የአፍሪካ ኅብረት የፌደራል መንግሥት እና ህወሓት የትግራይ ክልል ሁኔታን ላለማባባስ "እንዲታቀቡ" ጠየቀ

የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ማህሙድ አሊ ዩሱፍ፤ የፌደራል መንግሥት እና የህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) በክልሉ ያለውን ሁኔታ ላለማባባስ "ከፍተኛ ሁኔታ እንዲታቀቡ" ጠየቁ። በትግራይ ክልል አካባቢዎች እየተስተዋሉ ያሉት "ሰሞነኛ ክስተቶች እጅግ እንዳሳሰቧቸው" ሊቀ መንበሩ ገልጸዋል።

የኅብረቱ ሊቀመንበር ማህሙድ አሊ ዩሱፍ ይህንን ያሉት የዳግመኛ ግጭት ስጋት እያየለ የመጣበትን የፌደራል መንግሥት እና የትግራይ ኃይሎች መካረርን አስመልክተው ዛሬ አርብ ጥር 22/2018 ዓ.ም. ባወጡት መግለጫ ነው።

መቃቃር ውስጥ የሰነበቱት ሁለቱ አካላት ባለፉት ቀናት የትግራይ እና አማራ ክልሎች አዋሳኝ በሆነው ጸለምት አካባቢ ግጭት ውስጥ መግባታቸው ተዘግቧል።

የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ማህሙድ አሊ ዩሱፍ፤ "በትግራይ ክልል ክፍሎች እየተከናወነ ያለውን ሁኔታ በቅርበት እየተከታተሉ" እንደሆነ ገልጸዋል።

ኅብረቱ ያወጣው መግለጫ ሊቀመንበሩ "በትግራይ ክልል ክፍሎች ያለውን ሁኔታ በቅርበት እየተከታተሉ ሲሆን፣ ከሰሞኑ በታዩት ክስተቶች የተሰማቸውን ጥልቅ ስጋት ገልጸዋል" ይላል።

ሊቀመንበሩ በመግለጫቸው፤ በአፍሪካ ኅብረት የሚመራው እና የሁለት ዓመቱት ደም አፋሳሽ ጦርነት ያስቆመውን የፕሪቶሪያ ስምምነት ማስጠበቅ እንደሚገባም አሳስበዋል።

በስምምነቱ አማካኝነት "በከፍተኛ ጥረት የተገኙ ውጤቶችን ማስጠበቅ እጅግ የላቀ እና ቀጣይነት ያለው ጠቀሜታ" እንዳለው በመግለጫቸው አጽንኦት ሰጥተዋል።

"ሁሉም ወገኖች" ያለውን ሁኔታ ሊያባብሱ የሚችሉ እርምጃዎችን ከመውሰድ "በከፍተኛ ሁኔታ እንዲታቀቡ" እንዲሁም "መተማመንን ሊሸረሽሩ ከሚችሉ ድርጊቶች እንዲታቀቡ" ሊቀመንበሩ በመግለጫቸው ጠይቀዋል።

የፌደራል መንግሥት እና ህወሓት "ማናቸውንም ያልተፈቱ ጉዳዮችን የዘላቂ የግጭት የማቆም ስምምነቱን ግዴታዎች እና መንፈስ ሙሉ በሙሉ በማክበር ገንቢ በሆነ ውይይት እንዲፈቱም" ጥሪ አቅርበዋል።

የአፍሪካ ኅብረት የፕሪቶሪያ ስምምነት "ሙሉ በሙሉ እና ውጤታማ" በሆነ መልኩ እንዲፈጸም "የማይናወጥ ቁርጠኝነት" እንዳለው በመግለጫው አረጋግጧል።

በዚህ "የሰላም ግንባታ እና የእርቅ ሂደት" ውስጥ ለስምምነቱ ፈራሚ አካላት "የሚያደርገውን ቀጣይነት ያለው ድጋፍ" እንደሚቀጥልም አስታውቋል።

ኅብረቱ የዚህን ስምምነት አፈጻጸም ከመከታተል ባቋቋመው ከፍተኛ ፓነል አማካኝነት በሁለቱ ወገኖች መካከል የሚደረግ "ንግግር፣ ትብብር እና የመተማን ግንባታ" ሂደትን ለማጠናከር ዝግጁ መሆኑንም አመልክቷል። ይህንን የሚያደርገው "በትግራይ ክልል ዘላቂ ሰላም እና መረጋጋት" እንዲሰፍን ለማድረግ ለሚደረገው ጥረት ባለው ድጋፍ እንደሆነም ገልጿል።

የአፍሪካ ኅብረት በትግራይ ውስጥ ለሁለት ዓመታት የተካሄደውን ደም አፋሳሽ ጦርነት ያስቆመውን በፌደራል መንግሥቱ እና በህወሓት መካከል የተደረሰውን የፕሪቶሪያ ስምምነት ያደራደረ ዋነኛው አካል ነው።

ከስምምነቱ በኋላ ላለፉት ሦስት ዓመታት ሰላም ሰፍኖ የነበረ ቢሆንም ሁለቱም ወገኖች ስምምነቱ ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ አልሆነም በማለት ሲካሰሱ ቆይተዋል።

ላለፉት ወራት በፌደራል መንግሥቱ እና በህወሓት መካከል ያለው አለመግባባት እየተባባሰ ውጥረት ውስጥ የቆዩ ሲሆን፣ በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ላይ ግጭቶች መካሄዳቸው ተዘግቧል።

በፌደራል መንግሥቱ የመከላከያ ሠራዊት እና በህወሓት መካከል ግጭቶች መካሄዳቸውን የዲፕሎማሲ እና የደኅንነት ምንጮች የተናገሩ ቢሆንም፤ መንግሥትም ሆነ ህወሓት እስካሁን ስለ ሁኔታው ላይ በይፋ የገለጹት ነገር የለም።