የአውሮፓ ኅብረት የኢራን እስላማዊ አብዮታዊ ዘብን በአሸባሪነት ፈረጀ

ኢራን ባለፉት ሳምንታት ተቃዋሚዎች ላይ የወሰደችውን በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን የገደለ እርምጃ ተከትሎ የአውሮፓ ኅብረት የኢራን እስላማዊ አብዮታዊ ዘብን የአሸባሪዎች ዝርዝር ውስጥ አካተተ።

የአውሮፓ ኅብረት ኮሚሽን ምክትል ፕሬዝዳንት የሆኑት ካጃ ካላስ፤ ይህ እርምጃ ኢራን ውስጥ ዋነኛ ወታደራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ኃይል የሆነውን እስላማዊ አብዮታዊ ዘብ እንደ አል ቃኢዳ እና ኢስላሚክ ስቴት ያሉ ጂሃዳዊ ቡድኖች ተርታ እንደሚያስቀምጠው ተናግረዋል።

ምክትል ፕሬዝዳንቷ አክለውም፤ "ጭቆና ምላሽ ሳይሰጠው አያልፍም" ብለዋል።

ኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አባስ አራግቺ በበኩላቸው የአውሮፓ ኅብረት ውሳኔን "ተውኔታዊ" እና "ጉልህ ስትራቴጂክ ስህተት" ሲሉ ጠርተውታል።

የኅብረቱ ምክትል ፕሬዝዳንት ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ባሰፈሩት አጭር መግለጫ፤ "በሺዎች የሚቆጠር የራሱን ሕዝብ የሚገድል የትኛውም አገዛዝ ራሱን ወደ ሞቱ ለመውሰድ እየሠራ ነው" ብለዋል።

ምንም እንኳ አብዮታዊ ዘቡ የአሸባሪዎች ዝርዝር ውስጥ ቢካተትም፤ ምክትል ፕሬዝዳንቷ በኢራን እና በኅብረቱ መካከል ያለው ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቶች ክፍት ሆነው ይቆያሉ ብለው እንደሚጠብቁ ገልጸዋል።

በአዲሱ ውሳኔ መሠረት የአውሮፓ ኅብረት በስድስት የኢራን ተቋማት እና በአገሪቱ በሚገኙ 15 ሰዎች ላይ ማዕቀብ ተጥሏል። ማዕቀብ ከተጣለባቸው መካከል የአገር ውስጥ ጉዳዮች ሚኒስትሩ እስካንዳር ሞሜኒ፣ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕጉ ሞሐመድ ሞቫሄዲ አዛድ እንዲሁም ዋና ዳኛው ኢማን አፍሻሪ ይገኙበታል።

የአውሮፓ ኅብረት በመግለጫው "እነዚህ ሁሉም ሰላማዊ ተቃዋሚዎች ላይ እንዲሁም የዘፈቀደ የፖለቲካ አክቲቪስቶች እና የሰብአዊ መብቶች ተሟጋቾች ላይ በተወሰደው ኃይል የተሞላበት አፈና ላይ ተሳትፈዋል" ብሏል።

የአውሮፓ ኅብረት የአሸባሪዎች ዝርዝር ውስጥ የተካተቱ ተቋማት የጉዞ እና የሀብት እገዳን ጨምሮ የተለያዩ ማዕቀቦች ያጋጥሟቸዋል። እነዚህ እርምጃዎች ማዕቀቡ የሚጣልባቸው አካላት ያላቸውን የድጋፍ መረብ ለመበጠስ ያለመ ነው።

የሰብአዊ መብት ተሟጋች ቡድኖች ለሳምንታት በዘለቀው ተቃውሞ ወቅት በሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎች እንደ አብዮታዊ ዘቡ ባሉ የፀጥታ ኃይሎች እንደተገደሉ ግምታቸውን አስቀምጠዋል።

ብራስልስ ውስጥ ንግግር ያደረጉት የፈረንሳይ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጄን ኖይል ባሮት "በዘመናዊ የኢራን ታሪክ ውስጥ እጅግ አስከፊ የሆነ ጭቆና" ሲሉ በተቃውሞው ወቅት የተወሰደውን እርምጃ ገልጸውታል። "ለተፈጸሙት ወንጀሎች አንድም ተጠያቂነት" ላይኖር እንደሚችልም ተናግረዋል።

ፈረንሳይ ከዚህ ቀደም አብዮታዊ ዘቡ የአውሮፓ ኅብረት የአሸባሪዎች ዝርዝር ውስጥ እንዲካተት ለማድረግ ስታመነታ ቆይታለች። ይህ መቆጠቧ ከኢራን ጋር ያላትን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ላለማቋረጥ ከመፈለጓ የሚመነጭ ነው።

ረቡዕ ዕለት ግን ይህንን አቋሟን ቀይራ በጣልያን ሲመራ ለነበረው ይህንን እርምጃ የማስፈጸም እንቅስቃሴ ከጀርባ ሆና ከፍተኛ ድጋፍ ሰጥታለች።

እጅግ ኃያል የኢራን ወታደራዊ ኃይል የሆነው እስላማዊ አብዮታዊ ዘብ በአውሮፓውያኑ 1979 ከፈነዳው አብዮት ጥቂት ጊዜ በኋላ የተቋቋመው የአገሪቱን እስላማዊ ሥርዓት ለማስጠበቅ ሲባል ነበር።

ወደ 190 ሺህ ገደማ ወታደሮች እንዳሉት የሚገመተው ይህ ኃይል በየብስ፣ በአየር እና በባሕር ላይ የመዋጋት አቅም አለው። የኢራንን ስትራቴጂካዊ መሳሪያዎችንም በበላይነት ይቆጣጠራል።

ለአጋር መንግሥታት እና ለታጠቁ ቡድኖች ገንዘብ፣ መሳሪያ፣ ቴክኖሎጂ እና ምክር በመስጠት በውጭ አገራት ላይ ተጽዕኖውን ያሳርፋል።

በተጨማሪም በኢራን ውስጥ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ አባላት ያሉት እና ተቃውሞዎችን ለማፈን የሚውለውን 'ባሲጅ ሬዚስታንስ ፎርስ' የተባለውን ከፊል ወታደራዊ ኃይልንም ይቆጣጠራል።