጥ የሚገኙ የሥልጣን ጥም ያለባቸው ግለሰቦች…ትግራይን ወደ ሌላ ዙር ጦርነት ሊያስገቧት እንቅስቃሴ እያደረጉ ይገኛሉ" በማለት በትግርኛ ጽፈዋል።

የቀድሞው የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት አቶ ጌታቸው፤ ግጭት መካሄዱን በሚያመለክት ሁኔታ የህወሓት መሪዎች ወጣቶችን ለጉዳት የሚዳርግ የጦር ስልት መከተላቸውን ጠቅሰው "...ከእንግዲህ አጉል መስዋዕትነት አልከፍልም ብለህ ተቃውሞህን አሰማ" በማለት ጥሪ አቅርበዋል።

አንድ ስማቸው ያልተጠቀሰ የአካባቢው ነዋሪ ግጭቶች መካሄዳቸውን አረጋግጠዋል። ነገር ግን ኤኤፍፒ ለፌደራል መንግሥቱ ሠራዊት እና ለህወሓት ጥያቄ አቅርቦ ምላሽ እየጠበቀ ነው።

በተመሳሳይ ሮይተርስ የዜና ወኪል አንድ ዲፕሎማቲክ ምንጭን ጠቅሶ "በዚህ ሳምንት በምዕራብ ትግራይ ለአጭር ጊዜ የቆየ ግጭት" በመከላከያ ሠራዊት እና በትግራይ ኃይሎች መካከል መካሄዱን ዘግቧል።

ግጭቱን በተመለከተ የፌደራል መንግሥቱም ሆነ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር እስካሁን ያሉት ነገር የለም።

ይህንንም ተከትሎ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከትግራይ እና ወደ ትግራይ የሚያደርጋቸው በረራዎች "ከዕቅድ ውጪ በመሆነ ምክንያት" መቋረቸወውን ለመንገደኞች በአጭር የጽሑፍ መልዕክት ትናንት አመሻሽ ላይ ካስታወቀ በኋላ በዛሬው ዕለት [ሐሙስ] በረራዎች ተቋርጠዋል።

የትግራይ ክልል ትራንስፖርት ቢሮ ኃላፊ ኃላፊ አቶ ታደለ መንግሥቱ በረራዎች መቋረጣቸውን ለቢቢሲ አረጋግጠው፤ ነገር ግን ዝርዝር መረጃ እንደሌላቸው ዛሬ ረፋድ ላይ ተናግረዋል።

ቢቢሲ ከአየር መንገዱ ይፋዊ ማብራሪያ ለማግኘት ያደረገው ሙከራ እስካሁን ምላሽ ባያገኝም፤ አንድ ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈቀዱ የአየር መንገዱ ባልደረባ እንደገለጹት "በረራዎች ለዛሬ [ሐሙስ] ብቻ ነው የተሰረዙት፤ ነገር ግን የቀጣይ ቀናት በረራዎች በሚኖረው ሁኔታ የሚወሰን ይሆናል" ብለዋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ በፌደራል መንግሥቱ እና በትግራይ ኃይሎች መካከል አዲስ ጦርነት ሊቀሰቀስ ይችላል በሚል ስጋት የትግራይ ክልል ነዋሪዎች ገንዘባቸውን ለማውጣት ወደ ባንኮች በብዛት መሄዳቸውን ሮይተርስ ዘግቧል።

የዜና ወኪሉ ጨምሮም አንድ የትግራይ ክልል ከፍተኛ ባለሥልጣን ክልሉ የአውሮፕላን በረራዎች ለምን እንደተቋረጡ ከፌደራል መንግሥቱ ማብራሪያ ጠይቆ ምላሽ እንዳላገኘ ተናግረዋል ብሏል።

የፌደራል መንግሥቱም ሆነ የኢትዮጵያ አየር መንገድ እስካሁን ወደ ትግራይ የሚደረጉ በረራዎች ስለመቋረጣቸው የሰጡት ማብራሪያ የለም።