ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በአላማጣ እና ኮረም የተከሰተው ምንድን ነው?
የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት እና የፌደራል ኃይሎች ከአላማጣ እና ኮረም ከተሞች መውጣታቸውን እየተዘገበ ባለበት ወቅት ነዋሪዎችም ለደኅንነታቸው በመስጋት እየሸሹ መሆናቸውን ለቢቢሲ ገለጹ።
ግጭት ይቀሰቀሳል በሚል እና ታጣቂዎች "የሚወስዱት እርምጃ ስጋት ፈጥሮብናል" ያሉ ነዋሪዎች ወደ አጎራባች አካባቢዎች በመጓዝ ላይ መሆናቸውን ነዋሪዎች ተናግረዋል።
የአላማጣ ነዋሪ እንዲሁም የቀድሞ የአካባቢው ባለሥልጣን እና በትግራይ ጊዜያዊ አስተዳዳር ሥር የአላማጣ ከተማ ከንቲባ የነበሩት አቶ ዝናቡ ደስታ በከተማው ውጥረት መኖሩን እና ነዋሪዎች እየሸሹ እንደሚገኙ ገልጸዋል።
ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ ቢቢሲ ያነጋገራቸው ግለሰብ ከአላማጣ ሸሽተው ወደ ቆቦ መሄዳቸውን ተናግረዋል።
"አሁን [ሐሙስ] ቆቦ ነን። አልጋ የሚባል የለም። በጣም ውድ የሆኑ አልጋዎች ብቻ ናቸው የቀሩት" ያሉት ነዋሪው "ቤተሰብ ያለው ቤተሰብ ጋር ወይም አልጋ ለሁለትም ለሦስትም ይዞ ነው ያለው" ብለዋል።
"አብዛኛው ወጣት እየወጣ ያለው ታፍነው ወደ ጦር ሜዳ እንዳይሰለፉ ለማምለጥ ነው። ሁሉም መሸሽ ነው የሚፈልገው" ሲሉም አክለዋል።
"ኮማንድ ፖስቱ ማለትም የመከላከያ ታጣቂዎች እና የፌደራል ታጣቂዎች ራሳቸውን ብቻ መታደግ ጀመሩ። እነሱ ካምፓቸውን ለቅቀው ሲወጡ ሕዝቡ በእግሩ መውጣት ጀመረ" ብለዋል ነዋሪው።
ሐሙስ ጠዋት በአንድ መኪና የወጡ ሰዎች እንደነበሩ ጠቅሰው "አሁን መኪናም ታግዷል አያስወጡም። ንብረትም ይዞ መውጣት አይቻልም" ብለዋል።
የከተማው ነዋሪዎች ከረቡዕ ጥር 20/2018 ዓ.ም. ምሽት ጀምሮ በእግራቸው እንደወጡም ገልጸዋል። "በእግር ጫካ ለጫካ ነው [የወጡት]። አሁን ደግሞ የጫካውንም መንገድ ሰምተው ዘግተውታል" ሲሉ ነዋሪው አክለዋል።
መከላከያ ሠራዊት እና የፌደራል ኃይሎች ከካምፓቸው ወጥተው "ወደ ጥሙጋ አፈግፍገዋል ሲሉን ደነገጥን" በማለት በሕዝቡ ዘንድ የተፈጠረውን አብራርተዋል።
በአላማጣ ከተማ የተለያዩ የአስተዳደር ቢሮዎች ሠራተኞች ወደ አንድ ቦታ መሰብሰብ መጀመራቸው ከተሰማ በኋላ "ወደ ማታ አካባቢ የትግራይ አመራሮች ተቋሞችን መያዝ ጀመሩ" ሲሉ ገልጸዋል።
መከላከያ ሠራዊት እና የፌደራል ኃይሎች ረቡዕ ሌሊት ከ8 እስከ 10 ሰዓት ባለው ጊዜ መውጣት መጀመራቸውንም ተናግረዋል።
