አንድ ከፍተኛ የእስራኤል ባለሥልጣን በጋዛ 70 ሺህ ሰዎች እንደተገደሉ ማመናቸውን መገናኛ ብዙኃን ዘገቡ

የእስራኤል ጦር በጋዛ 70 ሺህ ፍልስጤማዊያን ተገድለዋል ብሎ እንደሚያምን የእስራኤል መገናኛ ብዙኃን አንድ ከፍተኛ ወታደራዊ ምንጭ ጠቅሰው ዘገቡ።

እስራኤል ከዚህ ቀደም በሐማስ የሚመራው የጋዛ የጤና ሚኒስቴር የሚያወጣውን ቁጥር አትቀበልም ነበር።

ነገር ግን የተባበሩት መንግሥታትን ጨምሮ ሌሎች የሰብዓዊ መብት ድርጅቶች እና ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃን ይህን ቁጥር ሲዘግቡት ቆይተዋል።

በአውሮፓውያኑ ጥቅምት 2023 ሐማስ በደቡብ እስራኤል ድንገተኛ ጥቃት ፈፅሞ 1200 ሰዎችን ሲገድል 251 ሰዎችን አግቶ መውሰዱ ይታወሳል። ይህ ክስተት የጋዛው ጦርነት ምክንያት ሆኗል።

እስራኤል ለዚህ ምላሽ በጋዛ ወታደራዊ ዘመቻ ያካሄደች ሲሆን በዚህ ወቅት 71 ሺህ 660 ሰዎች መገደላቸውን በሐማስ የሚመራው የጋዛ የጤና ሚኒስቴር መረጃ ያሳያል።

ሚኒስቴሩ ባለፈው ጥቅምት በሐማስ እና በእስራኤል መካከል የተኩስ አቁም ከተደረገ በኋላ ቢያንስ 492 ፍልስጤማዊያን ተገድለዋል ይላል። አራት እስራኤላዊያን መገደላቸውም ተነግሯል።

እስራኤል በተደጋጋሚ የሐማስን የሟቾች ቁጥር እንደማትቀበለው የገለፀች ሲሆን ካለፈው የአውሮፓውያኑ ዓመት የተኩስ አቁም በፊት 1600 ተዋጊዎች እንዲሁም በጦርነቱ ወቅት 22 ሺህ ታጣቂዎች መግደሏን ትናገራለች።

የእስራኤል መከላከያ ሠራዊት ከዚህ ቀደም በእያንዳንዱ ሟች ተዋጊ ቁጥር ልክ ሁለት ወይም ሶስት ሰላማዊ ዜጎች መገደላቸውን እንደሚያምን ገልፆ ነበር።

አንድ ከፍተኛ የእስራኤል ወታደራዊ ምንጭን ጠቅሰው ሀሬትዝ እና ታይምስ ኦፍ እስራኤልን ጨምሮ ሌሎች መገናኛ ብዙኃን እንደዘገቡት የሐማስ የጤና ሚኒስቴር የገለፀው ቁጥር ከሞላ ጎደል ትክክለኛ ነው። ነገር ግን ከሟቾቹ መካከል ምን ያህሉ ተዋጊዎች እንደሆኑ እና ምን ያህሉ ደግሞ በግጭቱ ምክንያት እንደሞቱ ማወቅ እንዳልቻሉ ዘግበዋል።

የእስራኤል መገናኛ ብዙኃንን ዘገባ ተከትሎ አንድ ወታደራዊ ባለሥልጣን ዘገባዎቹ የእስራኤል መከላከያ ሠራዊትን ኦፊሴላዊ መረጃ የማያንፀባርቅ ነው ብለዋል።

"ይህን በተመለከተ የሚወጣ የትኛውም ዘገባ በኦፊሴላዊ እና ትክክለኛው መንገድ የሚለቀቅ ይሆናል" ሲል ሠራዊቱ መግለጫ አውጥቷል።