በቱርክና በሶሪያ በደረሱ ርዕደ መሬቶች ከ15 ሺህ ሰዎች በላይ ሞቱ

በቱርክ የደረሰው ርዕደ መሬት

በቱርክ እና በሰሜን ሶሪያ በተከሰቱት አስከፊ ርዕደ መሬቶች ቢያንስ የ15 ሺህ ሰዎች ህይወት ማለፉ ተረጋገጠ።

በሃገራቱ ዕሁድ ለሰኞ ሌሊት የደረሱት ርዕደ መሬቶች በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን ህይወት ቀጥፏል እንዲሁም በርካቶችም ጉዳት ደርሶባቸዋል።

የነፍስ አድን ሰራተኞች በርዕደ መሬቶቹ ከፈራረሱ ህንጻዎችና ቤቶች ስር ተጎጂዎችን ለማውጣት እየሞከሩ ሲሆን የሟቾችም ቁጥር ከፍተኛ ሊሆን እንደሚችልም የዓለም ጤና ድርጅት አስጠንቅቋል።

በአደጋው ከ23 ሚሊዮን በላይ ሰዎች ሊጎዱ ይችላሉም ተብሏል።

የነፍስ አድን ሰራተኞች ከአስከፊ ውሽንፍርና ዝናብም ጋር በመታገል በሺዎች ከሚቆጠሩ ህንጻዎች ፍርስራሽ ውስጥ ነዋሪዎችን ለመታደግ እየሞከሩም ይገኛሉ። በነዚህ ርዕደ መሬቶች የበርካቶች ህይወት መቀጠፍ በተጨማሪ በሺዎች የሚቆጠሩ ህንጻዎችም ተደርምሰዋል።

ሆኖም በቱርክ በአንዳንድ አካባቢዎች የነፍስ አድን ሰራተኞች ምላሽ የዘገየ ነው በማለት ቤተሰቦቻቸውንና ዘመዶቻቸውን ለመፈለግና ህይወታቸውን ለማዳን ያላቸውን መሳሪያዎች ይዘው ወጥተዋል።

በርዕደ መሬቶቹ ክፉኛ በተጎዱ 10 የቱርክ ግዛቶች ለሶስት ወራት የሚቆይ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ታውጇል።

የቱርክ ፕሬዚዳንት ሬሲፕ ጣይብ ኤርዶጋን ርዕደ መሬቶቹ ክፉኛ የመቷቸውን አካባቢዎች ለመጎብኘት ማቅናቸውን የዜና ወኪሎች ዘግበዋል። የርዕደ መሬቶቹ ማዕከል የሆነችውን ፓዛርቺክን ጨምሮ ካህራማንማራስ እና ሃታይ እንደሚጎበኙም ተነግሯል።

አንዳንዶች ዕርዳታ እንዳልደረሳቸው እየተናገሩ ባሉበት ወቅትም መንግሥት ያሳየው ቸልተኝነት ቁጣን ቀስቅሷል።

በደቡባዊ ቱርክ ኑሙን ነዋሪ የሆነችው አርዙ ዴዴኦግሉ ሁለት የእህቶቿ ልጆች ከፍርስራሹ ስር እንዳሉና እስካሁን ምንም እርዳታ እንዳልደረሳቸው ለቢቢሲ ተናግራለች።

ህጻናቱ በህይወት ላይኖሩ እንደሚችሉም በኃዘኔታ የተናገረችው ግለሰቧ “የነፍስ አድን ሰራተኞች ለምን እንዳልመጡም ጠይቃለች።

በደቡባዊዋ አንታክያ ነዋሪ የሆኑትና ከርዕደ መሬቶቹ የተረፉት የ64 ዓመቷ ሜሌክ “ድንኳኖቹ የት አሉ? የምግብ መኪኖቹስ?” ሲሉም ተናግረዋል።

“በኃገራችን ከዚህ ቀደም ከደረሱት አደጋዎች በተለየ ሁኔታ እርዳታ ለሚሹ ሰዎች ምግብ እየተሰራጨ አይደለም። ከርዕደ መሬቶቹ አደጋ ብንተርፍም በረሃብ ወይም በብርድ መሞታችን ነው” ብለዋል።

መንግሥት ባሳየው ቸልተኝነት የተቆጡ በርካቶች ጉዳዩን ወደ ማህበራዊ ሚዲያ የወሰዱት ሲሆን፤ የከፋ ጉዳት የደረሰባቸው አካባቢዎች ምንም እርዳታ አልደረሳቸውም ሲሉም ወቅሰዋል።

በዓለም ዙሪያ ያሉ ሃገራት ልዩ ቡድኖችን፣ አነፍናፊ ውሻዎችና መሳሪያዎችን ጭምር በመላክ ድጋፋቸውን እያሳዩ ይገኛሉ። ከነዚህም ውስጥ ጣሊያን፣ አሜሪካ፣ እስራኤልና ታይዋን ይገኙበታል።