"ሲቪሎች ተደናግጠው ሌሊት አምስትም፣ ስድስት ሰዓትም መውጣት ጀምረዋል" ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ነዋሪው አክለውም "ምንም ተኩስ አልነበረም። የሆነ ቢሮ ሲቆጣጠሩ ባንዲራ ይሰቅላሉ። ወደ ላይ ይተኩሳሉ። የተኩስ ልውውጥ አልተካሄደም። አርሚ 24 እና አርሚ 33 የሚባሉት በከፍተኛ ቁጥር እየገቡ ነበር" ብለዋል።
ለደኅነንታቸው ሲባል ስማቸው እንዲገለጽ ያልፈለጉ አንድ የቀድሞ የአካባቢው ባለሥልጣን የፌደራል ኃይሎች ከተማዋን ለቅቀው የወጡት ሌሊት ስምንት ሰዓት ጀምሮ እንደሆነ ለቢቢሲ ገልጸዋል።
"አወዛጋቢ ቦታ ነው፤ ፌደራል ነበር የሚቆጣጠረው። በሁለቱም ወገን ያለው የመንግሥት መዋቅር ፈርሷል። ኮማንድ ፖስት ነበር የሚያስተዳድረው" ብለዋል።
የቀድሞው ባለሥልጣን አክለውም "አሁን ግን ሙሉ በሚሉ ሠራዊቱ ስለወጣ ሙሉ ሌሊቱን በታጣቂዎች ሰው ሲታሰር እና ሲታፈን ነው ያደረው። ዘረፋም እየተፈጸመ ነው። ብዙው ነዋሪ ወደ ቆቦ እና ወልዲያ ሸሽቶ ወጥቷል።"
በአካባቢው ምንም ዓይነት ተኩስ እንዳልነበረ ነዋሪዎች ለቢቢሲ ገልጸው፤ "የትግራይ ኃይሎች የተለያዩ አርሚዎችን ሲያስጠጉ ስለነበር የፌደራል ኃይሎች ኃይላቸውን ለመሰብሰብ ብለው" ከስፍራው ሳይወጡ እንዳልቀረ አመልክተዋል።
በአካባቢው ያለው ሁኔታ "ወደ ግጭት የሚያመራ ይመስለኛል" ያሉት የቀድሞው የአካባቢው ባለሥልጣን፤ ሠራዊቱ አሁን ላይ ወደ ቆቦ እና ጮቢ የተባለ አካባቢ እንደሰፈረ ተናግረዋል።
"የትግራይ ኃይሎች ቀድሞም ከተማው ውስጥም ገጠር አካባቢም ነበሩ" ያሉት የቀድሞ ባለሥልጣኑ፤ "የተለያዩ ወንጀሎች ቢፈጸምም የኃይል መመጣጠን ስላልነበረ መከላከያም ፌደራል ፖሊሶችም ማስቆም አልቻሉም ነበር" ብለዋል።
አሁን ላይ "ሙሉ በሙሉ አካባቢው በትግራይ ኃይሎች ሥር" አንደሚገኝም አክለዋል። በነዋሪዎች ዘንድም "ከፍተኛ የሆነ ሽብር እና ስጋት" እንዳለም ገልጸዋል።
በትግራይ ጊዜያዊ አስተዳዳር ሥር የአላማጣ ከተማ ከንቲባ የነበሩት እና አሁን ላይ የከተማዋን ሁኔታ በቅርበት የሚከታተሉ አቶ ዝናቡ ደስታ "ከሁለት ሦስት ቀናት በፊት ጦርነቱ በማይፀብሪ አካባቢ፣ በፀለምት በይፋ ጀምረዋል" ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
"አሁንም የ2013፣ 2014 እና 2015 ተመሳሳይ የሆነ በወጣቱ ላይ እልቂት ጀምረዋል። ቶሎ ብሎ ሊቋረጥ ካልቻለ መልሶ የትግራይ ሕዝብ በተለይ እናቶች የሚያለቅሱበት ነው የሚሆነው" ሲሉ ስጋታቸውን ገልጸዋል።
ረቡዕ ምሽት የመከላከያ ሠራዊት እና የፌደራል ኃይሎች ከአላማጣ ለቅቀው መውጣታቸውን አረጋግጠው "አሁን በከተማው ላይ ሰፊ ውጥረት አለ" ብለዋል።
በአሁኑ ሰዓት "ሰዎች እየታፈኑ ነው" ያሉት አቶ ዝናቡ "ሪዞር ተብሎ የሚጠራው አካባቢ እና ራያ አላማጣ ፖሊስ ጣቢያ አካባቢ የማሰሪያ ማዕከላት አሉ" ብለዋል።
ኮማንድ ፖስቱ ከአካባቢው ለቅቆ እንደወጣ እና በትግራይ ኃይሎች ቁጥጥር እንደሚገኝ ጠቅሰው ሕዝቡ በተፈጠረው ነገር ተረብሾ በስጋት ውስጥ እንዳለም አመልክተዋል።
የመከላከያ ሠራዊት እና የፌደራል ኃይሎች ሲወጡ "የተኩስ ልውውጥ እንዳልነበረ" ተናግረው "አሁን ግን የጦርነት ድምጽ አለመሰማቱ እንጂ የጦርነት ድባብ ነው በአካባቢው ያለው" ብለዋል።
"ሕብረሰቡ በትልቅ ውጥረት እና ስጋት ላይ ነው ያለው። እየታሰረ፣ እየተዘረፈ ነው ያለው። ሥርዓት አልበኛነት ነግሷል" ሲሉም ለቢቢሲ ገልጸዋል።
ቢቢሲ ከትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር በኩል እስካሁን ምላሽ አላገኘም። ቢቢሲ ያነጋገራቸው ነዋሪ፣ የቀድሞ የአካባቢው ባለሥልጣን እና አቶ ዝናቡም "ዝርፊያ፣ እስራት እና አፈና" እየተፈጸመ መሆኑን ቢናገሩም ቢቢሲ ከገለልተኛ ወገን ክሶቹን ማጣራት አልቻለም።
ስላለው ወቅታዊ ሁኔታ ከትግራይ አስተዳደርም ሆነ ከፌደራል መንግሥት በኩል እስካሁን በይፋ የተገለጸ ነገር ባይኖርም፤ በሌላ አካባቢ በመከላከያ ሠራዊት እና በትግራይ ኃይሎች መካከል ግጭት መከሰቱን ዲፕሎማቲክ ምንጮች ተናግረዋል።
የፈረንሳይ ዜና አገልግሎት እና ሮይተርስ የደኅንነት እና ዲፕሎማሲያዊ ምንጮችን ጠቅሰው እንደዘገቡት ጸለምት በሚባል አካባቢ ባለፉት ቀናት ግጭቶች እንደነበሩ አረጋግጠዋል።
ሐሙስ ዕለት ደግሞ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከአዲስ አበባ ወደ ተለያዩ የትግራይ ክልል ከተሞች የሚያደርጋቸው በረራዎች መሰረዛቸውን ተጓዦች፣ አንድ የክልሉ ባለሥልጣን እና የአየር መንገዱ ምንጭ ለቢቢሲ አረጋግጠዋል።
ለሁለት ዓመታት የተካሄደውን የትግራይ ጦርነትን ተከትሎ በተደረሰው የሰላም ስምምነት ላላፉት ሦስት ዓመታት ጦርነት ቆሞ የነበረ ሲሆን፣ አሁን የተፈጠረው ውጥረት ሌላ ዙር ጦርነትን እንዳይቀሰቅስ ስጋት ፈጥሯል።
ቀናት ያስቆጠሩ አሳሳቢ ክስተቶችን በተመለከተ የኢትዮጵያ መንግሥትም ሆነ የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር አስካሁን ያሉት ነገር የለም።